ሕዝቅኤል 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 እርሱም፥ “የሰው ልጅ ሆይ! ያገኘኸውን ብላ፤ ይህን መጽሐፍ ብላ፤ ሄደህም ለእስራኤል ልጆች ተናገር” አለኝ። 2 አፌንም ከፈትሁ፤ መጽሐፉንም አበላኝ። 3 እርሱም፥ “የሰው ልጅ ሆይ! አፍህ ይብላ፤ በምሰጥህም በዚህ መጽሐፍ ሆድህን ሙላ” አለኝ። እኔም በላሁት፤ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠ። 4 እንዲህም አለኝ፥ “የሰው ልጅ ሆይ! ተነሥተህ ወደ እስራኤል ቤት ሂድና ግባ፥ ቃሌንም ንገራቸው። 5 ወደ እስራኤል ቤት እንጂ ንግግራቸው ልዩ ወደ ሆነ፥ ቋንቋቸውም ወደማይታወቅ ሕዝብ አልተላክህምና፤ 6 ንግግራቸው ልዩ ወደ ሆነ፥ ቋንቋቸውም ሌላ ወደ ሆነ፥ ቃላቸውንም ታውቅ ዘንድ ወደማይቻልህ ሕዝብ አልላክሁህም። ወደ እነዚያስ ልኬህ ቢሆን ኖሮ በሰሙህ ነበር። 7 ነገር ግን የእስራኤል ቤት ሁሉ ክፉዎችና ልበ ደንዳኖች ናቸውና፥ እኔንም መስማት እንቢ ብለዋልና የእስራኤል ቤት አንተን አይሰሙህም። 8 እነሆ ፊትህን በፊታቸው አጸናሁት፤ ኀይልህንም ከኀይላቸው ይልቅ አጸናለሁ። 9 ሁልጊዜ ከዓለት ይልቅ ትጸናለህ፤ አትፍራቸው፤ ከፊታቸውም አትደንግጥ፤ ዐመፀኛ ቤት ናቸውና።” 10 እርሱም፥ “የሰው ልጅ ሆይ! የነገርሁህን ቃሌን ሁሉ በልብህ ጠብቀው፤ በጆሮህም ስማው። 11 ተነሥተህም ወደ ተማረኩ ወደ ወገንህ ልጆች ሂድ፤ እነርሱም ቢሰሙ ወይም ቢፈሩ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገራቸው” አለኝ። 12 መንፈስም ወደ ላይ ወሰደኝ፤ በኋላዬም፥ “የእግዚአብሔር ክብር ከቦታው ይባረክ” የሚል የታላቅ ንውጽውጽታ ድምፅ ሰማሁ። 13 የእነዚያም እንስሳ ክንፎች እርስ በርሳቸው ሲማቱ፥ በአጠገባቸውም የመንኰራኵሮችን ድምፅ፥ የታላቁንም ንውጽውጽታ ድምፅ ሰማሁ። 14 መንፈስም አንሥቶ ወሰደኝ፤ እኔም በምሬትና በመንፈሴ ሙቀት ሄድሁ፤ የእግዚአብሔርም እጅ በላዬ በርትታ ነበር። 15 በቴልአቢብም ወደ አሉ፥ በኮቦርም ወንዝ አጠገብ ወደ ተቀመጡ ምርኮኞች መጣሁ፤ በተቀመጡበትም ቦታ ተቀመጥሁ፤ በዚያም በመካከላቸው እየተመላለስሁ ሰባት ቀን ተቀመጥሁ። እግዚአብሔር ሕዝቅኤልን ጠባቂ አድርጎ እንደ ሾመው 16 ከሰባቱም ቀን በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 17 “የሰው ልጅ ሆይ! ለእስራኤል ቤት ጕበኛ አድርጌሃለሁ፤ ስለዚህ የአፌን ቃል ስማ፤ በቃሌም ገሥጻቸው። 18 እኔ ኀጢአተኛውን፥ “በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁት ጊዜ አንተም ባትነግረው፥ ነፍሱም እንድትድን ከክፉ መንገዱ ይመለስ ዘንድ ለኀጢአተኛው ባትነግረው፥ ያ ኀጢአተኛ በኀጢአቱ ይሞታል፤ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። 19 ነገር ግን አንተ ኀጢአተኛውን ብትገሥጸው እርሱም ከኀጢአቱና ከክፉ መንገዱ ባይመለስ፥ በኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ነፍስህን ታድናለህ። 20 ደግሞ ጻድቁ ከጽድቁ ተመልሶ ኀጢአት በሠራ ጊዜ እኔ በፊቱ ዕንቅፋት ባደርግ፥ እርሱ ይሞታል፤ አንተም አልነገርኸውምና በኀጢአቱ ይሞታል፤ ያደረጋትም የጽድቅ ነገር አትታሰብለትም፤ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። 21 ነገር ግን ኀጢአት እንዳይሠራ ጻድቁን ብትገሥጸው፥ እርሱም ኀጢአት ባይሠራ፥ ጻድቅ ነውና በሕይወት ይኖራል፤ አንተም ነፍስህን አድነሃል።” 22 በዚያም የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ነበረች፤ እርሱም፥ “ተነሥተህ ወደ ሜዳ ሂድ፤ በዚያም እነግርሃለሁ” አለኝ። 23 እኔም ተነሥቼ ወደ ሜዳው ሄድሁ፤ እነሆም በኮቦር ወንዝ እንዳየሁት ክብር ያለ የእግዚአብሔር ክብር በዚያ ቆሞ ነበር፤ በግምባሬም ተደፋሁ። 24 መንፈስም ወደ እኔ መጣ፤ በእግሬም አቆመኝ፤ ተናገረኝም እንዲህም አለኝ፥ “ሂድ ገብተህ ቤትህን ዝጋ። 25 አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ! እነሆ ገመድ ያደርጉብሃል፤ ያስሩህማል፤ አንተም ከመካከላቸው አትወጣም፤ 26 እኔም ምላስህን ከትናጋህ ጋር አጣብቃታለሁ፤ አንተም ዲዳ ትሆናለህ፤ እነርሱም ዐመፀኛ ቤት ናቸውና የሚዘልፍ ሰው አትሆንባቸውም። 27 ነገር ግን በተናገርሁህ ጊዜ አፍህን እከፍታለሁ፤ እነርሱም ዐመፀኛ ቤት ናቸውና አንተ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሚሰማ ይስማ፤ እንቢ የሚልም እንቢ ይበል” ትላቸዋለህ። |