ሕዝቅኤል 29 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በግብፅ ላይ የተነገረ ትንቢት 1 በዐሥረኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር ከወሩም በዐሥራ ሁለተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ! ፊትህን በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ላይ አድርግ፤ በእርሱና በግብፅ ሁሉ ላይም ትንቢት ተናገር፤ 3 እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በወንዞች መካከል የሚተኛ፥ ወንዙ የእኔ ነው፤ ለራሴም ሠርቼዋለሁ የሚል ታላቅ ዘንዶ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ሆይ! እነሆ በአንተ ላይ ነኝ። 4 በመንጋጋዎችህ መቃጥን አገባብሃለሁ፤ የወንዞችህንም ዓሦች ሁሉ ወደ ቅርፊትህ አጣብቃለሁ፤ ከወንዞችህም መካከል አወጣሃለሁ፤ የወንዞችህም ዓሦች ሁሉ ወደ ቅርፊትህ ይጣበቃሉ። 5 አንተንና የወንዞችህን ዓሦች ሁሉ ወደ ምድረ በዳ እጥላለሁ፤ በምድርም ፊት ላይ ትወድቃለህ እንጂ አትከማችም፤ አትሰበሰብምም፤ መብልም አድርጌ ለምድር አራዊትና ለሰማይ ወፎች ሰጥቼሃለሁ። 6 ለእስራኤል ቤት የሸንበቆ በትር ሁነሃቸዋልና በግብፅ የሚኖሩ ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 7 በእጅ በያዙህ ጊዜ ተሰበርህ፤ ጫንቃቸውንም ሁሉ አቈሰልህ፤ በተደገፉብህም ጊዜ ተሰበርህ፤ ወገባቸውንም ሁሉ አንቀጠቀጥህ። 8 “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ ሰይፍን አመጣብሃለሁ፦ ሰውንና እንስሳንም ከአንተ ዘንድ አጠፋለሁ። 9 የግብፅም ምድር ባድማና ውድማ ትሆናለች፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ አንተ፦ ወንዙ የእኔ ነው፤ የሠራሁትም እኔ ነኝ ብለሃልና። 10 ስለዚህ፥ እነሆ በአንተና በወንዞችህ ላይ ነኝ፤ የግብፅንም ምድር ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሰዌኔና እስከ ኢትዮጵያ ዳርቻ ድረስ በጦርና በቸነፈር ውድማና ባድማ አደርጋታለሁ። 11 የሰው እግር አያልፍባትም፤ የእንስሳም ኮቴ አይረግጣትም፥ እስከ አርባ ዓመትም ድረስ ማንም አይኖርባትም። 12 ባድማም በሆኑ ምድሮች መካከል የግብፅን ምድር ባድማ አደርጋታለሁ፤ በፈረሱትም ከተሞች መካከል ከተሞችዋ አርባ ዓመት ፈርሰው ይቀመጣሉ፤ ግብፃውያንንም ወደ አሕዛብ እበትናቸዋለሁ፤ በሀገሮችም እዘራቸዋለሁ።” 13 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ከአርባ ዓመት በኋላ ግብፃውያንን ከተበተኑባቸው አሕዛብ ዘንድ እሰበስባለሁ፤ 14 የግብፅንም ምርኮ እመልሳለሁ፤ ወደ ተወለዱባትም ምድር ወደ ጳትሮስ እመልሳቸዋለሁ፤ በዚያም የተዋረደች መንግሥት ይሆናሉ። 15 እንደ ገና በአሕዛብ ላይ ከፍ ከፍ እንዳይሉ ትንሽ መንግሥት ይሆናሉ፤ በአሕዛብም ላይ እንዳይበዙ አሳንሳቸዋለሁ። 16 የእስራኤል ቤት እነርሱን በተከተሉ ጊዜ እርስዋ በደልን ታሳስባለች፤ ከእንግዲህም ወዲያ መታመኛ አትሆንላቸውም፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” ንጉሥ ናቡከደነፆር ግብፅን ድል እንደ አደረገ 17 እንዲህም ሆነ፤ በሃያ ሰባተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 18 “የሰው ልጅ ሆይ! የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሠራዊቱን በጢሮስ ላይ ጽኑ ሥራን አሠራቸው፤ ራስ ሁሉ የተላጨ፥ ጫንቃም ሁሉ የተላጠ ሆኖአል፤ ነገር ግን በላይዋ ስለ አሠራው ሥራ እርሱና ሠራዊቱ ከጢሮስ ደመወዝ አልተቀበሉም። 19 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ የግብፅን ምድር ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እሰጠዋለሁ፤ ብዛቷንም ይወስዳል፤ ምርኮዋንም ይማርካል፤ ብዝበዛዋንም ይበዘብዛል፤ ይህም ለሠራዊቱ ደመወዝ ይሆናል። 20 ስለ እኔ ሠርተዋልና በጢሮስ ላይ ስለ አገለገለው አገልግሎት የግብፅን ምድር ደመወዝ አድርጌ ሰጥቼዋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 21 “በዚያ ቀን ለእስራኤል ቤት ቀንድን አበቅላለሁ፤ በመካከላቸውም ለአንተ የተከፈተ አፍን እሰጥሀለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” |