ሕዝቅኤል 24 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የዛገች ድስት ምሳሌ 1 በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር ከወሩም በዐሥረኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ! የዚህን ቀን፥ የዛሬን ቀን ስም ጻፍ፤ በዚህ ቀን የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣልና። 3 ለዐመፀኛውም ቤት ምሳሌን ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጣድ፥ ድስቲቱን ጣድ፥ ውኃም ጨምርባት። 4 ቍራጭዋንም፥ መልካሙን ቍራጭ ሁሉ፥ ጭኑንና ወርቹን በእርስዋ ውስጥ ጨምር፤ የተመረጡትንም አጥንቶች ሙላባት። 5 ከመንጋው የተመረጠውን ውሰድ፤ አጥንቶቹም እንዲበስሉ በበታችዋ እሳት አንድድ፤ አፍላው፤ በእጅጉ ይፍላ፤ አጥንቶቹም በውስጥዋ ይቀቀሉ። 6 “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ዝገቷ ላለባት፥ ዝገቷም ከእርስዋ ላልወጣ ድስት፥ ለደም ከተማ ወዮላት! ቍራጭ ቍራጩን አውጣ፤ ዕጣ አልወደቀባትም። 7 ደምዋም በመካከልዋ አለ። በተራቈተ ድንጋይ ላይ አደረገችው እንጂ በአፈር ይከደን ዘንድ በመሬት ላይ አላፈሰሰችውም። 8 መዓቴን አወጣ ዘንድ፥ በቀሌንም እበቀል ዘንድ፥ ደምዋ እንዳይከደን በተራቈተ ድንጋይ ላይ አደረግሁ። 9 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለደም ከተማ ወዮላት! እኔ ደግሞ ማገዶዋን ታላቅ አደርገዋለሁ። 10 ደሟ እስኪያልቅ ድረስ ሥጋዋ ያርር ዘንድ፥ አጥንቶችዋም ይቀጠቀጡ ዘንድ፤ እንጨቱን አበዛለሁ፤ እሳቱንም አነድዳለሁ፥ 11 ድስቷም እስክትፈላና እስክትሰበር ድረስ በፍሙ ላይ አኖራታለሁ፤ ርኵሰትዋም በመካከሏ እንደ ሰም ይቀልጣል፤ ዝገትዋም ይጠፋል፤ 12 በከንቱ ደከመች፤ ሆኖም ብዙ ዝገቷ ከእርስዋ አልለቀቀም። 13 በርኵሰትሽ ሴሰኝነት አለ፤ አነጻሁሽ፤ አልነጻሽምና መዓቴን በላይሽ እስክጨርስ ድረስ እንግዲህ ከርኵሰትሽ አትነጺም። 14 እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ እመጣለሁ፤ እኔም አደርገዋለሁ፤ አልተውም፤ አልራራም፤ አልጸጸትም፤ እንደ መንገድሽና እንደ ሥራሽም እፈርድብሻለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ስለዚህ የሰውን ደም እንደ አፈሰስሽ እኔ እፈርድብሻለሁ፤ እንደ ኀጢአትሽም ተበቅዬ አጠፋሻለሁ፤ ስምሽም ጐሰቈለ፥ ብዙ ኀዘንንም ታዝኛለሽ።” የነቢዩ ሚስት መሞት 15 የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 16 “የሰው ልጅ ሆይ! እነሆ የዐይንህን አምሮት በመቅሠፍት እወስድብሃለሁ፤ አንተም ዋይ አትበል፤ አታልቅስም፤ እንባህንም አታፍስስ። 17 በቀስታ ተክዝ፤ ነገር ግን የሙታንን ልቅሶ አታልቅስ፤ መጠምጠሚያህን በራስህ ላይ አድርግ፤ ጫማህንም በእግርህ አጥልቅ፤ ከንፈሮችህንም አትሸፍን፤ የዕዝን እንጀራንም አትብላ።” 18 እኔም በማለዳ ለሕዝቡ ተናገርሁ፤ ወደ ማታም ሚስቴ ሞተች፤ በነጋውም እንደ ታዘዝሁ አደረግሁ። 19 ሕዝቡም፥ “ይህ የምታደርገው ነገር ለእኛ ምን እንደ ሆነ አትነግረንምን?” አሉኝ። 20 እኔም እንዲህ አልኋቸው፥ “የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 21 ለእስራኤል ቤት ተናገር፤ እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ የኀይላችሁን ትምክሕት፥ የዐይናችሁን አምሮት፥ የነፍሳችሁንም ምኞት፥ መቅደሴን አረክሳለሁ፤ ያስቀራችኋቸውም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። 22 እኔም እንዳደረግሁ እናንተ ታደርጋላችሁ፤ በአንደበታቸው አትጽናኑም፤ የዕዝን እንጀራንም አትበሉም። 23 መጠምጠሚያችሁም በራሳችሁ፥ ጫማችሁም በእግራችሁ ይሆናል፤ ዋይ አትሉም፤ አታለቅሱምም፤ በኀጢአታችሁም ትሰለስላላችሁ፤ ሁላችሁም ጓደኞቻችሁን ታጽናናላችሁ። 24 ሕዝቅኤልም ምልክት ይሆናችኋል፤ እርሱ እንደ አደረገ ሁሉ እናንተ ታደርጋላችሁ፤ ይህም በመጣ ጊዜ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 25 “አንተም የሰው ልጅ ሆይ! ኀይላቸውን፥ የተመኩበትንም ደስታ፥ የዐይናቸውንም አምሮት፥ የነፍሳቸውንም ምኞት፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በወሰድሁባቸው ቀን፥ 26 በዚያ ቀን ያመለጠው ይህን ነገር በጆሮህ ያሰማ ዘንድ ወደ አንተ ይመጣል። 27 በዚያ ቀን አፍህ ላመለጠው ይከፈታል፤ አንተም ትናገራለህ፤ ከዚያም ወዲያ ዲዳ አትሆንም፤ ምልክትም ትሆናቸዋለህ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” |