ሕዝቅኤል 10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእግዚአብሔር ክብር ከቤተ መቅደስ እንደ ተነሣ 1 እኔም አየሁ፤ እነሆም በኪሩቤል ራስ ላይ ባለው ጠፈር በላያቸው እንደ ሰንፔር ድንጋይ ያለ ዙፋን የሚመስል መልክ ተገለጠ። 2 በፍታም የለበሰውን ሰው፥ “በመንኰራኵሮች መካከል በኪሩብ በታች ግባ፤ ከኪሩቤልም መካከል ከአለው እሳት ፍም እጆችህን ሙላ፤ በከተማዪቱም ላይ በትነው” ብሎ ተናገረው። እኔም እያየሁ ገባ። 3 ሰውየውም ሲገባ ኪሩቤል በቤቱ ቀኝ በኩል ቆመው ነበር፤ ደመናውም ውስጠኛውን አደባባይ ሞላ። 4 የእግዚአብሔር ክብርም ከኪሩቤል ወጥቶ በቤቱ መድረክ ላይ ቆመ፤ ቤቱም በደመናው ተሞላ፤ አደባባዩም በእግዚአብሔር ክብር ፀዳል ተሞላ። 5 የኪሩቤልም የክንፎቻቸው ድምፅ ሁሉን የሚችል አምላክ እንደሚናገረው ያለ ድምፅ እስከ ውጭው አደባባይ ድረስ በሩቅ ይሰማ ነበር። 6 የተቀደሰ በፍታም የለበሰውን ሰው፥ “ከመንኰራኵሮቹ ከኪሩቤል መካከል እሳት ውሰድ” ብሎ በአዘዘው ጊዜ እርሱ ገብቶ በመንኰራኵር አጠገብ ቆመ። 7 ከኪሩቤል መካከልም አንዱ ኪሩብ እጁን በኪሩቤል መካከል ወደ አለው እሳት ዘርግቶ ከዚያ እሳት ወሰደ፤ የተቀደሰ በፍታም በለበሰው ሰው እጅ አኖረው፤ እርሱም ይዞ ወጣ። 8 ኪሩቤልንም አየሁ፤ ከክንፎቻቸውም በታች የሰው እጅ መሳይ አለ። 9 እኔም አየሁ፤ እነሆም በኪሩቤል አጠገብ አራት መንኰራኵሮች ነበሩ፤ አንዱ መንኰራኵር በአንዱ ኪሩብ፥ አንዱ መንኰራኵር በአንዱ ኪሩብ አጠገብ ነበረ። የመንኰራኵሮቹም መልክ እንደ ቢረሌ ድንጋይ ነበረ። 10 የአራቱም መልክ አንድ ይመስል ነበር፤ መልካቸውም በመንኰራኵር ውስጥ እንደ አለ መንኰራኵር ነበረ። 11 ሲሔዱም በአራቱ ጎድናቸው ይሄዱ ነበር። ሲሄዱም ወዲያና ወዲህ አይሉም ነበር፤ መጀመሪያው ወደሚያመለክትበት ስፍራ ይሄዱ ነበር፤ ሲሄዱም ወዲያና ወዲህ አይሉም ነበር። 12 ገላቸውም ሁሉ፥ ጀርባቸውም፥ እጆቻቸውም፤ ክንፎቻቸውም፥ መንኰራኵሮቹም፤ ለአራቱ የነበሩ መንኰራኵሮች በዙሪያቸው ዐይኖች ተሞልተው ነበር። 13 አራቱም መንኰራኵሮች እኔ እየሰማሁ ጌልጌል ተብለው ተጠሩ። 14 ለእያንዳንዱም አራት አራት ፊት ነበሩት፤ አንደኛው ፊት የኪሩብ ፊት፥ ሁለተኛውም የሰው ፊት፥ ሦስተኛው የአንበሳ ፊት፥ አራተኛውም የንስር ፊት ነበረ። 15 እነዚህም በኮቦር ወንዝ በእንስሶች አምሳል ያየኋቸው ኪሩቤል በረሩ። 16 ኪሩቤልም ሲሄዱ መንኰራኵሮቹ ከእነርሱ ጋር ተያይዘው ይሄዱ ነበር፤ ኪሩቤልም ይበሩ ዘንድ ክንፋቸውን ከምድር በሚያነሡ ጊዜ ከእነርሱ ጋር የተያያዘ መንኰራኵራቸው አይመለስም ነበር። 17 የሕይወት መንፈስ በውስጣቸው ነበርና እነዚህ ሲቆሙ እነዚያም ይቆሙ ነበር፤ እነዚህም ሲበርሩ፥ እነዚያ ከእነርሱ ጋር ይበርሩ ነበር። 18 የእግዚአብሔርም ክብር ከቤቱ መድረክ ላይ ወጥቶ በኪሩቤል ላይ ተቀመጠ። 19 ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ዘረጉ፤ እኔም እያየሁ ከምድር በረሩ፤ በወጡም ጊዜ መንኰራኵሮቹ በአጠገባቸው ነበሩ፤ፊት ለፊት በአለው በእግዚአብሔር ቤት መግቢያ በር ዳርቻ ቆሙ፤ የእስራኤልም አምላክ ክብር ከእነርሱ ጋራ በላያቸው ነበረ። 20 ይህ በኮቦር ወንዝ ከእስራኤል አምላክ በታች ያየሁት እንስሳ ነው፤ ኪሩቤልም እንደ ነበሩ ዐወቅሁ። 21 ለእያንዳንዱ አራት አራት ፊት፥ ለእያንዳንዱም አራት አራት ክንፍ ነበሩት፤ የሰውም እጅ አምሳያ ከክንፎቻቸው በታች ነበረ። 22 ፊቶቻቸውም በኮቦር ወንዝ ከእስራኤል አምላክ ክብር በታች ያየኋቸውን ፊቶች ይመስሉ ነበር፤ እነርሱና መልካቸውም እንዲሁ ነበረ፤ እያንዳንዱም አቅንቶ ወደ ፊት ይሄድ ነበር። |