ሕዝቅኤል 22 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኢየሩሳሌም ሕዝብ ኀጢአት 1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 “አንተም የሰው ልጅ ሆይ! ደም በምታፈስስ ከተማ ላይ ትፈርዳለህን? ርኵሰቷን ሁሉ አስታውቃት። 3 እንዲህም በላት፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጊዜሽ እንዲደርስ በመካከልሽ ደምን የምታፈስሺ፥ እንድትረክሺም በራስሽ ላይ ጣዖታትን የምታደርጊ ከተማ ሆይ! 4 ባፈሰስሽው ደም በድለሻል፤ ባደረግሻቸውም ጣዖታት ረክሰሻል፤ ቀንሽንም አቀረብሽ፤ ዘመንሽንም አሳጠርሽ፤ ስለዚህ ለአሕዛብ መሰደቢያ፥ ለሀገሮችም ሁሉ መሳለቂያ አደረግሁሽ። 5 አንቺ ስምሽ የረከሰ፥ ኀጢአትም የሞላብሽ ሆይ! ወደ አንቺ የቀረቡና ከአንቺ የራቁ ይሳለቁብሻል። 6 “እነሆ የእስራኤል ቤት አለቆች እያንዳንዳቸው ከዘመዶቻቸው ጋር ደም ያፈስሱ ዘንድ በአንቺ ውስጥ ተባበሩ። 7 በአንቺ ውስጥ አባትንና እናትን አቃለሉ፤ በመካከልሽ በመጻተኛው ላይ በደልን አደረጉ፤ በአንቺ ውስጥ ድሀ አደጉንና መበለቲቱን አስጨነቁ። 8 ቅድሳቴንም ናቁ፤ ሰንበታቴንም አረከሱ። 9 በውስጥሽ ደምን ያፈስሱ ዘንድ ሌቦች ሰዎች በአንቺ ውስጥ ነበሩ፤ በአንቺ ውስጥ በተራሮች ላይ በሉ፤ በመካከልሽም የማይገባ ነገርን አደረጉ። 10 በአንቺ ውስጥ የአባቶቻቸውን ኀፍረተ ሥጋ ገለጡ፤ በአንቺም ውስጥ አደፍ ያለባትን አዋረዱ። 11 ሰውም ከባልንጀራው ሚስት ጋር ሰሰነ፤ አባትም የልጁን ሚስት በኀጢአት አረከሰ፤ በአንቺም ዘንድ ወንድም የአባቱን ልጅ እኅቱን አስነወረ። 12 በአንቺ ውስጥ ደምን ያፈስሱ ዘንድ መማለጃን ተቀበሉ፤ በአንቺም አራጣና ትርፍ ወስደዋል፤ ቀማኛነትሽንና ኀጢአትሽን ፈጸምሽ፤ እኔንም ረሳሽኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 13 “ስለዚህ እነሆ አንቺ ባደረግሽው ሥራ፥ በመካከልሽም በነበረው ደም ላይ በእጄ አጨበጨብሁ። 14 እኔ በማደርግብሽ ወራት ልብሽ ይታገሣልን? ወይስ እጆችሽ ይጸናሉን? እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ አደርገውማለሁ። 15 ወደ አሕዛብም እበትንሻለሁ፤ በሀገሮችም እዘራሻለሁ፤ ከአንቺም ርኵሰትሽ ይጠፋል። 16 በአሕዛብም ፊት ከአንቺ እወርሳለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” 17 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 18 “የሰው ልጅ ሆይ! የእስራኤል ቤት ሁሉ የተቀላቀሉ ናስና ቆርቆሮ፥ ብረትና እርሳስ ሆኑብኝ፤ በማጣሪያም መካከል የተቀላቀለ ብር ሆኑ። 19 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሁላችሁ አተላ ሆናችኋልና ስለዚህ እነሆ በኢየሩሳሌም ውስጥ እሰበስባችኋለሁ። 20 እንዲያቀልጡት እሳት ያናፉበት ዘንድ ብርንና መዳብን፥ ብረትንና እርሳስን፥ ቆርቆሮንም በከውር እንደሚሰበስቡ፥ እንዲሁ በቍጣዬና በመዓቴ እሰበስባችኋለሁ፤ በዚያም ውስጥ እጨምራችኋለሁ፤ አቀልጣችሁማለሁ። 21 በላያችሁ የመዓቴን እሳት አነድድባችኋለሁ፤ በመካከሉም ትቀልጣላችሁ። 22 ብርም በከውር ውስጥ እንደሚቀልጥ፥ እንዲሁ በውስጥዋ ትቀልጣላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር መዓቴን እንዳፈሰስሁባችሁ ታውቃላችሁ።” የእስራኤል መሪዎች በደል 23 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 24 “የሰው ልጅ ሆይ! አንቺ ዝናም የማይዘንብብሽ፥ በቍጣ ቀን ጠል የማይወርድብሽ ምድር ነሽ በላት። 25 በመካከሏ ያሉ ነቢያት እንደ አንበሳ ያገሳሉ፤ ይነጥቃሉ፤ ፈጽመውም ይቀማሉ፤ ሰውነትንም ያጠፋሉ፤ መማለጃንም ይቀበላሉ፤ በመካከልዋም መበለቶችዋ ይበዛሉ። 26 ካህናቷም ሕጌን ጣሱ፤ በመቅደሴም መካከል ቅድሳቴን አረከሱ፤ ከርኵሰትም አልራቁም፤ በንጹሕና በርኩስ መካከል ያለውንም ልዩነት አላወቁም፤ ዐይናቸውንም ከሰንበታቴ ሸፈኑ፤ እኔም በመካከላቸው ረከስሁ። 27 በውስጥዋ ያሉ አለቆችዋ የስስትን ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ደምን ያፈስሱ ዘንድ፥ ነፍሶችንም ያጠፉ ዘንድ እንደሚናጠቁ ተኵላዎች ናቸው። 28 ነቢያቶቻቸውም ይቀቡአቸዋል፤ ከንቱ ነገርንም ያዩላቸዋል፤ እግዚአብሔር እንዲህ አለ እያሉም በሐሰት ያምዋርቱላቸዋል፤ እግዚአብሔር ግን አልነገራቸውም። 29 የምድር ሕዝብ ግፍን አደረጉ፤ ቅሚያንም ሠሩ፤ ድሆችንና ችግረኞችን አስጨነቁ፤ ለመጻተኛውም አልፈረዱለትም። 30 ቅጥርን የሚጠግንን፥ ምድሪቱንም እንዳላጠፋት በፈረሰበት በኩል በፊቴ የሚቆምላትን ሰው ከእነርሱ መካከል ፈለግሁ፤ ነገር ግን አላገኘሁም። 31 ስለዚህ ቍጣዬን አፈሰስሁባቸው፤ በመዓቴም እሳት አጠፋኋቸው፤ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ መለስሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።” |