ሕዝቅኤል 11 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በኢየሩሳሌም ላይ የተላለፈ ፍርድ 1 መንፈስም አነሣኝ፤ ወደ ምሥራቅም አንጻር ወደሚያሳየው ወደ እግዚአብሔር ቤት በር ወሰደኝ። እነሆም በበሩ መግቢያ ሃያ አምስት ሰዎች ነበሩ፤ በመካከላቸውም የሕዝቡን አለቆች የዓዙርን ልጅ ያእዛንያንና የበናያስ ልጅ ፈላጥያን አየሁ። 2 እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “የሰው ልጅ ሆይ! እነዚህ ከንቱን የሚያስቡ፥ በዚችም ከተማ ክፉን ምክር የሚመክሩ ሰዎች ናቸው። 3 እነርሱም፦ በውኑ ቤቶች በድንገት የሚሠሩ አይደለምን? ይህች ከተማ ድስት እኛም ሥጋ ነን ብለዋል። 4 ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ! ትንቢት ተናገርባቸው፤ ትንቢት ተናገር።” 5 የእግዚአብሔርም መንፈስ በላዬ መጣ፤ እንዲህም አለኝ፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ተናገር፦ የእስራኤል ቤት ሆይ! ይህን ነገር ተናግራችኋል፤ እኔም የሰውነታችሁን በደል አውቃለሁ። 6 በዚህች ከተማ ውስጥ ግዳዮቻችሁን አብዝታችኋል፤ በጎዳናዎችዋም ሙታናችሁን ሞልታችኋል። 7 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመካከልዋ ያኖራችኋቸው ግዳዮቻችሁ እነርሱ ሥጋ ናቸው፤ ይህችም ከተማ ድስት ናት፤ እናንተን ግን ከመካከልዋ አወጣችኋለሁ። 8 ሰይፍን ትፈራላችሁ፤ እኔም ሰይፍን አመጣባችኋለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 9 ከመካከልዋም አወጣችኋለሁ፤ በባዕዳንም እጅ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ በላያችሁም ፍርድን አደርጋለሁ። 10 በሰይፍ ትወድቃላችሁ፤ በእስራኤልም ተራሮች እፈርድባችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 11 ይህች ከተማ ድስት አትሆንላችሁም፤ እናንተም በመካከልዋ ሥጋ አትሆኑም፤ እኔም በእስራኤል ተራሮች እፈርድባችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 12 በትእዛዜ አልሄዳችሁምና፥ ፍርዴንም አላደረጋችሁምና፥ በዙሪያችሁም እንደሚኖሩት እንደ አሕዛብ ሕግ አድርጋችኋል።” 13 ትንቢትም በተናገርሁ ጊዜ የበናያስ ልጅ ፈላጥያ ሞተ፤ እኔም በግንባሬ ተደፍቼ፥ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ወዮ! ወዮልኝ! በውኑ የእስራኤልን ቅሬታ ፈጽመህ ታጠፋለህን?” ብዬ በታላቅ ድምፅ ጮኽሁ። እግዚአብሔር ለስደተኞች የሰጠው ተስፋ 14 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 15 “የሰው ልጅ ሆይ! በኢየሩሳሌም የሚኖሩ፦ ከእግዚአብሔር ዘንድ ራቁ፤ ይህች ምድር ርስት ሆና ለእኛ ተሰጥታለች የሚሉአቸው ወንድሞችህና ዘመዶችህ፥ የምርኮ ሰዎችህም ሁሉ፥ የእስራኤልም ቤት ሁሉ ያልቃሉ። 16 ስለዚህ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ወደ አሕዛብ አርቄአቸዋለሁ፤ ወደ ሀገሮችም እበትናቸዋለሁ፤ ይሁን እንጂ በመጡባቸው ሀገሮች በእነዚያ ትንሽ መቅደስ እሆናቸዋለሁ በል። 17 ስለዚህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከአሕዛብ ዘንድ እቀበላቸዋለሁ፤ ከበተንሁባቸውም ሀገሮች እሰበስባቸዋለሁ፤ የእስራኤልንም ምድር እሰጣቸዋለሁ። 18 ወደዚያም ይመጣሉ፤ በደልንና ርኵሰትንም ሁሉ ከእርስዋ ያስወግዳሉ። 19 ሌላ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ በውስጣቸውም አዲስ መንፈስ አሳድራለሁ፤ ከሥጋቸውም ውስጥ የድንጋዩን ልብ አወጣለሁ፤ የሥጋንም ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ 20 በትእዛዜም ይሄዱ ዘንድ፥ ፍርዴንም ይጠብቁና ያደርጉ ዘንድ እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል፥ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ። 21 ጣዖት በሚያመልኩበት ልባቸውና በኀጢአታቸው እንደ ልባቸው ቢሄዱ መንገዳቸውን በራሳቸው ላይ እመልሳለሁ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የእግዚአብሔር ክብር ከኢየሩሳሌም መነሣት 22 ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ዘረጉ፥ መንኰራኵሮችም በአጠገባቸው ነበሩ፤ የእስራኤልም አምላክ ክብር በላያቸው ነበረ። 23 የእግዚአብሔርም ክብር ከከተማዪቱ መካከል ተነሥቶ በከተማዪቱ ምሥራቅ በኩል በአለው ተራራ ላይ ቆመ። 24 መንፈስም አነሣኝ፤ በእግዚአብሔርም መንፈስ በራእይ ወደ ከላውዴዎን ምድር ወደ ምርኮኞቹ አመጣኝ። 25 ያየሁትም ራእይ ከእኔ ወጣ። እግዚአብሔርም ያሳየኝን ነገር ሁሉ ለምርኮኞች ተናገርሁ። |