አሞጽ 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእስራኤል ቅጣት 1 ጽዮንን ለሚንቁ፥ በሰማርያም ተራራ ለሚታመኑ ሰዎች ወዮላቸው፤ የአሕዛብን አለቆች ለቀሙአቸው። 2 የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ወደ ካልኔ ተሻግራችሁ ተመልከቱ፤ ከዚያም ወደ ኤማትራባ እለፉ፤ ከዚያም ወደ ፍልስጥኤም ጌት ውረዱ፤ እነርሱ ከእነዚህ መንግሥታት ይበረታሉ፤ ድንበራቸውም ከድንበራቸው ይሰፋልና። 3 ክፉ ቀንን ለሚፈልጓት፥ የሐሰት ሰንበታትን ለሚያቀራርቡና አንድ ለሚያደርጉ፥ 4 ከዝሆን ጥርስ በተሠራ አልጋ ላይ ለሚተኙ፥ በምንጣፋቸው ደስ ለሚሰኙ፥ ከበጎችም መንጋ ጠቦትን፥ ከጋጥም ውስጥ ጥጃን ለሚመገቡ፥ 5 ከበገናው ድምፅ ጋር አስተባብረው ለሚያጨበጭቡ ሰዎች፤ ይኸውም የማያልፍ ለሚመስላቸውና እንደሚያመልጣቸው ለማያውቁ፤ 6 በጽዋ የቀላ ወይን ለሚጠጡ፥ እጅግ በአማረ ሽቱም ለሚቀቡ፥ በዮሴፍ ስብራት ለማያስቡ ወዮላቸው። 7 ስለዚህ ከአለቆቻቸው አስቀድመው ይማረካሉ፤ ሯጮች የሚሆኑ የኤፍሬም ፈረሶችም ያልቃሉ። 8 ጌታ እግዚአብሔር፥ “የያዕቆብን ትዕቢት አረክሳለሁ፤ ሀገሮቹንም ጠላሁ፤ ከተሞቹንም ከሚኖሩባቸው ሰዎች ጋር አጠፋለሁ” ብሎ በራሱ ምሎአልና። 9 እንዲህም ይሆናል፤ ዐሥር ሰዎች በአንድ ቤት ውስጥ ቢቀሩ እነርሱ ይሞታሉ፤ የቀሩት ግን ይተርፋሉ። 10 አጥንቶቻቸውንም ከቤት ያወጡ ዘንድ ቤተሰቦቻቸው በወሰዱአቸው ጊዜ፥ ቤት ጠባቂውን በአንተ ዘንድ የቀረ አለን? በአለው ጊዜ እርሱ የለም ይላል። ያም የእግዚአብሔርንም ስም እንዳትጠራ ዝም በል ይለዋል። 11 እነሆም እግዚአብሔር ያዝዛል፤ ታላቁንም ቤት በማፍረስ፥ ታናሹንም ቤት በመሰባበር ይመታል። 12 ፍርድን ወደ ቍጣ፥ የእውነትንም ፍሬ ወደ እሬት ለውጣችኋልና፥ በውኑ ፈረሶች በጭንጫ ላይ ይሮጣሉን? ወይስ በሬዎች በዚያ ላይ ያርሳሉን? 13 በከንቱ ነገር ደስ የሚላችሁ በኀይላችን ቀንዶችን አበቀልን የምትሉ አይደለምን? 14 “የእስራኤል ቤት ሆይ እነሆ እኔ የሚያስጨንቋችሁን ሕዝብ አስነሣባችኋለሁ፥” ይላል የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር፤ እነርሱም ከሐማት መግቢያ ጀምረው እስከ ዐረባ ወንዝ ድረስ ትገቡ ዘንድ አይፈቅዱላችሁም። |