ሕዝቅኤል 28 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በጢሮስ ንጉሥ ላይ የተነገረ ትንቢት 1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 “አንተ የሰው ልጅ ሆይ! የጢሮስን አለቃ እንዲህ በለው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ልብህ ኰርትዋል፥ አንተ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ እግዚአብሔርም በባሕር መካከል እንዲቀመጥ እኔም ተቀምጫለሁ ብለሃልና፤ አንተ ሰው ስትሆን ልብህን እንደ እግዚአብሔር ልብ ብታደርግም አንተ እግዚአብሔር አይደለህም። 3 ከዳንኤል ይልቅ አንተ ጥበበኛ ነህን? ብልሃተኞችም በጥበባቸው አላስተማሩህም። 4 በጥበብህና በማስተዋልህ ብልጽግናን ለራስህ አግኝተሃልን? ወርቅንና ብርንም በግምጃ ቤትህ ውስጥ ሰብስበሃልን? 5 በታላቅ ጥበብህና በንግድህ ብልጽግናህን አብዝተሃል፤ በብልጽግናህም ልብህ ኰርቶአል። 6 ሰለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ልብህን እንደ እግዚአብሔር ልብ አድርገሃልና፤ 7 ስለዚህ እነሆ የሌላ ሀገር ሰዎችን፥ የአሕዛብ ጨካኞችን አመጣብሃለሁ፤ ሰይፋቸውንም በጥበብህ ውበት ላይ ይመዝዛሉ፤ ክብርህንም ያረክሳሉ። 8 ወደ ጕድጓድ ያወርዱሃል፤ በሰይፍም ትሞታለህ፤ ሬሳህንም ወደ ባሕር ይጥሉታል። 9 አንተ ሰው ስትሆን ለሚገድሉህ ሰዎች፦ እግዚአብሔር ነኝ ትላቸዋለህን? ሰው ነህ እንጂ እግዚአብሔር አይደለህም። 10 የሚወጉህም ሰዎች ብዙዎች ናቸው፤ ያልተገረዙትን ሰዎች ሞት ትሞታለህ፤ የሚገድሉህም ሰዎች ያልተገረዙት ናቸው፤ በእጃቸውም ትሞታለህ። እኔ ተናግሬአለሁና ይላል እግዚአብሔር።” 11 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 12 “የሰው ልጅ ሆይ! በጢሮስ ንጉሥ ላይ ሙሾ አሙሽበት፤ እንዲህም በለው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጥበብን የተሞላህ፥ ውበትህም የተፈጸመ መደምደሚያ አንተ ነህ። 13 በእግዚአብሔር ገነት በዔድን ነበርህ፤ የከበረ ዕንቍስ ሁሉ፥ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮን፥ አልማዝ፥ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያሰጲድ፥ ሰንፔር፥ በሉር፥ የሚያብረቀርቅ ዕንቍ፥ ወርቅም ልብስህ ነበረ፤ የከበሮህና የእንቢልታህ ሥራ በአንተ ዘንድ ነበረ፤ በተፈጠርህበትም ቀን ተዘጋጅተው ነበር። 14 አንተ ልትጋርድ የተቀባህ ኪሩብ ነበርህ፤ በተቀደሰው በእግዚአብሔር ተራራ ላይ አኖርሁህ፤ በእሳት ድንጋዮች መካከል ተመላለስህ። 15 ከተፈጠርህበት ቀን ጀምረህ በደል እስከሚገኝብህ ድረስ በመንገድህ ፍጹም ነበርህ። 16 በንግድህም ብዛት ግፍ በውስጥህ ተሞላ፤ ኀጢአትንም ሠራህ፤ ስለዚህ እንደ ርኩስ ነገር ከእግዚአብሔር ተራራ ጣልሁህ፤ የምትጋርድ ኪሩብ ሆይ! ከእሳት ድንጋዮች መካከል አጠፋሁህ። 17 በውበትህ ምክንያት ልብህ ኰርቶአል፤ ከክብርህ የተነሣ ጥበብህን አረከስህ፤ በምድር ላይ ጣልሁህ፤ ያዩህም፥ ይዘብቱብህም ዘንድ በነገሥታት ፊት አሳልፌ ሰጠሁህ። 18 በበደልህ ብዛት፥ በንግድህም ኀጢአት መቅደስህን አረከስህ፤ ስለዚህ እሳትን ከውስጥህ አውጥቻለሁ፤ እርስዋም በልታሃለች፤ በሚያዩህም ሁሉ ፊት በምድር ላይ አመድ አድርጌሃለሁ። 19 በአሕዛብም ውስጥ የሚያውቁህ ሁሉ ያለቅሱልሃል፤ አንተም ለድንጋጤ ሆነሃል፤ እስከ ዘለዓለምም አትኖርም።” 20 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 21 የሰው ልጅ ሆይ! ፊትህን ወደ ሲዶና አቅንተህ ትንቢት ተናገርባት፤ እንዲህም በል፦ 22 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሲዶና ሆይ! እነሆ በአንቺ ላይ ነኝ፤ በውስጥሽም እከብራለሁ፤ ፍርድንም በአደረግሁብሽ ጊዜ፥ በተቀደስሁብሽም ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ። 23 ቸነፈርንም በአንቺ ላይ፥ ደምንም በጎዳናሽ ላይ እሰድዳለሁ፤ ከዙሪያሽም በላይሽ ባለ ሰይፍ የተወጉ በመካከልሽ ይወድቃሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 24 ከእንግዲህም ወዲያ ለእስራኤል ቤት የሚወጋ እሾህ፥ በዙሪያቸውም ከአሉ ከናቋቸው ሁሉ የሚያቈስል ኩርንችት አይሆንም፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 25 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤልን ቤት ከተበተኑባቸው አሕዛብ ዘንድ እሰበስባቸዋለሁ፤ በአሕዛብና በሕዝብ ፊትም እቀደስባቸዋለሁ፤ ለባሪያዬ ለያዕቆብም በሰጠኋት ምድራቸው ይቀመጣሉ። 26 ተዘልለውም ይቀመጡባታል፤ ቤቶችንም ይሠራሉ፤ ወይኑንም ይተክላሉ፤ በዙሪያቸውም በአሉ በሚንቋቸው ሁሉ ላይ ፍርድን በአደረግሁ ጊዜ ተዘልለው ይቀመጣሉ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካቸው፥ የአባቶቻቸውም አምላክ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። |