ሕዝቅኤል 21 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በባቢሎን የእግዚአብሔር ሰይፍ 1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ! ስለዚህ ትንቢት ተናገር፤ ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም አቅና፤ ወደ መቅደሶችም ተመልከት፤ በእስራኤልም ምድር ላይ ትንቢት ተናገር። 3 ለእስራኤልም ምድር እንዲህ በል፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ በአንቺ ላይ ነኝ፤ ሰይፌንም ከሰገባው እመዝዘዋለሁ፤ ጻድቁንና ኃጥኡን ከአንቺ ዘንድ አጠፋለሁ። 4 እኔም ጻድቁንና ኃጥኡን ከአንቺ ዘንድ ስለማጠፋ፥ ስለዚህ ሰይፌ ከደቡብ ጀምሮ እስከ ሰሜን ድረስ በአለ በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ከሰገባው ይመዘዛል። 5 ሥጋ ለባሹም ሁሉ እኔ እግዚአብሔር ሰይፌን ከሰገባው እንደ መዘዝሁ ያውቃል፤ እርሱም ደግሞ አይመለስም። 6 ስለዚህ አንተ የሰው ልጅ ሆይ! ወገብህን በማጕበጥ አልቅስ፤ በፊታቸውም ምርር ብለህ አልቅስ። 7 እነርሱም፦ ስለ ምን ታለቅሳለህ? ቢሉህ አንተ እንዲህ በላቸው፦ ስለሚመጣው ወሬ ነው፤ ልብም ሁሉ ይቀልጣል፤ እጆችም ሁሉ ይዝላሉ፤ ሥጋና መንፈስ ሁሉ ይደክማል፤ ከጕልበትም እዥ ይፈስሳል፤ እነሆ ይመጣል፤ ይፈጸማልም፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 8 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 9 “የሰው ልጅ ሆይ! እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ትንቢት ተናገር፤ ሰይፍ ሰይፍ የተሳለች፥ የተሰነገለችም ሁኚ። 10 ወግተሽ ትገድሊ ዘንድ፥ ታብረቀርቂም ዘንድ ተሳዪ፤ ትገድሊም ዘንድ፥ ዕንጨቱንም ሁሉ ትጥዪ ዘንድ ጨክኚ፤ 11 በእጁም ይይዛት ዘንድ ለአርበኛ ተሰጠች፤ ሰይፍ በገዳይ እጅ እንድትሰጥ ተሳለችና ተዘጋጀች። 12 የሰው ልጅ ሆይ! በሕዝቤ ላይ ነውና፥ በእስራኤልም አለቆች ሁሉ ላይ ነውና ጩኽ፤ ዋይም በል፤ እነርሱ ከሕዝቤ ጋር ለሰይፍ ተሰጥተዋል፤ ስለዚህ እጅህን ጽፋ። 13 እውነት ሆኖአልና፤ የራቁ ሕዝቤ ምን ሆኑ? የሉምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 14 ስለዚህ አንተ የሰው ልጅ ሆይ! ትንቢት ተናገር፤ እጅህን በእጅህ ላይ አጨብጭብ፤ የተገደሉ ሰዎች ሰይፍ ሦስት ጊዜ ይደጋግም፤ ይኸውም የታላቅ ግድያ ሰይፍ ነው፤ ያስደነግጣቸዋልም። 15 ልባቸው እንዲቀልጥ፥ መሰናክላቸውም እንዲበዛ የሚገድለውን ሰይፍ በበሮቻቸው ሁሉ ላይ አድርጌአለሁ፤ ወዮ! ያብረቀርቅ ዘንድ ተሰንግሏል፤ ይገድልም ዘንድ ተስሏል። 16 ፊትህ ወደ አቀናው ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ሂድ። 17 እኔ ደግሞ እጄን በእጄ ላይ አጨበጭባለሁ፤ መዓቴንም እልካለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።” 18 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 19 “አንተም የሰው ልጅ ሆይ! የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ የምትገባባቸው ሁለት መንገዶችን አድርግ፤ ሁለቱም ከአንዲት ምድር ይውጡ፤ ምልክትንም አድርግ፤ በከተማዪቱ መንገድ ራስ ላይም አድርገው። 20 ሰይፍ ወደ አሞን ልጆች ሀገር፥ ወደ ራባት፥ ወደ ይሁዳም፥ ወደ ኢየሩሳሌምም፥ በመካከልዋ ይገባ ዘንድ መንገድን አድርግ። 21 የባቢሎን ንጉሥ ምዋርቱን ያምዋርት ዘንድ፥ በትሩን ያነሣ ዘንድ፥ ጣዖቱንም ይጠይቅ ዘንድ በሁለት መንገዶች ራስ ላይ ይቆማል። 22 የቅጥሩን ማፍረሻ ያደርግ ዘንድ፥ አፍንም በጩኸት ይከፍት ዘንድ፥ በውካታም ድምፅን ከፍ ያደርግ ዘንድ፥ የቅጥሩን ማፍረሻ በበሮች ላይ ያደርግ ዘንድ፥ አፈርን ይደለድል ዘንድ፥ ምሽግም ይሠራ ዘንድ የኢየሩሳሌም ምዋርት በቀኝ እጁ ውስጥ ነበረ። 23 እርሱ በፊታቸው ምዋርትን ያምዋርታል፤ ኀጢአታቸውንም ዐስቦ ሰባት ሱባዔ ይቈጥርባቸዋል። 24 “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ኀጢአታችሁን ስለ ዐሰባችሁ፥ መተላለፋችሁም ስለ ተገለጠ፥ ኀጢአታችሁም በሥራችሁ ሁሉ ስለ ታየ፥ እናንተም ስለ ታሰባችሁ፥ በእርሱ ትያዛላችሁ። 25 አንተም ቀንህና የኀጢአትህ ቀጠሮ ጊዜ የደረሰብህ፥ ርኩስ ኀጢአተኛ የእስራኤል አለቃ ሆይ! 26 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ መጠምጠሚያውን አውልቅ፤ ዘውዱንም አርቅ፤ ይህ እንዲህ አይሆንም፤ የተዋረደውን ከፍ አድርግ፤ ከፍ ያለውንም አዋርድ። 27 ባድማ፥ ባድማ፥ ባድማ አደርጋታለሁ፤ ፍርድ ያለው እስኪመጣ ድረስ ይህች ደግሞ አትሆንም፤ ለእርሱም እሰጣታለሁ፤ 28 “አንተም የሰው ልጅ ሆይ! ጌታ እግዚአብሔር ስለ አሞን ልጆችና ስለ ስድባቸው እንዲህ ይላል ብለህ ትንቢት ተናገር፤ ሰይፍ ሰይፍ ለመግደል ተመዝዞአል፤ ጨርሶም ያርድ ዘንድ ተሰንግሎአል በል። 29 በተገደሉት ኀጢአተኞች አንገት ላይ ያኖሩህ ዘንድ ከንቱ ራእይን ሲያዩልህ፥ በሐሰት ምዋርትም ሲናገሩልህ፥ በኀጢአታቸው ቀጠሮ ጊዜ ቀናቸው ደረሰ። 30 ወደ ሰገባውም መልሰው፤ በተፈጠርህባት ስፍራ አትደር፤ በተወለድህባትም ምድር እፈርድብሃለሁ። 31 ቍጣዬንም አፈስስብሃለሁ፤ በመዓቴም እሳት አናፋብሃለሁ፤ ማጥፋትንም ለሚያውቁ ለጨካኞች ሰዎች እጅ አሳልፌ እሰጥሃለሁ። 32 ለእሳት ማገዶ ትሆናለህ፤ ደምህም በምድር መካከል ይፈስሳል፤ ደግሞም አትታሰብም፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁና።” |