ሕዝቅኤል 26 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በጢሮስ ላይ የተነገረ ትንቢት 1 እንዲህም ሆነ፤ በዐሥራ አንደኛው ዓመት ከወሩ በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ፥ ጢሮስ በኢየሩሳሌም ላይ፦ እሰይ፥ ተሰበረች፥ ጠፋችም፥ ሕዝቧም ወደ እርስዋ ተመለሱ፤ ሞልታ የነበረች አለቀች ብላለችና፤ 3 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጢሮስ ሆይ! እነሆ በአንቺ ላይ ነኝ፤ ባሕርም ሞገድዋን እንደምታወጣ እንዲሁ ብዙ አሕዛብን አወጣብሻለሁ። 4 የጢሮስንም ቅጥሮች ያፈርሳሉ፤ ግንቦችዋንም ያፈርሳሉ፤ ትቢያዋንም ከእርስዋ እፍቃለሁ፤ እንደ ተራቈተ ድንጋይም አደርጋታለሁ። 5 በባሕር ውስጥ የመረብ ማስጫ ትሆናለች፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥” ይላል እግዚአብሔር፤ ለአሕዛብም ብዝበዛ ትሆናለች። 6 በሜዳ ያሉትም ሴቶች ልጆችዋ በሰይፍ ይገደላሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 7 “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ጢሮስ ሆይ! እነሆ ከሰሜን የነገሥታት ንጉሥ የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን ከፈረሶችና ከሰረገሎች፥ ከፈረሰኞችም፥ ከጉባኤና ከብዙ ሕዝብም ጋር በአንቺ ላይ አመጣለሁ። 8 እርሱ በምድረ በዳ ያሉ ሴቶች ልጆችሽን በሰይፍ ይገድላቸዋል፤ ጠባቂዎችንም በአንቺ ላይ ያስቀምጣል፤ በዙሪያሽም ግንብ ይሠራል፤ የጦር መሣሪያም ይዘው ይከቡሻል፤ በጦራቸውም ይወጉሻል፤ 9 ግንቦችሽንና ቅጥርሽን በምሳር ያፈርሳል። 10 ከፈረሶቹም ብዛት የተነሣ በትቢያ ይሸፍንሻል፤ ከሠረገላ መንኰራኵርና ከፈረሶቹ ድምፅ የተነሣም ቅጥሮችሽን ያፈርሳል፤ ወንበዴ መሣሪያውን ይዞ ወደ ምድረ በዳ ቦታ እንዲገባ በሮችሽን ይገቡባቸዋል። 11 ፈረሶቹ አደባባይሽን ይረግጣሉ፤ ሠራዊቶችሽንም በሾተል ይገድሏቸዋል፤ የጸና አርበኛሽንም በምድር ላይ ይጥለዋል። 12 ገንዘብሽን ይበረብራሉ፤ መንጋሽንም ይዘርፋሉ፤ አምባሽንም ይንዳሉ፤ የተወደዱ ቤቶችሽንም ያፈርሳሉ፤ እንጨቶችሽንና ድንጋይሽን፥ መሬትሽንም በባሕሩ ጥልቅ ውስጥ ይጥሉታል። 13 የዘፋኞችሽንም ብዛት ዝም አሰኛለሁ፤ የመሰንቆሽም ድምፅ ከዚያ ወዲያ አይሰማም። 14 እንደ ተራቈተ ድንጋይ አደርግሻለሁ፤ የመረብም ማስጫ ትሆኛለሽ፤ ከእንግዲህ ወዲህ አትሠሪም፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁና፥” ይላል እግዚአብሔር። 15 “ስለ ጢሮስ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሾተላቸውን በመካከልሽ በመዘዙ ጊዜ ከውድቀትሽ፥ ከቈሰሉትም ጩኸት የተነሣ፤ ደሴቶች የሚነዋወጡ አይደለምን? 16 የባሕርም አለቆች ሁሉ ከዙፋኖቻቸው ይወርዳሉ፤ ዘውዳቸውን ከራሳቸው ያወርዳሉ፤ ወርቀ ዘቦ ልብሳቸውን ያወልቃሉ፤ በመሬትም ላይ ተቀምጠው ይደነግጣሉ፤ ሞታቸውንም ይፈራሉ፤ ስለ አንቺም ያለቅሳሉ። 17 በአንቺም ላይ ሙሾ ያሞሻሉ፤ እንዲህም ይሉሻል፦ በባሕር የተቀመጥሽ፥ በባሕርም ውስጥ የጸናሽ፥ ከሚቀመጡብሽም ጋር በዙሪያሽ የሚኖሩትን ሁሉ ያስፈራሽ፥ የከበርሽ ከተማ ሆይ! እንዴት ጠፋሽ! 18 አሁን በውድቅትሽ ቀን ደሴቶች ይፈራሉ፥ በባሕርም ውስጥ ያሉ ደሴቶች ከመውጣትሽ የተነሣ ይደነግጣሉ። 19 “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ሰው እንደሌለባቸው ከተሞች ባድማ ከተማ ባደረግሁሽ ጊዜ፥ ቀላዩንም ባወጣሁብሽ ጊዜ፥ ብዙ ውኆችም በከደኑሽ ጊዜ፥ 20 ወደ ጥልቁ ከሚወርዱት ጋር ወደ ቀደሙት ሕዝብ አወርድሻለሁ። በምድርም ላይ በሕይወትሽ ጸንተሽ እንዳትኖሪም ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱ ሰዎች ጋር ቀድሞ በፈረሰው ቤት ከምድር በታች አኖርሻለሁ። 21 ለሞት እሰጥሻለሁ፤ ከእንግዲህም አትኖሪም፤ ይፈልጉሻል፥ ለዘለዓለምም አያገኙሽም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።” |