ሕዝቅኤል 15 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የወይን ተክል ምሳሌ 1 የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ! የወይን ግንድ ከዱር ዛፎች ሁሉና ከዱር ዛፎች ቅርንጫፎች ሁሉ ይልቅ ብልጫው ምንድን ነው? 3 በውኑ ሥራ የሚሠራበትን እንጨት ከእርሱ ይወስዳሉን? ወይስ ሰዎች ዕቃ የሚንጠለጠልበትን ኩላብ ከእርሱ ይወስዳሉን? 4 እነሆ ለመቃጠል በእሳት ላይ ተጥሎአል፤ እሳቱም ሁለቱን ጫፎቹን በልቶአል፤ መካከሉም ተቃጥሎአል፤ በውኑ ለሥራ ይጠቅማልን? 5 ከውፍረቱም የተነሣ ለሥራ አይሆንም፤ ለምትበላና ለምታጠፋ እሳት ይሆናል እንጂ ከዚያ በኋላ በውኑ ለሥራ ይሆናልን? 6 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዱር ዛፎች መካከል ያለውን የወይን ግንድ እሳት ይበላው ዘንድ እንደ ሰጠሁት፥ እንዲሁ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን አሳልፌ እሰጣለሁ። 7 ፊቴንም በእነርሱ ላይ አጸናለሁ፤ ከእሳትም አይወጡም፤ እሳትም ይበላቸዋል፤ ፊቴንም በእነርሱ ላይ በአጸናሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 8 ዐመፅን አድርገዋልና ምድሪቱን ባድማ አደርጋለሁ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |