ዘፀአት 35 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሰንበት አከባበር ሥርዐት 1 ሙሴም የእስራኤልን ልጆች ማኅበር ሁሉ ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፥ “ታደርጉ ዘንድ እግዚአብሔር ያለው ነገር ይህ ነው፤ 2 ስድስት ቀን ሥራህን ትሠራለህ፤ በሰባተኛው ቀን ታርፋለህ፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የዕረፍት ሰንበት ነው፤ የሚሠራበትም ሁሉ ይሙት። 3 በማደሪያዎቻችሁ ውስጥ በሰንበት ቀን እሳትን አታንድዱ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” ለድንኳኑ ሥራ የቀረበ መባ ( ዘፀ. 25፥1-9 ) 4 ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ አላቸው፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ያዘዘው ነገር ይህ ነው፤ 5 ከእናንተ ዘንድ ለእግዚአብሔር ቍርባንን አቅርቡ፤ የልብ ፈቃድ ያለው ከገንዘቡ የመጀመሪያውን ለእግዚአብሔር ያምጣ፤ ወርቅና ብር፥ ናስም፤ 6 ሰማያዊም፥ ሐምራዊም፥ ድርብ ቀይ ግምጃም፥ የተፈተለ በፍታም፥ የፍየል ጠጕርም፤ 7 ቀይ ቀለምም የገባበት የአውራ በግ ቍርበት፥ የአቆስጣም ቍርበት፥ የማይነቅዝም ዕንጨት፤ 8 ለመብራትም ዘይት፥ ለቅብዐት ሽቱን፥ ለማዕጠንት ዕጣንን፤ 9 የመረግድ ድንጋይና የተቀረጸ ድንጋይ፥ ለልብሰ መትከፍና ለልብሰ እንግድዓ የሚደረግ ፈርጥ ያምጣ። የድንኳኑ መገልገያ ዕቃዎች ( ዘፀ. 39፥34-43 ) 10 “በእናንተ ዘንድ ያለ፥ በልቡ ጥበበኛ የሆነ ሁሉ መጥቶ እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ ያድርግ። 11 ድንኳኑንም፥ አደባባዩንም፥ መደረቢያውንም፥ መያዣዎቹንም፥ ሳንቆቹንም፥ መወርወሪያዎቹንም፥ ምሰሶዎችንና እግሮቻቸውን፤ 12 የቃል ኪዳኑን ታቦትም፥ መሎጊያዎቹንም፥ የስርየት መክደኛውንም፥ መጋረጃውንም፤ 13 ገበታውንና መሎጊያዎቹንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ ኅብስተ ገጹንም፤ 14 መብራት የሚያበሩበትን መቅረዙን፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ ቀንዲሉንም፥ የመብራቱንም ዘይት፤ 15 የዕጣኑንም መሠዊያ፥ መሎጊያዎቹንም፥ የቅብዐቱንም ዘይት፥ ጣፋጩንም ዕጣን፥ ለማደሪያውም ደጃፍ የሚሆን የደጃፉን መጋረጃ፤ 16 ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያውን፥ የናሱንም መከታ፥ መሎጊያዎቹንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንም፥ መቀመጫውንም፤ 17 የአደባባዩን መጋረጆች፥ ምሰሶዎችንም፥ እግሮቻቸውንም፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ፤ 18 የማደሪያውን ካስማዎች፥ የአደባባዩንም ካስማዎች፥ አውታሮቻቸውንም፤ 19 በመቅደስ ውስጥ ለማገልገል በብልሃት የተሠሩትን ልብሶች፥ በክህነት ያገለግሉበት ዘንድ የተቀደሱትን የካህኑን የአሮንን ልብሶች፥ የልጆቹንም ልብሶች።” 20 የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ከሙሴ ዘንድ ወጡ። 21 ከእነርሱም ሰው ሁሉ እያንዳንዱ ልቡ እንዳነሣሣው፥ መንፈሱም እሺ እንዳሰኘው ለምስክሩ ድንኳን ሥራ ለማገልገያውም ሁሉ ለመቅደስ ልብስ ለእግዚአብሔር ስጦታ አመጡ። 22 ወንዶችና ሴቶችም ልባቸው እንደ ፈቀደ ማርዳዎችን፥ ሎቲዎችንም፥ ቀለበቶችንም፥ ድሪዎችንም፥ የወርቅ ጌጦችንም ሁሉ አመጡ፤ ሰዎችም ሁሉ የወርቅ ስጦታ ለእግዚአብሔር አቀረቡ። 23 ሰማያዊም፥ ሐምራዊም፥ ቀይ ግምጃም፥ የተፈተለ በፍታም፥ የፍየል ጠጕርም፥ ቀይ የአውራ በግ ቍርበትም፥ የአቆስጣ ቍርበትም ያላቸው ሰዎች ሁሉ አመጡ። 24 ስዕለት የተሳለ ሁሉ፥ የብርንም፥ የናስንም ስጦታ ለእግዚአብሔር ቍርባን አቀረበ፤ የማይነቅዝ ዕንጨት ያለው ሁሉ ለድንኳኑ ማገልገያ ለሚያስፈልገው ሥራ አመጣ። 25 በልባቸው ጥበበኞች የሆኑ ሴቶችም በእጃቸው ፈተሉ፤ የፈተሉትንም ሰማያዊውን፥ ሐምራዊውንም፥ ቀዩንም ግምጃ፥ ጥሩውንም በፍታ አመጡ። 26 ልባቸውም በጥበብ ያስነሣቸው ሴቶች ሁሉ የፍየልን ጠጕር ፈተሉ። 27 አለቆችም የመረግድ ድንጋይና የተቀረጸ ድንጋይን ለልብሰ መትከፍና ለልብሰ እንግድዓ የሚገቡትንም ፈርጦችን፥ 28 ለመብራትም፥ ለቅብዐት ዘይትም፥ ለጣፋጭ ዕጣንም ሽቱንና ዘይትን አመጡ። 29 ከእስራኤል ልጆችም ያመጡ ዘንድ ልባቸው ያስነሣቸው ወንዶችና ሴቶች ሁሉ ሙሴ ይሠራ ዘንድ እግዚአብሔር ላዘዘው ሥራ ሁሉ ለእግዚአብሔር ስጦታ በፈቃዳቸው አመጡ። ባስልኤልና ኤልያብ ( ዘፀ. 31፥1-11 ) 30 ሙሴም የእስራኤልን ልጆች አላቸው፥ “እዩ፥ እግዚአብሔር ከይሁዳ ነገድ የሆነውን የሆር የልጅ ልጅ፥ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠራው። 31 በሥራ ሁሉ ብልሃት፥ በጥበብም፥ በማስተዋልም፥ በዕውቀትም የእግዚአብሔርን መንፈስ ሞላበት፤ 32 በአናጺዎች ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ፥ የጥበብንም ሥራ ያስተውል ዘንድ፥ በወርቅና በብር፥ በናስም ይሠራ ዘንድ፥ 33 በፈርጥ የሚሆነውን የዕንቍ ድንጋይ ይቀርጽ ዘንድ፥ ዕንጨቱንም ይጠርብ ዘንድ፥ የብልሃት ሥራውንም ሁሉ ይሠራ ዘንድ። 34 እርሱና የዳን ነገድ የሆነው የአሒሳሚክ ልጅ ኤልያብ ያስተምሩ ዘንድ በልባቸው አሳደረባቸው። 35 በአንጥረኛ፥ በብልህ ሠራተኛም፥ በሰማያዊና በሐምራዊ፥ በቀይም ግምጃ፥ በጥሩ በፍታም በሚሠራ ጠላፊ፥ በሸማኔም ሥራ የሚሠራውን፥ ማናቸውንም ሥራና በብልሃት የሚሠራውን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ በእነርሱ ልብ ጥበብን ሞላ። |