2 ዜና መዋዕል 33 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የይሁዳ ንጉሥ የምናሴ ዘመነ መንግሥት ( 2ነገ. 21፥1-9 ) 1 ምናሴም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የዐሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አምሳ አምስት ዓመት ነገሠ። 2 እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳወጣቸው እንደ አሕዛብ ያለ ርኵሰት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አደረገ። 3 አባቱም ሕዝቅያስ ያፈረሳቸውን የኮረብታ መስገጃዎች መልሶ ሠራ፤ ለበዓሊምም መሠዊያ ሠራ፤ የማምለኪያ ዐፀዶችንም ተከለ፤ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ሰገደ፤ አመለካቸውም። 4 እግዚአብሔርም፥ “ስሜ በኢየሩሳሌም ለዘለዓለም ይኖራል” ባለው በእግዚአብሔር ቤት የጣዖት መሠዊያዎችን ሠራ። 5 በእግዚአብሔርም ቤት በሁለቱ አደባባዮች ላይ ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ መሠዊያዎችን ሠራ። 6 በሄኖምም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ልጆቹን በእሳት አቃጠለ፤ ሞራ ገላጭም ሆነ፤ አስማትም አደረገ። መተተኛም ነበረ፤ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችንም ሰበሰበ፤ ያስቈጣውም ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገርን አደረገ። 7 እግዚአብሔርም ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን፥ “በዚህ ቤትና ከእስራኤል ነገድ ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘለዓለም አኖራለሁ፤ 8 ያዘዝኋቸውንም ሁሉ፥ በሙሴ የተሰጠውን ሕግና ሥርዐት ፍርድንም ሁሉ ቢያደርጉ ቢጠብቁም፥ ለአባቶቻችሁ ከሰጠኋት ምድር የእስራኤልን እግር እንደ ገና አላርቅም” ባለበት በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የሠራውን ጣዖትና የተቀረጸውን ምስል አቆመ። 9 ምናሴም እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ ክፉ ይሠሩ ዘንድ በይሁዳና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን አሳተ። 10 እግዚአብሔርም ምናሴንና ሕዝቡን ተናገራቸው፤ ግን አልሰሙትም። 11 ስለዚህም እግዚአብሔር የአሦርን ንጉሥ ሠራዊት አለቆች አመጣባቸው፤ ምናሴንም በዛንጅር ያዙት፤ በሰንሰለትም አስረው ወደ ባቢሎን ወሰዱት። 12 በተጨነቀም ጊዜ አምላኩን እግዚአብሔርን ፈለገ፤ በአባቶቹም አምላክ ፊት ሰውነቱን እጅግ አዋረደ። 13 የንጉሡ የሕዝቅያስ ልጅ ምናሴም ጸለየ እንዲህም አለ፦ የምናሴ ጸሎት 14 “ዓለምን ሁሉ የምትገዛ፥ የአባቶቻችን የአብርሃምና የይስሐቅ፥ የያዕቆብም የጻድቃን ልጆቻቸውም አምላክ ሆይ፥ ሰማይንና ምድርን ከዓለሞቻቸው ጋር የፈጠርህ፥ 15 በቃልህ ትእዛዝ ባሕርን የገሠጽሃት፥ ቀላዮችን የዘጋህ፥ የሚያስፈራውንም የወሰንህ፥ 16 ይኸውም በተመሰገነው ስምህ ነው፤ ኀይልህ ከመገለጡ የተነሣ ሁሉ የሚርድና የሚንቀጠቀጥ፤ 17 ለክብርህ ከፍተኛነት ፍጻሜ የለውምና፥ የቍጣህም መቅሠፍት በኃጥአን ላይ ግሩም ነው። 18 በትእዛዝህ ለሚሆነው ይቅርታ ስፍር ቍጥር የለውም፤ ገናና እግዚአብሔር አንተ ብቻ ነህና፥ ይቅር ባይ፥ ከቍጣ የራቅህ፥ ይቅርታህ የበዛ፥ የሰውንም ኀጢአት የምታስተሰርይ አንተ ነህ። 19 አሁንም አቤቱ፥ የጻድቃን አምላካቸው አንተ ነህ። ንስሓን የፈጠርህ ለጻድቅ ሰው አይደለምና፥ አንተን ላልበደሉ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም አይደለምና፤ ነገር ግን የእኔን የኃጥኡን ንስሓ ወደ ማየት ተመለስ። 20 ቍጥሩ ከባሕር አሸዋ የሚበልጥ በደልን በድያለሁና፥ ኀጢአቴም ብዙ ነውና፤ ከበደሌም ብዛት የተነሣ ቀና ብዬ የሰማይን ርዝመት አይ ዘንድ አገባቤ አይደለም። ሰውነቴን ከኀጢአቴ አሳርፋት ዘንድ በብረት ቀፎ ደከምሁ፤ በዚህም ደግሞ አላረፍሁም፤ መዓትህን አነሣሥቻለሁና፥ 21 ከንቱውን ስመለከት የማይጠቅመኝንም ነገር ሳበዛ በፊትህ ክፉ ሥራን ሠርቻለሁና። 22 አሁንም ቸርነትህን እየለመንሁ በልቤ ጕልበት እሰግዳለሁ። 23 አቤቱ፥ ጌታዬ፥ ፈጽሜ በደልሁ፤ ኀጢአቴንም አምናለሁ። 24 አንተንም እማልዳለሁ፤ እለምንህማለሁ፤ ይቅር በለኝ፤ አቤቱ፥ ይቅር በለኝ፤ ለኀጢአቴም አሳልፈህ አትስጠኝ። 25 ለዘለዓለም ክፋቴን አትመልከትብኝ፤ በምድር ጥልቀትም አትበቀለኝ፤ አቤቱ፥ በንስሓ ለሚመለሱ ሰዎች፥ አምላካቸው አንተ ነህና፥ ቸርነትህ በእኔ ላይ ይገለጥ፤ መዳን የማይገባኝ ሲሆን በይቅርታህ ብዛት አዳንኸኝ። 26 በየጊዜውና በሕይወቴ ዘመን ሁሉ አመሰግንሃለሁ። የሰማያት ኀይል ሁሉ አንተን ያመሰግናሉና፤ ለዘለዓለምም ምስጋና ለአንተ ይገባል፤” አሜን። እግዚአብሔርም ምናሴ ባለማወቅ ከአደረገው ክፉ ሥራው እንደ ተመለሰ ባየ ጊዜ ይቅር አለው፤ ጸሎቱንም ሰማው፤ ልመናውንም ተቀበለው፤ ወደ መንግሥቱም ወደ ኢየሩሳሌም መለሰው፤ ምናሴም እርሱ አምላክ እንደ ሆነ ዐወቀ። 27 ከዚህ በኋላ በዳዊት ከተማ በስተውጭው ከግዮን ሰሜናዊ ምዕራብ በሸለቆው ውስጥ እስከ ዓሣ በር መግቢያ ድረስ ቅጥር ሠራ። እስከ ዖፌልም አዞረበት፤ እጅግም ከፍ አደረገው፤ በተመሸጉትም በይሁዳ ከተሞች ሁሉ የጭፍራ አለቆችን አኖረ። 28 እንግዶችንም አማልክትና ጣዖታቱንም ከእግዚአብሔር ቤት አራቀ፤ የእግዚአብሔርም ቤት ባለበት ተራራ ላይና በኢየሩሳሌም የሠራቸውን መሠዊያዎች ሁሉ ወስዶ ከከተማዪቱ በስተውጭ ጣላቸው። 29 የእግዚአብሔርንም መሠዊያ ደግሞ አደሰ፤ የደኅነትንና የምስጋናንም መሥዋዕት ሠዋበት፤ የይሁዳም ሕዝብ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ አዘዘ። 30 ሕዝቡ ግን ከአምላካቸው ከእግዚአብሔር ፈጽመው ርቀው ገና በኮረብታዎች ላይ ይሠዉ ነበር፥ 31 የምናሴም የቀሩት ነገሮች፥ ወደ አምላኩም የጸለየው ጸሎት፥ በእስራኤልም አምላክ በእግዚአብሔር ስም የነገሩት የነቢያት ቃል፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል። 32 ደግሞም ጸሎቱን፥ እግዚአብሔር እንደ ሰማው፥ ኀጢአቱና መተላለፉ ሁሉ፥ ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ኮረብታውን የሠራበት ዐፀዱንና የተቀረጹትንም ምስሎች የተከለበት ስፍራ፥ እነሆ፥ በባለ ራእዩ የታሪክ መጽሐፍ ተጽፈዋል። 33 ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በቤቱም አትክልት ቦታ ቀበሩት፤ ልጁም አሞጽ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። 34 አሞጽ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ ሁለት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሁለት ዓመት ነገሠ። 35 አባቱም ምናሴ እንዳደረገ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ አሞጽም አባቱ ምናሴ ለሠራቸው ለተቀረጹት ምስሎች ሁሉ ሠዋ፤ አመለካቸውም። 36 አባቱም ምናሴ ሰውነቱን እንዳዋረደ በእግዚአብሔር ፊት ሰውነቱን አላዋረደም፤ ነገር ግን አሞጽ መተላለፉን እጅግ አበዛ። 37 አገልጋዮቹም ተነሡበት፤ በቤቱም ገደሉት። 38 የሀገሩ ሕዝብ ግን በንጉሡ በአሞጽ ላይ የተነሡትን ሁሉ ገደሉ፤ የሀገሩም ሕዝብ ልጁን ኢዮስያስን በእርሱ ፋንታ አነገሡ። |