本书并非出自上帝启示,且不属于基督教正典或犹太教塔纳赫的一部分。仅为历史与研究目的而展示。 查看完整说明 መጽሐፈ ባሮክ 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ኢየሩሳሌም ሆይ! የኀዘንሽንና የመከራሽን ልብስ ከአንቺ አውልቂው፤ ለዘለዓለም ከእግዚአብሔር ያገኘሽውን የክብር ጌጥሽንም ልበሺ። 2 ከእግዚአብሔር ዘንድ የጽድቅ መጐናጸፊያሽን ተጐናጸፊ፤ የዘለዓለማዊውን አምላክ የክብር ዘውድሽንም በራስሽ ላይ ተቀዳጂ። 3 እግዚአብሔር ከሰማይ በታች ላሉ ሁሉ ብርሃንሽን ገልጧልና። 4 ስምሽም በእግዚአብሔር ዘንድ ለዘለዓለም የጽድቅ ሰላምና እግዚአብሔርን የመፍራት ክብር ተብሎ ይጠራል። 5 ኢየሩሳሌም ሆይ! ተነሥተሽ፥ በላይኛውም ቦታ ቁሚ፤ ወደ ምሥራቅም ተመልከቺ፤ ከምዕራብና ከምሥራቅም በቅዱሱ ቃል ልጆችሽ እንደ ተሰበሰቡ እዪ፤ እግዚአብሔርንም በማሰብ ደስ ይላቸዋል። 6 ከአንቺም በእግር ወጡ፤ ጠላቶቻቸውም ወሰዷቸው፤ እግዚአብሔር ግን እንደ ንጉሥ ዙፋን በክብር ተሸክመው ወደ አንቺ እንዲያመጧቸው ያደርጋል። 7 እግዚአብሔርም ረጃጅሞች ተራሮች ሁሉ ዝቅ ይሉ ዘንድ፥ ጐድጓዳውም ሁሉ ይሞላ ዘንድ፥ ምድርም ይስተካከል ዘንድ፥ እስራኤልም በእግዚአብሔር ክብር በጥርጊያው ጐዳና ይሄድ ዘንድ አዘዘ። 8 እስራኤልን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ዛፍ ሁሉ፥ በጎ መዓዛ ያለው ዕንጨትም ሁሉ ይጋርዳቸዋልና። 9 እግዚአብሔር እስራኤልን በደስታና፥ በክብሩ ብርሃን፥ በምሕረቱና ከእርሱ በሆነች በጽድቁም ያመጣቸዋልና። |