ሕዝቅኤል 14 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ጣዖት አምላኪዎች እንደ ተወገዙ 1 ከእስራኤልም ሽማግሌዎች አያሌ ሰዎች ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ። 2 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 3 “የሰው ልጅ ሆይ! እነዚህ ሰዎች በልባቸው ጣዖቶቻቸውን አኑረዋል፤ የበደላቸውንም መቅሠፍት በፊታቸው አቁመዋል፤ እኔስ ለእነርሱ መልስ ልመልስላቸውን? 4 ስለዚህ ንገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከእስራኤል ቤት ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም መቅሠፍት በፊቱ የሚያቆም ሰው ሁሉ ወደ ነቢዩ ቢመጣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ጣዖታቱ ብዛት እመልስለታለሁ። 5 ይህም የእስራኤልን ወገኖች በዐሳባቸው ከእኔ እንደ ተለዩበት እንደ ልባቸውና እንደ ርኵሰታቸው ያስታቸው ዘንድ ነው።” 6 ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፥ “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ንስሓ ግቡ፤ ከበደላችሁም ተመለሱ፤ ፊታችሁንም ከኀጢአታችሁ ሁሉ መልሱ። 7 ከእስራኤልም ቤት፥ በእስራኤልም ዘንድ ከሚቀመጡ መጻተኞች የሚሆን፥ ከእኔ ተለይቶ ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም መቅሠፍት በፊቱ የሚያቆም ሰው ሁሉ ስለ እኔ ይጠይቅ ዘንድ ወደ ነቢዩ በመጣ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር በራሴ እመልስለታለሁ። 8 ፊቴንም በዚያ ሰው ላይ አደርጋለሁ፤ እንዲጠፋም አደርገዋለሁ፤ ከሕዝቤም መካከል አስወግደዋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 9 ነቢዩም ቢታለል፥ ቃልንም ቢናገር፥ ያን ነቢይ ያታለልሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ እጄንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ፤ ከሕዝቤም ከእስራኤል መካከል አጠፋዋለሁ። 10 ኀጢአታቸውን ይሸከማሉ፤ እንደሚጠይቀውም ሰው ኀጢአት እንዲሁ የነቢዩ ኀጢአት ይሆናል። 11 ይኸውም የእስራኤል ቤት ደግሞ ከእኔ ርቀው እንዳይስቱ፥ በኀጢአታቸውም ሁሉ እንዳይረክሱ ነው፤ እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 12 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 13 “የሰው ልጅ ሆይ! ምድር ብትበድለኝ፥ ብትስት፥ ኀጢአትም ብትሠራ እጄን በእርስዋ አነሣለሁ፤ የእህሉንም ኀይል አጠፋለሁ፤ በእርስዋም ረሀብን እልካለሁ፤ ከብቱንና ሰዉንም ከእርስዋ አጠፋለሁ። 14 እነዚህ ሦስቱ ሰዎች ኖኅና ዳንኤል ኢዮብም በመካከልዋ ቢኖሩ በጽድቃቸው የገዛ ነፍሳቸውን ያድናሉ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 15 በዚያች ሀገር ላይ ክፉ አውሬን ባመጣ፥ ፈጽሜም ባጠፋት በዚያም አውሬ ፊት የሚያልፍ ባይገኝ፥ 16 እነዚህ ሦስት ሰዎች በመካከልዋ ቢኖሩ፥ እኔ ሕያው ነኝ! እነርሱ ብቻቸውን ይድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም፤ ምድሪቱም ባድማ ትሆናለች፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 17 ወይም በዚያች ምድር ላይ ሰይፍ አምጥቼ፦ ሰይፍ ሆይ! በምድሪቱ ላይ እለፊ ብል፥ ሰውንና እንስሳውንም ከእርስዋ ባጠፋ፥ 18 እነዚህ ሦስት ሰዎች በመካከልዋ ቢኖሩ፥ እኔ ሕያው ነኝ! እነርሱ ብቻቸውን ይድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 19 ወይም በዚያች ምድር ላይ ቸነፈርን ብሰድድ፥ ሰውንና እንስሳውንም ከእርስዋ አጠፋ ዘንድ መዓቴን በደም ባፈስስባት፥ 20 ኖኅና ዳንኤል ኢዮብም በመካከልዋ ቢኖሩ፤ እኔ ሕያው ነኝ! በጽድቃቸው ነፍሳቸውን ብቻ ያድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 21 ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፥ “ይልቁንስ ሰውንና እንስሳን ከእርስዋ አጠፋ ዘንድ በኢየሩሳሌም ላይ አራቱን ክፉ መቅሠፍቶችን፥ ሰይፍንና ራብን፥ ክፉዎችንም አውሬዎች፥ ቸነፈርንም ስሰድድባት፥ 22 ነገር ግን እነሆ የሚያመልጡና ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ከእርስዋ የሚያወጡ ይቀሩላታል፤ እነሆ ወደ እናንተ ይወጣሉ፤ እናንተም መንገዳቸውንና ሥራቸውን ታያላችሁ፤ በኢየሩሳሌምም ላይ ስላመጣሁት ክፉ ነገር ሁሉ፥ ስላመጣሁባትም ነገር ሁሉ ትጽናናላችሁ፤ 23 መንገዳቸውንና ሥራቸውን በአያችሁ ጊዜ ያጽናኗችኋል፤ ያደረግሁባትንም ሁሉ በከንቱ እንዳላደረግሁባት ታውቃላችሁ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |