ሕዝቅኤል 20 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእስራኤል እንቢተኛነት 1 እንዲህም ሆነ፥ በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በዐሥረኛው ቀን እግዚአብሔርን ይጠይቁ ዘንድ ከእስራኤል ሽማግሌዎች ሰዎች መጡ፤ በፊቴም ተቀመጡ። 2 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 3 “የሰው ልጅ ሆይ! ለእስራኤል ሽማግሌዎች ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔን ትጠይቁ ዘንድ መጥታችኋልን? እኔ ሕያው ነኝ! አልመልስላችሁም፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 4 ነገር ግን በቀልን እበቀላቸዋለሁ፤ የሰው ልጅ ሆይ! የአባቶቻቸውን ኀጢአት አስታውቃቸው። 5 እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤልን ቤት በመረጥሁበት፥ ለያዕቆብም ቤት ዘር በታወቅሁበት ቀን፥ በግብፅም ምድር በተገለጥሁላቸው ጊዜ እጄን አንሥቼ፦ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ አልኋቸው። 6 በዚያ ቀን ከግብፅ ምድር ወዳዘጋጀሁላቸው፥ ወተትና ማር ወደምታፈስሰው፥ ከምድር ሁሉ ወደምትበልጥ ምድር አወጣቸው ዘንድ እጄን አነሣሁ። 7 እኔም፦ ከእናንተ እያንዳንዱ ርኵሰቱን ከፊቱ ያስወግድ፤ በግብፅም ጣዖታት አትርከሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ አልኋቸው። 8 እነርሱ ግን ዐመፁብኝ፤ ይሰሙኝም ዘንድ አልወደዱም፤ ሁሉም እያንዳንዱ ርኵሰቱን ከፊቱ አላስወገደም፤ የግብጽንም ጣዖታት አልተወም፤ በዚህም ጊዜ በግብፅ ምድር መካከል ቍጣዬን እፈጽምባቸው ዘንድ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ አልሁ። 9 ነገር ግን በመካከላቸው በአሉ፥ ከግብጽም ምድር አወጣቸው ዘንድ በፊታቸው በተገለጥሁላቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ። 10 “ከግብፅም ምድር አወጣኋቸው ወደ ምድረ በዳም አመጣኋቸው። 11 ሰው ቢያደርገው በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴንም ሰጠኋቸው፤ ፍርዴንም አስታወቅኋቸው። 12 የምቀድሳቸውም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቁ ዘንድ፥ በእኔና በእነርሱ መካከል ምልክት ይሆኑ ዘንድ ሰንበታቴን ሰጠኋቸው። 13 ነገር ግን የእስራኤልን ቤት በምድረ በዳ በትእዛዜ ሂዱ አልኋቸው፤ አልሄዱምም፤ ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትንም ሕጌን አፈረሱ፤ ሰንበታቴንም ፈጽመው አረከሱ። በዚህም ጊዜ አጠፋቸው ዘንድ ቍጣዬን በምድረ በዳ አፈስስባቸዋለሁ አልሁ። 14 ነገር ግን በፊታቸው ባወጣኋቸው በአሕዛብ ፊት ከሁሉ በላይ የሚሆን ስሜን እንዳያረክሱ አደረግሁ። 15 ወተትና ማርም ወደምታፈስሰው ከምድር ሁሉ ወደምታምር ወደ ሰጠኋቸው ምድር እንዳላገባቸው በምድረ በዳ በእነርሱ ላይ ፈጽሜ እጄን አነሣሁ። 16 ፍርዴንም ጥሰዋልና፥ በሥርዐቴም አልሄዱምና፥ ሰንበታቴንም አርክሰዋልና በልባቸው ዐሳብ ሄዱ። 17 ነገር ግን እኔ እንደ አላጠፋቸው፥ በምድረ በዳም ፈጽሜ እንደ አልጨርሳቸው ዐይኔ ራራችላቸው። 18 “ለልጆቻቸውም በምድረ በዳ እንዲህ አልኋቸው፦ በአባቶቻችሁ ልማድ አትሂዱ፤ ሥርዐታቸውንም አትጠብቁ፤ በበደላቸውም አንድ አትሁኑ፤ አትርከሱም። 19 እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ በትእዛዜ ሂዱ፤ ፍርዴንም ጠብቁ፤ አድርጓትም። 20 ሰንበታቴንም ቀድሱ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ በእኔና በእናንተ መካከል ምልክት ይሁኑ። 21 ልጆቻቸው ግን አማረሩኝ፤ ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትን ፍርዴን ጠብቀው አላደረጉትም፤ በሥርዐቴም አልሄዱም፤ ሰንበታቴንም አረከሱ፤ በዚህም ጊዜ፦ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ፤ ቍጣዬንም በምድረ በዳ እፈጽምባቸዋለሁ አልሁ። 22 ነገር ግን በፊታቸው ባወጣኋቸው በአሕዛብ ፊት ከሁሉ የሚበልጠው ስሜ እንዳይረክስ አደረግሁ። 23 ደግሞም ወደ አሕዛብ እበትናቸው ዘንድ፥ በሀገሮችም እበትናቸው ዘንድ በምድረ በዳ በእነርሱ ላይ እጄን አነሣሁ። 24 ፍርዴን አላደረጉምና፥ ሥርዐቴንም ጥሰዋልና፥ ሰንበታቴንም አርክሰዋልና፥ ዐይኖቻቸውም የአባቶቻቸውን ዐሳብ ተከትለዋልና። 25 ደግሞም መልካም ያልሆነውን ሥርዐት፥ በሕይወት የማይኖሩበትንም ፍርድ ሰጠኋቸው። 26 እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ እንዲያውቁ አጠፋቸው ዘንድ ማኅፀን የሚከፍተውን ሁሉ በአመጡልኝ ጊዜ፥ በመባቸው አረከስኋቸው። 27 “ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ! ለእስራኤል ቤት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚህም ደግሞ አባቶቻችሁ በአደረጉት ዐመፅ አስቈጡኝ። 28 እሰጣቸውም ዘንድ እጄን ወደ አነሣሁላቸው ምድር አገባኋቸው፤ ከፍ ያለውን ኮረብታ ሁሉ፥ ቅጠላማውንም ዛፍ ሁሉ አዩ፤ በዚያም ለጣዖቶቻቸው መሥዋዕታቸውን ሠዉ፤ በዚያም የሚያስቈጣኝን፤ ቍርባናቸውን አቀረቡ፤ በዚያም ደግሞ ጣፋጩን ሽታቸውን አደረጉ፤ በዚያም የመጠጥ ቍርባናቸውን አፈሰሱ። 29 እኔም፦ እናንተ ወደ እርሱ የምትሄዱበት ከፍታ ምንድን ነው? አልኋቸው። እስከ ዛሬም ድረስ ስሙ ባማ ተብሎ ተጠርቶአል። 30 ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እናንተ በአባቶቻችሁ ኀጢአት ረከሳችሁ፤ አመነዘራችሁ፤ ርኵሰታቸውንም ተከተላችሁ። 31 ቍርባናችሁን በአቀረባችሁ ጊዜ፥ ልጆቻችሁንም በእሳት ባሳለፋችሁ ጊዜ፥ እስከ ዛሬ ድረስ በዐሳባችሁ ሁሉ ረከሳችሁ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ! እኔስ እመልስላችኋለሁን? እኔ ሕያው ነኝ! አልመልስላችሁም፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 32 ለእናንተም፦ እንደ አሕዛብና እንደ ምድር ወገኖች እንሆናለን፤ እንጨትና ድንጋይም እናመልካለን የሚል ከልባችሁ የወጣ ዐሳብ አይፈጸምላችሁም። የእግዚአብሔር ቅጣትና ምሕረት 33 “እኔ ሕያው ነኝ! በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ፥ በፈሰሰችም መዓት እነግሥባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 34 ከአሕዛብም ዘንድ አወጣችኋለሁ፤ ከተበተናችሁባትም ሀገር ሁሉ በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ፥ በፈሰሰችም መዓት እሰበስባችኋለሁ። 35 ወደ አሕዛብም ምድረ በዳ አመጣችኋለሁ፤ በዚያም ፊት ለፊት ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ። 36 በግብፅ ምድረ በዳ ከአባቶቻችሁ ጋር እንደ ተፋረድሁ እንዲሁ ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 37 ከበትሬም በታች አሳልፋችኋለሁ፤ በቍጥርም እወስዳችኋለሁ። 38 ከእናንተም ዘንድ ዐመፀኞችንና የበደሉኝን እለያለሁ፤ ከኖሩባትም ምድር አወጣቸዋለሁ፤ ወደ እስራኤል ምድር ግን አይገቡም፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 39 እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሁላችሁ ኀጢአታችሁን ተዉ፤ ከዚህ በኋላ ስሙኝ፤ ቅዱሱን ስሜንም ከእንግዲህ ወዲህ በኀጢአታችሁና በመባችሁ አታርክሱ። 40 “በቅዱሱ ተራራዬ፥ ከፍ ባለው በእስራኤል ተራራ ላይ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ በዚያ የእስራኤል ቤት ሁሉ ሁላቸው ለዘለዓለም ይገዙልኛል፤ በዚያም እቀበላችኋለሁ፤ በዚያም ቀዳምያታችሁን፥ በኵራታችሁንም፥ የቀደሳችሁትንም ነገር ሁሉ እጐበኛለሁ። 41 ከአሕዛብ ዘንድ ባወጣኋችሁ ጊዜ፥ ከተበተናችሁባትም ሀገር ሁሉ በሰበሰብኋችሁ ጊዜ እንደ ጣፋጭ ሽታ እቀበላችኋለሁ፤ በአሕዛብም ፊት እቀደስባችኋለሁ። 42 ለአባቶቻችሁም እሰጣት ዘንድ እጄን ወደ አነሣሁላቸው ምድር ወደ እስራኤል ሀገር ባገባኋችሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 43 በዚያም የረከሳችሁባትን መንገዳችሁንና ሥራችሁን ሁሉ ታስባላችሁ፤ በፊታችሁም አይታችሁ ስለ ሠራችሁት ክፋታችሁ ሁሉ ታፍራላችሁ። 44 የእስራኤል ቤት ሆይ! እንደ ክፉ መንገዳችሁና እንደ ርኩስ ሥራችሁ ሳይሆን ስለ ስሜ ስል በሠራሁላችሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 45 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤ 46 “የሰው ልጅ ሆይ! ፊትህን ወደ ቴማን አቅና፤ ወደ ዳሮምም ተመልከት፤ በናጌብም ምድረ በዳ ዱር ንጉሥ ላይ ትንቢት ተናገር። 47 ለናጌብም ዱር እንዲህ በለው፦ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ በአንተ ውስጥ እሳትን አነድዳለሁ፤ በውስጥህም ያለውን የለመለመውንና የደረቀውን ዛፍ ሁሉ ይበላል፤ የሚቃጠለውም ነበልባል አይጠፋም፤ ከደቡብም ጀምሮ እስከ ሰሜን ድረስ ፊት ሁሉ ይቃጠልበታል። 48 እኔም እግዚአብሔር እንዳነደድሁት ሥጋ ለባሽ ሁሉ ያያል፥ እርሱም አይጠፋም። 49 እኔም፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይህ አይሁን አልሁ፤ እነርሱ ግን፦ ይህ የነገረን ምሳሌ አይደለምን? ይሉኛል።” |