2 ዜና መዋዕል 28 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የይሁዳ ንጉሥ የአካዝ ዘመነ መንግሥት ( 2ነገ. 16፥1-4 ) 1 አካዝም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ዐሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ፤ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አላደረገም። 2 ነገር ግን በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ ደግሞም ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎች ሠራ። 3 ደግሞም በሄኖም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ለምስሉ ሠዋ፤ እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳሳደዳቸው እንደ አሕዛብም ክፉ ልማድ ልጆቹን በእሳት አቃጠለ። 4 በኮረብታው መስገጃዎችና በተራሮች ላይ በለመለመውም ዛፍ ሁሉ በታች ያጥን ነበር። 5 ስለዚህ አምላኩ እግዚአብሔር በሶርያ ንጉሥ እጅ አሳልፎ ሰጠው፤ እርሱም መታው፤ ከእርሱም ብዙ ምርኮኞችን ወሰደ፤ ወደ ደማስቆም አመጣው። ደግሞም በእስራኤል ንጉሥ እጅ አሳልፎ ሰጠው፤ እርሱም በታላቅ አመታት መታው። 6 የአባቶቻቸውንም አምላክ እግዚአብሔርን ትተው ነበርና የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በአንድ ቀን ከይሁዳ ጽኑዓን የነበሩ መቶ ሃያ ሺህ ሰልፈኞችን ገደለ፤ 7 ከኤፍሬም ወገን የነበረው ኀያል ሰው ዝክሪም የንጉሡን ልጅ ማዓሥያንና የቤቱን አዛዥ ዓዝሪቃምን፥ ለንጉሡም በማዕርግ ሁለተኛ የሆነውን ሕልቃናን ገደለ። 8 የእስራኤል ልጆች ከወንድሞቻቸው ሦስት መቶ ሺህ ሴቶችን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ማረኩ፤ እጅግም ምርኮ ከእነርሱ ወስደው ወደ ሰማርያ አገቡ። 9 በዚያም ዖዴድ የተባለ የእግዚአብሔር ነቢይ ነበረ፤ ወደ ሰማርያም የሚመጣውን ጭፍራ ሊገናኘው ወጣ፤ እንዲህም አላቸው፤ “እነሆ፥ የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር ይሁዳን ስለ ተቈጣ በእጃችሁ አሳልፎ ሰጣቸው፤ እናንተም ወደ ሰማይ በሚደርስ ቍጣ ገደላችኋቸው። 10 አሁንም የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ልጆች ባሪያዎች አድርገን እንግዛ ትላላችሁ፤ የፈጣሪያችሁ የእግዚአብሔር ምስክር የምሆን እኔም ከእናንተ ጋር ያለሁ አይደለምን? 11 አሁንም ስሙ፤ የእግዚአብሔር ቍጣ በላያችሁ ነድዶአልና ከወንድሞቻችሁ የወሰዳችኋቸውን ምርኮኞች መልሱ።” 12 ደግሞም ከኤፍሬም ልጆች አለቆች የአናን ልጅ ዓዛርያስ፥ የመስለሞት ልጅ በራክያ፥ የሳሎም ልጅ ሕዝቅያስ፥ የአዳሊ ልጅ አማስያ ከሰልፍ የተመለሱትን ተቃወሙአቸው። 13 “ደግሞም በእግዚአብሔር ፊት በእኛ ላይ በደል ታመጡብናላችሁና፥ ኀጢአታችንንና በደላችንን ታበዙብናላችሁና የተማረኩትን ወደዚህ አታግቡ፤ በደላችን ታላቅ ነውና፥ የእግዚአብሔርም የመቅሠፍቱ ቍጣ በእስራኤል ላይ ነውና” አሉአቸው። 14 ሰልፈኞቹም ምርኮኞቹንና ምርኮውን በአለቆችና በጉባኤ ሁሉ ፊት ተዉ። 15 በስማቸውም የተጻፉ ሰዎች ተነሥተው ምርኮኞቹን ወሰዱ፤ በመካከላቸውም ራቁታቸውን ለነበሩት ሁሉ ከምርኮው አለበሱአቸው፤ አጐናጸፉአቸውም፤ ጫማም በእግራቸው አደረጉላቸው፤ መገቡአቸውም፤ አጠጡአቸውም፤ ቀቡአቸውም፤ ደካሞቹንም ሁሉ በአህዮች ላይ አስቀመጡአቸው፤ ዘንባባም ወዳለበት ከተማ ወደ ኢያሪኮ ወደ ወንድሞቻቸው አመጡአቸው፤ ወደ ሰማርያም ተመለሱ። ንጉሡ አካዝ የአሦርን ንጉሥ ርዳታ እንደ ጠየቀ ( 2ነገ. 16፥7-9 ) 16 በዚያም ጊዜ ንጉሡ አካዝ ርዳታ ፈልጎ ወደ አሦር ንጉሥ ላከ፤ 17 የኤዶምያስ ሰዎች ዳግመኛ መጥተው፥ ይሁዳንም መትተው ብዙ ምርኮኛ ወስደው ነበርና። 18 ደግሞም ፍልስጥኤማውያን በቆላውና በደቡብ በኩል ባሉት በይሁዳ ከተሞች አደጋ ጥለው ነበር፤ ቤትሳሚስንና ኤሎንን፥ ጋቤሮትንም፥ ሠካዕንና መንደሮችዋን፥ ቴምናንና መንደሮችዋንም፥ ጋማዚእንና መንደሮችዋን ወስደው በዚያ ተቀምጠው ነበር። 19 በይሁዳም ንጉሥ በአካዝ ምክንያት እግዚአብሔር ይሁዳን አዋረደው፤ እርሱ ከእግዚአብሔር እጅግ ርቆአልና። 20 የአሦርም ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር መጥቶ አስጨነቀው። 21 አካዝም ከእግዚአብሔር ቤት ከንጉሡና ከአለቆቹም ቤት የነበረውን ሁሉ ወሰደ፤ ለአሦርም ንጉሥ ሰጠ፥ ነገር ግን አስጨነቀው እንጂ አልረዳውም። 22 ዳግመኛም ንጉሡ አካዝ ፈጽሞ ከእግዚአብሔር ራቀ። 23 ንጉሡም፥ “የመቱኝን የደማስቆን አማልክት እፈልጋቸዋለሁ፤ የሶርያን ንጉሥ እርሱን ረድተውታልና እኔንም ይረዱኝ ዘንድ እሠዋላቸዋለሁ” አለ። ነገር ግን ለእርሱና ለእስራኤል ሁሉ ዕንቅፋት ሆኑ። 24 አካዝም የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃዎች ሁሉ ወስዶ ሰባበራቸው፤ የእግዚአብሔርንም ቤት ደጆች ዘጋ፤ በኢየሩሳሌምም ማዕዘን ሁሉ ለራሱ መሠዊያ ሠራ። 25 በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ለሌሎች አማልክት ያጥን ዘንድ የኮረብታ መስገጃዎችን አሠራ፤ የአባቶቻቸውንም አምላክ እግዚአብሔርን አስቈጣ። 26 የቀሩትም ነገሮቹና ሥራው ሁሉ፥ የፊተኞቹና የኋለኞቹ እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል። 27 አካዝም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት፤ ነገር ግን ወደ እስራኤል ነገሥታት መቃብር አላገቡትም፤ ልጁም ሕዝቅያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። |