ሕዝቅኤል 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ነቢዩ እንደ ስደተኛ 1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ! በዐመፀኛ ቤት መካከል ተቀምጠሃል፤ እነርሱ ያዩ ዘንድ ዐይን አላቸው ነገር ግን አያዩም፤ ይሰሙም ዘንድ ጆሮ አላቸው፤ ነገር ግን አይሰሙም፤ እነርሱ ዐመፀኛ ቤት ናቸውና። 3 አንተም የሰው ልጅ ሆይ! የስደተኛ እክት አዘጋጅ፤ በፊታቸውም ቀን ለቀን ተማረክ፤ በፊታቸውም ከስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ ተማርከህ ሂድ፤ እነርሱም ዐመፀኛ ቤት እንደ ሆኑ ምንአልባት ያስተውሉ ይሆናል። 4 ቀን ለቀንም በፊታቸው እክትህን እንደ ስደተኛ እክት አውጣው፤ በማታም ጊዜ በዐይናቸው እያዩህ ስደተኞች እንደሚወጡ እንዲሁ ውጣ። 5 በፊታቸውም ግንቡን ነድለህ በዚያ ውጣ። 6 ለእስራኤልም ቤት ምልክት አድርጌሃለሁና በፊታቸው ዕቃህን በትከሻህ ላይ አንግተው፤ በጨለማም ተሸክመህ ውጣ፤ ምድሪቱንም እንዳታይ ፊትህን ሸፍን።” 7 እንዳዘዘኝም አደረግሁ፤ ቀን ለቀንም እክቴን እንደ ስደተኛ እክት አወጣሁ፤ በማታም ጊዜ ግንቡን በእጄ ነደልሁ፤ በጨለማም አወጣሁት፤ በፊታቸውም በትከሻዬ ላይ አንግቼ ተሸከምሁት። 8 በነጋውም የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 9 “የሰው ልጅ ሆይ! ዐመፀኛ ቤት የእስራኤል ቤት፦ የምታደርገው ምንድር ነው? አላሉህምን? 10 አንተም፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህ ሸክም በኢየሩሳሌም በሚኖረው አለቃ ላይ፥ በመካከላቸውም በሚኖሩት በእስራኤል ቤት ሁሉ ላይ ነው በላቸው። 11 ደግሞም፦ እኔ ምልክታችሁ ነኝ፤ እኔ እንዳደረግሁ እንዲሁ ይደረግባቸዋል፥ እነርሱንም ማርከው ይወስዷቸዋል በል። 12 በመካከላቸውም የሚኖረው አለቃ በትከሻው ላይ አንግቶ በጨለማ ይወጣል፤ በዚያ ያወጡ ዘንድ ግንቡን ይነድላሉ፤ በዐይኑም ምድርን እንዳያይ ፊቱን ይሸፍናል። 13 መረቤንም በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ፤ በወጥመዴም ይያዛል፤ ወደ ከለዳውያንም ምድር ወደ ባቢሎን አመጣዋለሁ፤ ሆኖም አያያትም፤ በዚያም ይሞታል። 14 የሚረዱትንም፥ በዙሪያው ያሉትን ሁሉ፥ ጭፍሮቹንም ሁሉ ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናቸዋለሁ፤ በኋላቸውም ሰይፍን እመዝዛለሁ። 15 በአሕዛብም መካከል በምበትናቸው ጊዜ፥ በሀገሮችም በምዘራቸው ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 16 በሚሄዱባቸውም አሕዛብ መካከል ርኵሰታቸውን ሁሉ ይናገሩ ዘንድ ከሰይፍና ከራብ፥ ከቸነፈርም ጥቂቶች ሰዎችን ከእነርሱ አስቀራለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” 17 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 18 “የሰው ልጅ ሆይ! እንጀራህን በመታወክ ብላ፤ ውኃህንም በፍርሃትና በድንጋጤ ጠጣ፤ 19 ለምድሪቱም ሕዝብ፦ ጌታ እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ስለሚኖሩ ስለ እስራኤል ምድርም እንዲህ ይላል፦ የሚኖሩባት ሁሉ በዐመፅ ይኖራሉና ምድሪቱ በመላዋ ትጠፋ ዘንድ እንጀራቸውን በችግር ይበላሉ፤ ውኃቸውንም በድንጋጤ ይጠጣሉ። 20 ሰዎች የሚኖሩባቸው ከተሞች ይጠፋሉ፤ ምድሪቱም ውድማ ትሆናለች፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ በላቸው።” 21 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 22 “የሰው ልጅ ሆይ! በእስራኤል ምድር፦ ዘመኑ ረዝሞአል፤ ራእዩም ሁሉ ጠፍቶአል የምትሉት ምሳሌው ምንድን ነው? 23 ስለዚህ እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህን ምሳሌ አስቀረዋለሁ፤ በእስራኤልም ዘንድ ደግሞ ምሳሌ አድርገው አይናገሩትም፤ አንተ ግን፦ ዘመኑና የራእዩ ሁሉ ነገር ቀርቦአል በላቸው። 24 ከዚህም በኋላ በእስራኤል ቤት መካከል ከንቱ ራእይና ውሸተኛ ምዋርት አይሆንም። 25 እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ እናገራለሁ፤ የምናገረውም ቃል ይፈጸማል፤ ደግሞም አይዘገይም፤ እናንተ ዐመፀኛ ቤት ሆይ! በዘመናችሁ ቃሌን እናገራለሁ፤ እፈጽመውማለሁ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 26 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 27 “የሰው ልጅ ሆይ! ዐመፀኛው የእስራኤል ቤት፦ ይህቺ የሚያያት ራእይ ለብዙ ዘመን ናት፤ እርሱም ለሩቅ ወራት ትንቢትን ይናገራል” ይላሉ። 28 ስለዚህ በላቸው፥ “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የምናገረው ቃል ይፈጸማል እንጂ ከቃሌ ሁሉ ደግሞ የሚዘገይ የለም፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |