ሕዝቅኤል 16 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እምነት የጐደላት ኢየሩሳሌም 1 የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ! ለኢየሩሳሌም ኀጢአትዋን አስታውቃት፤ እንዲህም በላት፦ 3 ጌታ እግዚአብሔር ለኢየሩሳሌም እንዲህ ይላል፦ ዘርሽና ትውልድሽ ከከነዓን ምድር ነው፤ አባትሽ አሞራዊ ነበረ፤ እናትሽም ኬጢያዊት ነበረች። 4 በተወለድሽ ጊዜ በዚያው ቀን እትብትሽ አልታተበም፤ ንጹሕም ትሆኚ ዘንድ በውኃ አልታጠብሽም፤ በጨውም አልተወለወልሽም፤ በጨርቅም አልተጠቀለልሽም፤ በጭንም አልታቀፍሽም። 5 በተወለድሽበት ቀን ከሰውነትሽ ጕስቍልና የተነሣ በሜዳ ላይ ተጣልሽ እንጂ፥ ከዚህ አንዳች ይደረግልሽ ዘንድ ዐይኔ አልራራልሽም፤ ማንም አላዘነልሽም። 6 “በአንቺም ዘንድ ባለፍሁ ጊዜ፤ በደምሽም ተለውሰሽ በአየሁሽ ጊዜ፦ ከደምሽ ዳኝ አልሁሽ፤ 7 በእርሻ ላይ እንደ አለ ቡቃያ አበዛሁሽ፤ አንቺም አደግሽ፤ ታላቅም ሆንሽ፤ በእጅጉም አጌጥሽ፤ ከከተማ ወደ ከተማ ገባሽ፤ ጡቶችሽም አጐጠጐጡ፤ ጠጕርሽም አደገ፤ ነገር ግን ዕርቃንሽን ሆንሽ፤ ተራቍተሽም ነበርሽ። 8 በአንቺ ዘንድ በአለፍሁና በአየሁሽ ጊዜ፥ እነሆ ጊዜሽ እንደ ደረሰ፥ በአንቺም የሚያድሩ ሰዎች ጊዜ እንደ ደረሰ አየሁ። እጆችን በላይሽ ዘረጋሁ፤ ኀፍረተ ሥጋሽንም ከደንሁ፤ ማልሁልሽም፤ ከአንቺም ጋራ ቃል ኪዳን ገባሁ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ አንቺም ለእኔ ሆንሽ። 9 በውኃም አጠብሁሽ፤ ከደምሽም አጠራሁሽ፤ በዘይትም ቀባሁሽ። 10 ወርቀ ዘቦም አለበስሁሽ፤ ጥቁር ጫማም አደረግሁልሽ፤ በጥሩ በፍታ አስታጠቅሁሽ፤ በሐርም ከደንሁሽ። 11 በጌጥም አስጌጥሁሽ፤ በእጅሽም ላይ አንባር፥ በአንገትሽም ላይ ድሪ አደረግሁልሽ። 12 በአፍንጫሽም ቀለበት፥ በጆሮሽም ጉትቻ፥ በራስሽም ላይ የክብር አክሊል አደረግሁ። 13 በወርቅና በብር አጌጥሽ፤ ልብስሽም ጥሩ በፍታና ሐር፥ ወርቀ ዘቦም ነበረ፤ አንቺም መልካምን ዱቄትና ማርን፥ ዘይትንም በላሽ፤ ወፈርሽ፤ እጅግም ውብ ሆንሽ፤ ለመንግሥትም የተዘጋጀሽ አደረግሁሽ። 14 ባንቺ ላይ ከአኖርኋት ከክብሬ የተነሣ ውበትሽ ፍጹም ነበረና ስምሽ በአሕዛብ መካከል ተሰማ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 15 “ነገር ግን በውበትሽ ታምነሻል፤ በስምሽም አመንዝረሻል፤ ምንዝርናሽንም ከመንገድ አላፊ ሁሉ ጋር አበዛሽ። 16 ከልብስሽም ወስደሽ በመርፌ የተጠለፉ ጣዖታትን ሠራሽ፤ አመነዘርሽባቸውም፤ ስለዚህ ፈጽመሽ አልገባሽም፤ ከእንግዲህም ወዲህ እንዲህ ያለ ነገር አይሆንም። 17 ከሰጠሁሽም ከወርቄና ከብሬ የተሠራውን የክብርሽን ዕቃ ወስደሽ የወንድ ምስሎችን ለራስሽ አድርገሻል፤ አመንዝረሽባቸውማል። 18 ወርቀ ዘቦውን ልብስሽንም ወስደሽ ደረብሽላቸው፤ ዘይቴንና ዕጣኔንም በፊታቸው አኖርሽ። 19 የሰጠሁሽንም እንጀራዬን፥ ያበላሁሽንም ዱቄትና ዘይቱን፥ ማሩንም ጣፋጭ ሽታ አድርገሽ በፊታቸው አኖርሽ፤ እንዲህም ሆኖአል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 20 ለእኔም የወለድሻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽን ወስደሽ መብል ይሆኑ ዘንድ ሠዋሽላቸው፤ ገደልሻቸውም። 21 ልጆችን አረድሽ፤ ለሚቃጠል መሥዋዕትም አሳልፈሽ ሰጠሽ፤ በውኑ ግልሙትናሽ ጥቂት ነውን? 22 ከኀጢአትሽና ከዝሙትሽ ሁሉ ይህ ይከፋል፤ አንቺ ዕራቁትሽን ሳለሽ፥ ኀፍረትም ሞልቶብሽ ሳለሽ፥ በደምሽም ተለውሰሽ ሳለሽ፥ የሕፃንነትሽን ወራት አላሰብሽም። 23 “ከዚህም ከክፋትሽ ሁሉ በኋላ ወዮልሽ! ወዮልሽ! ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 24 የምትሰስኝበትን ቤት ለራስሽ ሠራሽ፤ በአደባባዩ ሁሉ ከፍ ያለ ቦታን አደረግሽ። 25 በየመንገዱ ራስ ከፍ ያለውን ቦታሽን ሠራሽ፤ ውበትሽንም አረከስሽ፤ ለመንገድ አላፊም ሁሉ እግርሽን ገለጥሽ፤ ዝሙትሽንም አበዛሽ። 26 አካላቸውም ከወፈረ ከጐረቤቶችሽ ከግብፃውያን ልጆች ጋር አመነዘርሽ፤ እኔንም ታስቆጭ ዘንድ ዝሙትሽን አበዛሽ። 27 ስለዚህ እነሆ እጄን በአንቺ ላይ ዘርግቻለሁ፤ ድርሻሽንም አጕድያለሁ፤ ለሚጠሉሽም፥ ከመንገድሽ ለመለሱሽና ለአሳቱሽ ለፍልስጥኤም ሴቶች ልጆች ፈቃድ አሳልፌ ሰጥቼሻለሁ። 28 ከአሦራውያን ልጆች ጋር ፈጽመሽ አመነዘርሽ፤ ከዚህም ጋር ገና አልጠገብሽም፤ ዝሙትሽም አልበቃሽም። 29 እስከ ከነዓን ምድር እስከ ከላውዴዎንም ድረስ ዝሙትሽን አበዛሽ። ከዚህም ጋር ገና አልጠገብሽም። 30 “ይህን ሁሉ የሴሰኛ ሴት ሥራን ሠርተሻልና፥ ከሴቶች ልጆችሽም ጋር ሦስት ጊዜ አመንዝረሻልና ሴቶች ልጆችሽን ምን አደርጋቸዋለሁ? ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 31 በየመንገዱ ራስ የምንዝርናሽን ስፍራ ሠርተሻል፤ በየአደባባዩም ከፍ ያለውን ቦታሽን አድርገሻል። ዋጋዋን እንደምትሰበስብ እንደ ጋለሞታም አልሆንሽም። 32 ከባልዋ ገንዘብ ተቀብላ የምታመነዝር ሴትን ትመስያለሽ። 33 ለአመንዝራዎች ሁሉ ዋጋ ይሰጡአቸዋል፤ አንቺ ግን ለወዳጆችሽ ሁሉ ዋጋ ትሰጫለሽ፤ ከአንቺም ጋር ለማመንዘር በዙሪያሽ ይገቡብሽ ዘንድ መማለጃን ትሰጫቸዋለሽ። 34 ዝሙትሽ ከሌሎች ሴቶች ዝሙት ልዩ ነው፤ ማንም ለዝሙት የሚከተልሽ የለም፤ ዋጋ ሳይሰጥሽ አንቺ ዋጋ በመስጠትሽ በዚህ ነገር ልዩ ሆነሻል። የእግዚአብሔር ፍርድ በኢየሩሳሌም ላይ 35 “ስለዚህ ዘማ ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሚ። 36 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወርቄን በትነሻልና ከኀጢአት ምኞት በሠራሽው ዝሙት ኀፍረተ ሥጋሽን ገልጠሻልና በሰጠሻቸውም በልጆችሽ ደም፥ 37 ስለዚህ እነሆ እኔ ከአንቺ ጋር አንድ የሆኑ ውሽሞችሽን በአንቺ ላይ እሰበስባቸዋለሁ፤ የምትወጃቸውንም ከምትጠያቸው ጋር በአንቺ ላይ እሰበስባቸዋለሁ፤ ይከቡሻል፤ በእነርሱም ዘንድ ጕስቍልናሽን እገልጥብሻለሁ፤ ሁሉም ኀፍረትሽን ያዩብሻል። 38 በአመንዝሮችና በደም አፍሳሾች በቀል እበቀልሻለሁ፤ በመዓትና በቅንአት ደምም አስቀምጥሻለሁ። 39 በእጃቸውም አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤ የምንዝርናሽንም ስፍራ ያፈርሳሉ፤ ከፍ ያለውንም ቦታሽን ይገለብጣሉ፤ ልብስሽንም ይገፉሻል፤ የክብርሽንም ጌጥ ይወስዳሉ፤ ዕራቁትሽንም ይተዉሻል፤ ቷረጃለሽም። 40 ብዙ ሕዝብን ይሰበሰቡብሻል፤ በድንጋይም ይወግሩሻል፤ በሰይፋቸውም ይወጉሻል። 41 ቤቶችሽንም በእሳት ያቃጥላሉ፤ በብዙም ሴቶች ፊት ይበቀሉሻል፤ ግልሙትናሽንም አስተውሻለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ዋጋ አትሰጪም። 42 መዓቴንም በአንቺ ላይ እጨርሳለሁ፤ ቅንዓቴም ከአንቺ ይርቃል፤ እኔም ዝም እላለሁ፤ ደግሞም አልቈጣም። 43 የሕፃንነትሽን ወራት አላሰብሽምና፥ በዚህም ነገር ሁሉ አስቈጥተሽኛልና፤ ስለዚህ እነሆ እኔ ደግሞ መንገድሽን በራስሽ ላይ አመጣለሁ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እንደዚህም በበደልሽ ሁሉ ላይ ኀጢአትን ሠራሽ። ልጅቱ እንደ እናቷ 44 “እነሆ በምሳሌ የሚናገር ሁሉ፥ እንደ እናቲቱ እንዲሁ ልጅቱ ናት፤ እያለ ምሳሌ ይመስልብሻል። 45 አንቺ ባልዋንና ልጆችዋን የጠላች የእናትሽ ልጅ ነሽ፤ አንቺም ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን የጠሉ የእኅቶችሽ እኅት ነሽ፤ እናታችሁ ኬጢያዊት ነበረች፤ አባታችሁም አሞራዊ ነበረ። 46 ታላቂቱም እኅትሽ ከሴቶች ልጆችዋ ጋር በስተ ግራሽ የምትቀመጥ ሰማርያ ናት፤ ታናሽቱም እኅትሽ ከሴቶች ልጆችዋ ጋር በሰተ ቀኝሽ የምትቀመጥ ሰዶም ናት። 47 አንቺ ግን በመንገዳቸው አልሄድሽም፤ እንደ ኀጢአታቸውም አላደረግሽም፤ ያው ለአንቺ ጥቂት ነበረና በመንገድሽ ሁሉ ከእነርሱ የሚከፋ ኀጢአት አደረግሽ። 48 እኔ ሕያው ነኝ! አንቺና ሴቶች ልጆችሽ እንዳደረጋችሁት እንዲሁ ሰዶምና ሴቶች ልጆችዋ አላደረጉም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 49 እነሆ የእኅትሽ የሰዶም ኀጢአት ይህ ነበረ፤ ትዕቢት፥ እንጀራን መጥገብ፥ መዝለልና ሥራን መፍታት፥ ይህ ሁሉ በእርስዋና በልጆችዋ ነበር፤ የችግረኛውንና የድሀውንም እጅ አላጸናችም። 50 ኰርተው ነበር፤ በፊቴም ርኵስ ነገር አደረጉ፤ ስለዚህ እንደ አየሁ አስወገድኋቸው። 51 ሰማርያም የኀጢአትሽን እኩሌታ አልሠራችም፤ አንቺ ግን ከእኅቶችሽ ይልቅ ኀጢአትን አበዛሽ፤ በሠራሽውም ኀጢአት ሁሉ አጸደቅሻቸው። 52 አሁንም ከእነርሱ ይልቅ አብዝተሽ በሠራሽው ኀጢአትሽ እኅቶችሽን ስላረከስሻቸው ቅጣትሽን ተሸከሚ። ከአንቺም ይልቅ አጸደቅሻቸው፤ አንችም እፈሪ፤ እፍረትሽንም ተሸከሚ፤ እኅቶችሽን አጽድቀሻቸዋልና። 53 ምርኮአቸውንም እመልሳለሁ፤ የሰዶምና የሴቶች ልጆችዋን ምርኮ፥ የሰማርያንና የሴቶች ልጆችዋን ምርኮ እመልሳለሁ፤ በመካከላቸውም ያሉትን የምርኮኞችሽን ምርኮ እመልሳለሁ። 54 ፍዳሽንም ትቀበዪ ዘንድ በአስቈጣሽኝ ሥራሽ ሁሉ ታፍሪያለሽ። 55 እኅቶችሽም ሰዶምና ሴቶች ልጆችዋ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ፤ ሰማርያና ሴቶች ልጆችዋም ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ፤ አንቺና ሴቶች ልጆችሽም ወደ ቀድሞ ሁኔታችሁ ትመለሳላችሁ። 56 እኅትሽ ሰዶምም በትዕቢትሽ ቀን በአፍሽ አልተወሳችም። 57 ክፋትሽ እንደ ዛሬው ሳይገለጥ ለሶርያ ሴቶች ልጆችና ለጐረቤቶችዋ ሁሉ በዙሪያሽም ለሚከቡሽ ፍልስጥኤማውያት ሴቶች ልጆች መሰደቢያ ሆነሻል። 58 ኀጢአትሽንና በደልሽን ተሽክመሻል፥ ይላል እግዚአብሔር። የዘለዓለም ቃል ኪዳን 59 “ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ አንቺ ቃል ኪዳንን በማፍረስ መሐላን የናቅሽ ሆይ! አንቺ እንዳደረግሽ እኔ ደግሞ አደርግብሻለሁ። 60 ነገር ግን በሕፃንነትሽ ወራት ከአንቺ ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳኔን ዐስባለሁ፤ የዘለዓለምንም ቃል ኪዳን አጸናልሻለሁ። 61 ታላቆቹንና ታናሾቹን እኅቶችሽንም በተቀበልሽ ጊዜ መንገድሽን ታስቢያለሽ፤ ታፍሪማለሽ፤ ለአንቺም ልጆች ይሆኑ ዘንድ እሰጣቸዋለሁ፤ ስለ ቃል ኪዳንሽ ግን አይደለም። 62 እኔም ቃል ኪዳኔን ከአንቺ ጋር አጸናለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ። 63 ታስቢ ዘንድ፥ ታፍሪም ዘንድ፥ ደግሞም ስላደረግሽው ነገር ሁሉ ይቅር ባልሁሽ ጊዜ፥ስለ ኀፍረትሽ አፍሽን ትከፍቺ ዘንድ አይቻልሽም፤” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |