ሕዝቅኤል 18 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)“ኀጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች” 1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 “በእስራኤል ልጆች፦ ‘አባቶች ጨርቋ የወይን ፍሬ በሉ፥ የልጆችም ጥርሶች ጠረሱ’ ብላችሁ በመካከላችሁ የምትመስሉት ምሳሌ ምንድን ነው? 3 እኔ ሕያው ነኝ! እንግዲህ ወዲህ ይህን ምሳሌ በእስራኤል ዘንድ አትመስሉትም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 4 እነሆ ነፍሳት ሁሉ የእኔ ናቸው፤ የአባት ነፍስ የእኔ እንደ ሆነች እንዲሁ የልጅ ነፍስ የእኔ ናት፤ ኀጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች። 5 “ሰውም ጻድቅ ቢሆን ፍርድንና ቅን ነገርንም ቢያደርግ፤ 6 በተራራም ላይ ባይበላ፥ ዐይኖቹንም ወደ እስራኤል ቤት ጣዖታት ባያነሣ፥ የባልንጀራውንም ሚስት ባያረክስ፥ አደፍም ወዳለባት ሴት ባይቀርብ፤ 7 ሰውንም ባያስጨንቅ፥ ለባለ ዕዳም መያዣውን ቢመልስ፥ ፈጽሞም ባይቀማ፥ ከእንጀራውም ለተራበ ቢሰጥ፥ የተራቈተውንም ከልብሱ ቢያለብስ፤ 8 በአራጣ ባያበድር፥ አትርፎም ባይወስድ፥ እጁንም ከኀጢአት ቢመልስ፥ በሰውና በሰው መካከልም የእውነትን ፍርድ ቢፈርድ፥ 9 በትእዛዜም ቢሄድ፥ እውነትንም ለማድረግ ፍርዴን ቢጠብቅ፥ እርሱ ጻድቅ ነው፤ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 10 “እርሱም ቀማኛና ደም አፍሳሽ ልጅን፥ ከዚህም ሁሉ አንዳቸውን የሚያደርገውን ቢወልድ፥ 11 እርሱም በጻድቅ አባቱ መንገድ ባይሄድ፥ በተራራም ላይ ቢበላ፥ የባልንጀራውንም ሚስት ቢያረክስ፥ 12 ድሀውንና ችግረኛውን ቢያስጨንቅ፥ ቢቀማም፥ መያዣውንም ባይመልስ፥ ዐይኖቹንም ወደ ጣዖታት ቢያነሣ፥ ርኩስንም ነገር ቢያደርግ፥ 13 በአራጣ ቢያበድር፥ አትርፎም ቢወስድ፥ እንደዚህ ያለ ሰው በሕይወት አይኖርም፤ ይህን ርኵሰት ሁሉ አድርጎአልና ፈጽሞ ይሞታል፤ ደሙም በላዩ ይሆናል። 14 “እነሆም ልጅ ቢወልድ፥ እርሱም አባቱ የሠራውን ኀጢአት አይቶ ቢፈራ፥ እንደርሱም ባይሠራ፥ 15 በተራራ ላይ ባይበላ፥ ዐይኖቹንም ወደ እስራኤል ቤት ጣዖታት ባያነሣ፥ የባልንጀራውንም ሚስት ባያረክስ፤ 16 ሰውንም ባያስጨንቅ፥ መያዣውንም ባይወስድ፥ ባይቀማም፥ ከእንጀራውም ለተራበ ቢሰጥ፥ ለተራቈተውም ልብስን ቢያለብስ፥ 17 እጁንም ከዐመፅ ቢመልስ፥ አራጣንም አትርፎ ባይወስድ፥ ፍርዴንም ቢያደርግ፥ በትእዛዜም ቢሄድ፥ እርሱ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ በአባቱ ኀጢአት አይሞትም። 18 አባቱ ግን ፈጽሞ በድሎአልና፥ ወንድሙንም ቀምቶአልና፥ በሕዝቡም መካከል ክፉን ነገር አድርጎአልና እነሆ እርሱ በበደሉ ይሞታል። 19 “እናንተ ግን፦ ልጅ የአባቱን ኀጢአት ስለ ምን አይሸከምም? ትላላችሁ። ልጅ ፍርድንና ቅን ነገርን በአደረገ፥ ትእዛዜንም ሁሉ በጠበቀና በአደረገ ጊዜ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል። 20 ኀጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች፤ ልጅ የአባቱን ኀጢአት አይሸከምም፤ አባትም የልጁን ኀጢአት አይሸከምም፤ የጻድቁ ጽድቅ በራሱ ላይ ይሆናል፤ የኀጢአተኛውም ኀጢአት በራሱ ላይ ይሆናል። 21 “ኀጢአተኛውም ከአደረጋት ኀጢአት ሁሉ ቢመለስ፥ ትእዛዜንም ሁሉ ቢጠብቅ፥ ፍርድንና ቅን ነገርንም ቢያደርግ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። 22 የበደለው በደል ሁሉ አይታሰብበትም፤ በሠራው ጽድቅ በሕይወት ይኖራል። 23 በውኑ ኀጢአተኛ ይሞት ዘንድ መፍቀድን እፈቅዳለሁን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከክፉ መንገዱ ይመለስና በሕይወት ይኖር ዘንድ ነው እንጂ። 24 ጻድቁ ግን ከጽድቁ ቢመለስ፥ ኀጢአትንም ቢሠራ፥ ኀጢአተኛውም እንደሚያደርገው ርኵሰት ሁሉ ቢያደርግ፥ በሕይወት ይኖራልን? የሠራው ጽድቅ ሁሉ አይታሰብለትም፤ በአደረገው ዐመፅና በሠራት ኀጢአት በዚያች ይሞታል። 25 “እናንተ ግን፦ የጌታ መንገድ የቀናች አይደለችም ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ! እንግዲህ ስሙ፤ በውኑ መንገዴ የቀናች አይደለችምን? ይልቅስ የእናንተ መንገድ ያልቀናች አይደለችምን? 26 ጻድቁ ከጽድቁ ቢመለስ፥ ኀጢአትንም በሠራ ጊዜ፥ በዚያ ቢሞት፥ እርሱ በአደረገው በደል ይሞታል። 27 ኀጢአተኛውም ከሠራው ኀጢአት ቢመለስ፥ ፍርድንና ቅን ነገርንም ቢያደርግ ነፍሱን ይጠብቃል። 28 ከሠራው ሁሉ በደል አይቶ ተመልሶአልና ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። 29 ነገር ግን የእስራኤል ቤት፦ የጌታ መንገድ የቀናች አይደለችም ይላሉ። የእስራኤል ቤት ሆይ! በውኑ መንገዴ የቀናች አይደለችምን? ይልቅስ የእናንተ መንገድ ያልቀናች አይደለችምን? 30 የእስራኤል ቤት ሆይ! ስለዚህ እንደ መንገዱ በየሰዉ ሁሉ እፈርድባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ንስሓ ግቡ፤ ኀጢአትም ዕንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኀጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ። 31 የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ፤ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስንም ለእናንተ አድርጉ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ! ስለ ምን ትሞታላችሁ? 32 የምዋቹን ሞት አልፈቅድምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ በንስሓ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ። |