ሕዝቅኤል 19 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኀዘን መዝሙር 1 “አንተም ለእስራኤል አለቃ ይህን ሙሾ አሙሽለት፤ 2 እንዲህም በል፦ እናትህ ምን ነበረች? እንስት አንበሳ ነበረች፤ በአንበሶች መካከል ተጋደመች፤ በደቦል አንበሶችም መካከል ግልገሎችዋን አሳደገች። 3 ከግልገሎችዋም አንዱን አወጣች፤ እርሱም ደቦል አንበሳ ሆነ፤ ንጥቂያንም ተማረ፤ ሰዎችንም ነጥቆ በላ። 4 አሕዛብም ስለ እርሱ ሰሙ፤ እርሱም በጕድጓዳቸው ተያዘ፤ በሰንሰለትም አስረው ወደ ግብፅ ምድር ወሰዱት። 5 እርስዋም ከእርስዋ እንደ ወሰዱት ባየች ጊዜ ኀይልዋ ጠፋ፤ ከግልገሎችዋም ሌላን ወስዳ ደቦል አንበሳ አደረገችው። 6 እርሱም በአንበሶች መካከል አደገ፤ ደቦል አንበሳም ሆነ፤ ንጥቂያም ተማረ፤ ሰዎችንም ነጥቆ በላ። 7 ተዘልሎም ይኖራል፤ ከተሞቻቸውንም አጠፋ፤ ሀገራቸውንም አፈረሰ፤ ከግሣቱም ድምፅ የተነሣ ምድርና ሞላዋ ጠፋች። 8 አሕዛብም በዙሪያው ከየሀገሩ ሁሉ ተሰበሰቡበት፤ መረባቸውንም በእርሱ ላይ ዘረጉ፤ በወጥመዳቸውም ተያዘ። 9 በሰንሰለትም አስረው በቀፎ ውስጥ አኖሩት፤ ወደ ባቢሎንም ንጉሥ አመጡት፤ ድምፁም በእስራኤል ተራሮች ላይ ከዚያ ወዲያ እንዳይሰማ ወደ ግዞት ቤት አገቡት። 10 “እናትህ በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለች እንደ ወይን ግንድና እንደ ጽጌረዳ ነበረች፤ ከውኃም ብዛት የተነሣ የምታፈራና የምትሰፋ ሆነች። 11 ከእርስዋም የጸናች በትር ወጣች፤ ለገዥዎችም በትር ሆነች፤ በዛፎችም መካከል ቁመቷ ረዘመ፤ በቅርንጫፎችዋም ርዝመቷ ታየ። 12 ነገር ግን በመዓት ተነቀለች፤ ወደ መሬትም ተጣለች፤ የሚያቃጥልም ነፋስ ፍሬዋን አደረቀ፤ ብርቱዎች በትሮችዋም ተሰበሩና ደረቁ፤ እሳትም በላቻቸው። 13 አሁንም በምድረ በዳ፥ በደረቅና በተጠማች መሬት ተተከለች። 14 ከተመረጡት ጫፎችዋም በትር እሳት ወጣች፤ ፍሬዋንም በላች፤ የነገሥታትም በትር ይሆን ዘንድ የበረታ በትር የለባትም።” ይህ ሙሾ ነው፤ ለልቅሶም ይሆናል። |