2 ዜና መዋዕል 35 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ንጉሡ ኢዮስያስ ለእግዚአብሔር የፋሲካን በዓል እንደ አከበረ ( 2ነገ. 23፥21-23 ) 1 ኢዮስያስም ለአምላኩ ለእግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ፋሲካ አደረገ፤ በመጀመሪያውም ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካውን በግ አረዱ። 2 ካህናቱንም በየሥርዐታቸው አቆመ፤ በእግዚአብሔርም ቤት ያገለግሉ ዘንድ አጸናቸው። 3 በእስራኤልም ሁሉ መሥራት የሚችሉትን ሌዋውያን ራሳቸውን ለእግዚአብሔር እንዲያነጹና ቅድስቲቱንም ታቦት የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በሠራው ቤት ውስጥ እንዲያኖሩ አዘዛቸው። ንጉሡም ኢዮስያስ አለ፥ “በትከሻችሁ የምትሸከሙት አንዳች ነገር አይኑር፤ አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርንና ሕዝቡን እስራኤልን አገልግሉ፤ 4 የእስራኤልም ንጉሥ ዳዊት እንደ አዘዘ፥ ልጁም ሰሎሞን እንደ አዘዘ በየሰሞናችሁና በየአባቶቻችሁ ቤቶች ተዘጋጁ፤ 5 እንደ ሕዝቡም ልጆች እንደ ወንድሞቻችሁ በየአባቶች ቤቶች አከፋፈል በመቅደሱ ቁሙ፤ እንዲሁም ለሌዋውያን በየአባቶቻቸው ቤት አከፋፈል ይሁን፤ 6 የፋሲካውንም በግ እረዱ፤ እናንተም ተቀደሱ፥ እግዚአብሔርም በሙሴ እጅ የተናገረውን ቃል ታደርጉ ዘንድ ለወንድሞቻችሁ አዘጋጁ።” 7 ኢዮስያስም ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን በዚያ ለነበሩት ለሕዝቡ ልጆች ከመንጋው ሠላሳ ሺህ የበግና የፍየል ጠቦቶች፥ ሦስት ሺህም ወይፈኖች ሰጣቸው፤ እነዚህም ከንጉሡ ሀብት ነበሩ። 8 አለቆቹም ለሕዝቡና ለካህናቱ፥ ለሌዋውያኑም በፈቃዳቸው ሰጡ፤ የእግዚአብሔርም ቤት አለቆች፥ ኬልቅያስ፥ ዘካርያስ፥ ኢዮሔል፥ ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን ሁለት ሺህ ስድስት መቶ በጎችንና ፍየሎችን፥ ሦስት መቶም በሬዎችን ለካህናቱ ሰጡ። 9 የሌዋውያኑም አለቆች ኮኒንያስ በንያስም፥ ወንድሞቹም ሰማዕያስና ናትናኤል፥ ሰብንያስ፥ ኢዮሄል፥ ኢዮዛብድ ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን አምስት ሺህ በጎችን፥ አምስት መቶም በሬዎችን ለሌዋውያን ሰጡ። 10 አገልግሎቱም ተዘጋጀ፤ ካህናቱም በየስፍራቸው፥ ሌዋውያኑም በየክፍላቸው እንደ ንጉሡ ትእዛዝ ቆሙ። 11 የፋሲካውንም በግ አረዱ፤ ካህናቱም ከእጃቸው የተቀበሉትን ደም ረጩ፤ ሌዋውያኑም ቍርበቱን ገፈፉ። 12 በሙሴም መጽሐፍ እንደ ተጻፈ ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ዘንድ በየአባቶቻቸው ቤቶች እንደ ክፍላቸው ለሕዝቡ ልጆች እንዲሰጡ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለዩ። እንዲሁም በበሬዎቹ አደረጉ። 13 የፋሲካውንም በግ እንደ ሙሴ ሥርዐት በእሳት ጠበሱ፤ የተቀደሰውንም ቍርባን በምንቸትና በሰታቴ፥ በድስትም ቀቀሉ፤ ተከናወነላቸውም፤ ለሕዝቡም ልጆች ሁሉ በፍጥነት አደረሱ። 14 ከዚያም በኋላ ለራሳቸውና ከእነርሱ ጋር ላሉ ለካህናቱ አዘጋጁ፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ስቡን ለማቅረብ እስከ ሌሊት ድረስ ይሠሩ ነበርና ስለዚህ ሌዋውያን ለራሳቸውና ለወንድሞቻቸው ለአሮን ልጆች ለካህናቱ አዘጋጁ። 15 የአሳፍም ልጆች መዘምራን እንደ ዳዊት፥ እንደ አሳፍም፥ እንደ ኤማንም የንጉሡም ባለ ራእይ እንደ ነበረው እንደ ኤዶትም ትእዛዝ በየስፍራቸው ነበሩ፤ በረኞቹም በሮቹን ሁሉ ይጠብቁ ነበር፤ ወንድሞቻቸውም ሌዋውያን ያዘጋጁላቸው ነበርና ከአገልግሎታቸው ይርቁ ዘንድ አያስፈልጋቸውም ነበር። 16 እንደ ንጉሡም እንደ ኢዮስያስ ትእዛዝ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ፥ ፋሲካውንም ያደርጉ ዘንድ፥ የእግዚአብሔር አገልግሎት ሁሉ በዚያ ቀን ተዘጋጀ። 17 የተገኙትም የእስራኤል ልጆች በዚያ ቀን ፋሲካውን፥ ሰባት ቀንም የቂጣውን በዓል አደረጉ። 18 ከነቢዩም ከሳሙኤል ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ያለ ፋሲካ በእስራኤል ዘንድ ከቶ አልተደረገም፤ ከእስራኤልም ነገሥታት ሁሉ ኢዮስያስና ካህናቱ፥ ሌዋውያኑም፥ በዚያም የተገኙ የይሁዳና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩት እንዳደረጉት ያለ ፋሲካ ያደረገ የለም። 19 ይህም ፋሲካ ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት ተደረገ። 19 ‘ሀ’ ንጉሡ ኢዮስያስ ካህኑ ኬልቅያስ በእግዚአብሔር ቤት ባገኘው መጽሐፍ የተጻፉትን ቃላት ሁሉ ለመጠበቅ አስማተኞችንና ጠንቋዮችን፥ ሟርተኞችንና በኢየሩሳሌም ምድርና በይሁዳ የሚገኙትን ምስሎችና ቃሪያሲም የተባሉ ጣዖታትን በእሳት አቃጠለ። 19 ‘ለ’ እንደ ሙሴ ሕግ ሁሉ በፍጹም ልቡ፥ በፍጹም ነፍሱ፥ በፍጹም ኀይሉ ከእርሱ በፊት ከነበሩት ወደ እግዚአብሔር የተመለሰ የሚመስለው ሰው አልነበረም። ከእርሱም በኋላ የሚመስለው አልተነሣም። 19 ‘ሐ’ ነገር ግን እግዚአብሔር ንጉሥ ምናሴ በይሁዳ ላይ በአደረገውና በአነሣሣው ጥፋት ሁሉ ከአስከተለው ታላቅ ቍጣ አልተመለሰም። 19 ‘መ’ እግዚአብሔርም አለ፥ “እስራኤልን እንዳራቅሁ ይሁዳን ከፊቴ አርቃለሁ። የመረጥኋትንም ከተማ ኢየሩሳሌምንና ስሜ በዚያ ይጠራበታል ያልሁትን ቤት እጥላለሁ።” 20 ከዚህም ሁሉ በኋላ፥ ኢዮስያስም ቤተ መቅደሱን ካሰናዳ በኋላ፥ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ኒካዑ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ የአሦርን ንጉሥ ይዋጋ ዘንድ ወጣ፤ ኢዮስያስም ሊጋጠመው ወጣ። 21 እርሱም፥ “የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? በምዋጋበት በሌላ ቤት ላይ ነው እንጂ በአንተ ላይ ዛሬ አልመጣሁም፤ እግዚአብሔርም እንድቸኩል አዝዞኛል፤ ከእኔ ጋር ያለው እግዚአብሔር እንዳያጠፋህ ተጠንቀቅ” ብሎ መልእክተኞችን ላከበት። 22 ኢዮስያስ ግን ይዋጋው ዘንድ ተጽናና እንጂ ፊቱን ከእርሱ አልመለሰም፤ በእግዚአብሔርም አፍ የተነገረውን የኒካዑን ቃል አልሰማም፤ በመጊዶንም ሸለቆ ይዋጋ ዘንድ መጣ። 23 ቀስተኞቹም ንጉሡን ኢዮስያስን ወጉት፤ ንጉሡም ብላቴኖቹን፥ “እጅግ ቈስያለሁና ከሰልፉ ውስጥ አውጡኝ” አላቸው። 24 ብላቴኖቹም ከሰረገላው አውርደው ለእርሱ በነበረው በሁለተኛው ሰረገላ ውስጥ አስቀመጡት፤ ወደ ኢየሩሳሌምም አመጡት፤ እርሱም በዚያ ሞተ፤ በአባቶቹም መቃብር ተቀበረ፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌምም ሁሉ ለኢዮስያስ አለቀሱ። 25 ኤርምያስም ለንጉሡ ለኢዮስያስ የልቅሶ ግጥም ገጠመለት፤ እስከ ዛሬም ድረስ ወንዶችና ሴቶች መዘምራን ሁሉ በልቅሶ ግጥማቸው ስለ ኢዮስያስ ይናገሩ ነበር፤ ይህም በእስራኤል ሁሉ ዘንድ ወግ ሆኖ በልቅሶ ግጥም ተጽፎአል። 26 የቀሩትም የኢዮስያስ ነገሮች፥ በእግዚአብሔርም ሕግ እንደ ተጻፈ ያደረገው ቸርነት፥ 27 የፊተኛውና የኋለኛውም ነገሩ፥ እነሆ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል። |