2 ዜና መዋዕል 31 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ይህም ሁሉ በተፈጸመ ጊዜ በይሁዳ ከተሞች የተገኙ እስራኤል ሁሉ ወጥተው ዐምዶቹን ሰበሩ፤ ዐፀዶችንም ኮረብታዎችንም አፈረሱ፤ መሠዊያውንም አጠፉ። በይሁዳና በብንያምም ሁሉ ደግሞም በኤፍሬምና በምናሴ የነበሩትን ፈጽመው እስከ ዘለዓለሙ አጠፉአቸው። የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ወደ ርስታቸውና ወደ ከተሞቻቸው ተመለሱ። 2 ሕዝቅያስም የካህናትንና የሌዋውያንን ሰሞን በየክፍላቸውና በየአገልግሎታቸው፥ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ በሮች የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ያቀርቡና ያገለግሉ ዘንድ፥ ያመሰግኑም፥ ያከብሩም ዘንድ ካህናቱንና ሌዋውያኑን መደበ። 3 በእግዚአብሔርም ሕግ እንደ ተጻፈ በጥዋትና በማታ በሰንበታቱም፥ በመባቻዎቹም፥ በበዓላትም ለሚቀርበው ለሚቃጠለው መሥዋዕት ንጉሡ ከገንዘቡ የሚከፍለውን ወሰነ። 4 በእግዚአብሔርም ቤት ለአገልግሎት እንዲጸኑ ለካህናቱና ለሌዋውያን ድርሻቸውን ይሰጡ ዘንድ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ሕዝብ አዘዘ። 5 ይህንም ነገር እንዳዘዘ የእስራኤል ልጆች የእህሉንና የወይኑን፥ የዘይቱንና የማሩንም፥ የእርሻውንም ፍሬ መጀመሪያ ሁሉ ሰጡ፤ የሁሉንም ዐሥራት አብዝተው አቀረቡ። 6 በይሁዳም ከተሞች የሚኖሩ የእስራኤልና የይሁዳ ልጆች የበሬዉንና የበጉን፥ የፍየሉንም ዐሥራት አመጡ፤ ለአምላካቸው ለእግዚአብሔርም ቀደሱት፤ ከምረውም አኖሩት። 7 በሦስተኛውም ወር መከመር ጀመሩ፤ በሰባተኛውም ወር ጨረሱ። 8 ሕዝቅያስና አለቆቹም መጥተው ክምሩን ባዩ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገኑ። ሕዝቡን እስራኤልንም ባረኩ። 9 ሕዝቅያስም ካህናቱንና ሌዋውያኑን ስለ ክምሩ ጠየቀ። 10 ከሳዶቅም ወገን የሆነ ታላቁ ካህን ዓዛርያስ፥ “ሕዝቡ መባውን ወደ እግዚአብሔር ፊት ማቅረብ ከጀመረ ወዲህ በልተናል፤ ጠጥተናልም፤ ጠግበናልም፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን ባርኮአልና ብዙ ተርፎአል፤ ከዚህም ገና ብዙ ተረፈ” ብሎ ተናገረ። 11 ሕዝቅያስም ለእግዚአብሔር ቤት ጎተራ ያዘጋጁ ዘንድ አዘዘ፤ እነርሱም አዘጋጁ። 12 መባኡንና ዐሥራቱን፥ የተቀደሱትንም በእምነት ወደዚያ አገቡ። ሌዋዊውም ኮክንያስ ተሾመባቸው፥ ወንድሙም ሰሜኢ በማዕርግ ሁለተኛ ነበረ፤ 13 ንጉሡም ሕዝቅያስና የእግዚአብሔር ቤት አለቃ ዓዛርያስ እንደ አዘዙ ኢዮኤል፥ ዓዛዝያ፥ አናኤት፥ ኡሳሄል፥ ኢያሪሞት፥ ኢዮዛብድ፥ ኤልሄል፥ ሰማኪያ፥ መሐት፥ በናያስና ልጆቹ፥ ከኮክንያስና ከወንድሙ ከሰሜኢ እጅ በታች ተቈጣጣሪዎች ነበሩ። 14 የሌዋዊውም የይምላእ ልጅ የምሥራቁ ደጅ በረኛ ቆሬ የእግዚአብሔርን መባና የተቀደሱትን ነገሮች እንዲያካፍል ሕዝቡ በፈቃዳቸው ለእግዚአብሔር በአቀረቡት ላይ ተሾመ። 15 በካህናቱም ከተሞች ለታላላቆችና ለታናናሾች ወንድሞቻቸው በየሰሞናቸው ክፍላቸውን በእምነት ይሰጡ ዘንድ ኤዶም፥ ብንያስ፥ ኢያሱ፥ ሴሚ፥ አማርያ፥ ኮክንያስ ከእጁ በታች ነበሩ። 16 ከሦስትም ዓመት ወደ ላይ ላሉ በየሰሞናቸው ለሥራቸውና ለአገልግሎታቸው ዕለት ዕለት ወደ እግዚአብሔር ቤት ለሚገቡ ወንዶች ሁሉ፥ 17 በየአባቶቻቸውም ቤት ለተቈጠሩ ካህናት፥ ከሃያ ዓመትም ወደ ላይ ላሉ በየሥርዐታቸውና በየሰሞናቸው ለተቈጠሩ ሌዋውያን፥ 18 በማኅበራቸውም ሁሉ በየትውልዳቸው ለተቈጠሩ ለሚስቶቻቸው፥ ለወንዶችና ለሴቶች ልጆቻቸውም ይሰጡ ነበር፤ በእምነት ፈጽመው ተቀድሰዋልና። 19 ክህነት ለሚገባቸው ለአሮን ልጆች ለካህናቱ፥ በከተሞቻቸውም ዙሪያ ባሉ መሰማሪያዎችና በሌሎችም ከተሞች ላሉ ለወንዶች ሁሉ፥ ከሌዋውያን ጋራ ለተቈጠሩ ሰዎችም ሁሉ ከፍለው ይሰጡ ዘንድ በስም የተጠሩ ሰዎች ነበሩ። 20 ሕዝቅያስም በይሁዳ ሁሉ እንዲህ አደረገ፤ በአምላኩም በእግዚአብሔር ፊት መልካምንና ቅን ነገርን እውነትንም አደረገ። 21 ስለ እግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት በጀመረው ሥራ ሁሉ፥ በሕጉና በትእዛዙም አምላኩን እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡ ፈለገው፤ ሥራውም ሁሉ ተከናወነለት። |