ሕዝቅኤል 27 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ጢሮስ የወጣ ሙሾ 1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 “አንተ የሰው ልጅ ሆይ! ስለ ጢሮስ ሙሾ አድርግ። 3 በባሕር መግቢያ የምትኖር፥ በብዙም ደሴቶች ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ጋር ንግድን የምታደርግ ጢሮስን እንዲህ በላት፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጢሮስ ሆይ! አንቺ፦ በውበት ፍጹም ነኝ ብለሻል። 4 ዳርቻሽ በባሕር ውስጥ ነው፤ ልጆችሽም ውበትሽን ፈጽመዋል። 5 ሳንቃዎችሽን ሁሉ ከሳኔር ጥድ ሠርተዋል፤ ምሰሶዎችሽንም ይሠሩልሽ ዘንድ ከሊባኖስ ዝግባን ወስደዋል። 6 ከባሳን ኮምቦል መቅዘፊያሽን ሠርተዋል፤ መቅደስሽንም በዝኆን ጥርስ ሠሩ፤ ከኪቲም ደሴቶች ዛፍም ቤቶችሽን ሠርተዋል። 7 ዓላማ እንዲሆንልሽ ሸራሽ ከግብፅ በፍታና ከወርቀ ዘቦ ተሠርቶአል፤ መደረቢያሽም ከኤሊሳ ደሴቶች ሰማያዊና ቀይ ሐር ተሠርቶአል። 8 አለቆችሽ በሲዶና ይኖሩ ነበር፤ የአራድ ሰዎችም ቀዛፊዎችሽ ነበሩ፤ ጢሮስ ሆይ! ጥበበኞችሽ በአንቺ ዘንድ ነበሩ፤ የመርከቦችሽም መሪዎች ነበሩ። 9 በአንቺ ውስጥ የነበሩ የጌባል ሽማግሌዎችና ጥበበኞችዋ ስብራትሽን ይጠግኑ ነበር፤ ከአንቺም ጋር ይነግዱ ዘንድ የባሕር መርከቦች ሁሉና መርከበኞቻቸው በመካከልሽ ነበሩ። 10 ፋርስና ሉድ፥ ሊብያም በሠራዊትሽ ውስጥ ሰልፈኞችሽ ነበሩ፤ ጋሻና ራስ ቍርም በአንቺ ውስጥ ያንጠለጥሉ ነበር፤ እነርሱም ክብርሽን ሰጡ። 11 የአራድ ልጆችና ሠራዊቶችሽ በቅጥሮችሽ ላይ በዙሪያ ነበሩ፤ ገማዳውያንም በግንቦችሽ ውስጥ ነበሩ፤ የጦር መሣሪያቸውንም በዙሪያ በቅጥርሽ ላይ አንጠለጠሉ፤ ውበትሽንም ፈጽመዋል። 12 “ከኀይልሽ ሁሉ ብዛት የተነሣ የተርሴስ ሰዎች ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ ገበያሽን ብር፥ ወርቅና ብረት፥ ቆርቆሮና እርሳስም አደረጉ። 13 ያዋንና ቶቤል፥ ሞሳሕም ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ ንግድሽንም በሰዎች ነፍሳትና በናስ ዕቃ አደረጉ። 14 ከቴርጋማ ቤትም የነበሩት ሰዎች ፈረሶችንና ፈረሰኞችን፥ በቅሎዎችንም ወደ ገበያሽ አመጡልሽ። 15 የሮድያን ልጆችም ነጋዴዎችሽ ነበሩ፥ ብዙ የሆኑ የደስያት ሰዎችም የዝኆን ጥርስ ይነግዱልሽ ነበር፤ ከዚያም የመጡ ሰዎች ዋጋሽን ይሰጡሽ ነበር። 16 የሶርያም ሰዎች ከገንዘብሽ ብዛት የተነሣ ነጋዴዎችሽ ነበሩ፥ ከአንቺም ጋር አንድ ከሆኑ ከብዙ ሰዎች ጋር ትነግጂ ነበር፤ ነጭ ሐርንና ዕንቍን፥ ቀይ ሐርንና ወርቀ ዘቦን ከርከዴን የሚባል ዕንቍንና ልባንጃም የሚባል ሽቱን ከተርሴስ ያመጡልሽ ነበር፤ ገበያሽንም ረዓሙትና ቆርኮር መሉት። 17 ይሁዳና እስራኤል ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ ስንዴንም ይሸምቱልሽ ነበር፤ ሰሊሆትንና በለሶንን፥ ዘይትንና የተወደደ ማርን፥ ርጢንንም ከአንቺ ጋር አንድ ይሆኑ ዘንድ ሰጡሽ። 18 ከሥራሽ ብዛትና ከብልጽግናሽ ሁሉ ብዛት የተነሣ የደማስቆ ሰዎች ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ በኬልቦን የወይን ጠጅ፥ በነጭም የበግ ጠጕር ይነግዱ ነበር። 19 ዳንና ያዋን፤ ከኦሴል የተሠራ ብረትንና ብርጕድን፥ ቀረፋንም ያመጡልሽ ነበር። 20 ድዳን በተመረጡ እንስሳትና በሠረገላቸው፥ በክብር ልብስም ነጋዴሽ ነበረች። 21 ዓረብና የቄዳር አለቆች ሁሉ የእጅሽ ነጋዴዎች ነበሩ፤ በግመሎችና በአውራ በጎች፥ በፍየሎችም በእነዚህ ከአንቺ ጋር ይነግዱ ነበር። 22 የሳባና የራዕማ ነጋዴዎች እነዚህ ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ ንግድሽን በጥሩ ሽቱና በከበረ ድንጋይ ሁሉ፥ በወርቅም አደረጉ። 23 የካራንና የካኔ፥ የኤደንም ሰዎች ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ አሦርና ኪልማድም ነጋዴዎችሽ ነበሩ። 24 እነዚህ በአማረ ልብስ፥ በሰማያዊ ካባ፥ በወርቀ ዘቦም፥ በዝግባ በተሠራች፥ በገመድም በታሰረች፥ በግምጃም በተሞላች ሣጥን በገበያሽ ይነግዱ ነበር። 25 የተርሴስ መርከቦች ሸቀጥሽን የሚሸከሙ ነበሩ፤ አንቺም ተሞልተሽ ነበር፤ በባሕርም ውስጥ እጅግ ከበርሽ። 26 “ቀዛፊዎችሽ ወደ ትልቁ ውኃ አመጡሽ፤ የምሥራቅ ነፋስ በባሕር ውስጥ ሰበረሽ። 27 ኀይልሽና ዋጋሽ፥ ንግድሽም፥ መርከበኞችሽም፥ መርከብ መሪዎችሽም፥ ሰባራሽን የሚጠግኑ ነጋዴዎችሽም፥ በአንቺም ዘንድ ያሉ ሰልፈኞችሽ ሁሉ በውስጥሽ ከአሉት ጉባኤ ሁሉ ጋር በወደቅሽበት ቀን በባሕር ውስጥ ይጠፋሉ። 28 ከጩኸትሽ የተነሣ የመርከብሽ መሪዎች ፍርሀትን ፈሩ። 29 ቀዛፊዎችም ሁሉ፥ በመርከብ የተጫኑትም መርከብ መሪዎችም ሁሉ ከመርከቦቻቸው ይወርዳሉ፤ በየብስም ላይ ይቆማሉ፤ 30 ድምፃቸውንም በአንቺ ላይ ያሰማሉ፤ ምርር ብለውም ይጮኻሉ፤ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ይነሰንሳሉ፤ አመድም ያነጥፋሉ። 31 ስለ አንቺም የራሳቸውን ጠጕር ይላጫሉ፤ ማቅም ያሸርጣሉ፤ በነፍስም ምሬት ስለ አንቺ መራራ ልቅሶን ያለቅሳሉ። 32 ልጆቻቸውም ሙሾን ያሞሹልሻል፤ በባሕር መካከል እንደ ታወከች እንደ ጢሮስ ያለ ማን ነበር? ይላሉ። 33 በባሕር ውስጥ ምን ያህል ዋጋ ታገኚ ነበር? በብልጥግናሽ ብዛት ብዙ አሕዛብን አጠገብሽ፤ ከአንቺም ጋር አንድ ከሆኑት ለይተሽ የምድርን ነገሥታት ሁሉ ባለጸጎች አደረግሻቸው። 34 አሁን ግን በጥልቅ ውኃ ውስጥ በባሕር ተሰብረሻል፤ ከአንቺ ጋር አንድ የሆኑ ሁሉ በመካከልሽ ወድቀዋል። ቀዛፊዎችሽም ሁሉ ይወድቃሉ፤ 35 በደሴቶች የሚኖሩ ሁሉ አለቀሱልሽ፤ ነገሥታቶቻቸውም እጅግ ፈርተዋል ፊታቸውንም ነጭተው አለቀሱ። 36 የአሕዛብ ነጋዴዎችም አፍዋጩብሽ፤ አንቺም ፈጽመሽ ትጠፊያለሽ፤ ከእግዲህም ወዲያ እስከ ዘለዓለም አትኖሪም።” |