ሕዝቅኤል 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እግዚአብሔር ሕዝቅኤልን ለነቢይነት እንደ ጠራው 1 እርሱም፥ “የሰው ልጅ ሆይ! በእግርህ ቁም፤ እኔም እናገርሃለሁ” አለኝ። 2 በተናገረኝም ጊዜ መንፈስ በእኔ ላይ መጣ፤ አነሣኝም፤ በእግሬም አቆመኝ፤ የሚናገረኝንም ሰማሁ። 3 እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “የሰው ልጅ ሆይ! እኔን ወደ አስመረሩኝ ወደ እስራኤል ቤት እልክሃለሁ። እነርሱና አባቶቻቸው እስከ ዛሬ ድረስ ዐመፁብኝ። 4 እነርሱ ፊታቸው የከፋ፥ ልባቸው የደነደነ ልጆች ናቸው። እኔ ወደ እነርሱ እልክሃለሁ፤ አንተም፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በላቸው። 5 “እነርሱ ዐመፀኛ ቤት ናቸውና ቢሰሙ ወይም ቢፈሩ አንተ በመካከላቸው ነቢይ እንደ ሆንህ ያውቃሉ። 6 አንተ የሰው ልጅ ሆይ! ኩርንችትና እሾህ ከአንተ ጋር ቢኖሩም፥ አንተም በጊንጦች መካከል ብትቀመጥ፥ አትፍራቸው፤ ቃላቸውንም አትፍራ፤ አንተ ቃላቸውን አትፍራ፤ ከፊታቸውም የተነሣ አትደንግጥ፤ እነርሱ ዐመፀኛ ቤት ናቸውና። 7 እነርሱ ዐመፀኛ ቤት ስለሆኑ ቢሰሙ ወይም ቢደነግጡ ቃሌን ትነግራቸዋለህ። 8 “አንተ የሰው ልጅ ሆይ! የምነግርህን ስማ፤ እንደእዚያ ዐመፀኛ ቤት ዐመፀኛ አትሁን፤ አፍህን ክፈት፤ የምሰጥህንም ብላ።” 9 በአየሁም ጊዜ፥ እነሆ እጅ ወደ እኔ ተዘርግታ ነበር፤ እነሆም የመጽሐፍ ጥቅልል ነበረባት። 10 በፊቴም ዘረጋው፤ በውስጥና በውጭም ተጽፎበት ነበረ፤ ጽሑፉም “ልቅሶና ኀዘን፥ ዋይታም” ይል ነበር። |