2 ዜና መዋዕል 23 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የይሁዳ ንጉሥ የአካዝያስ ዘመነ መንግሥት ( 2ነገ. 11፥4-16 ) 1 በሰባተኛውም ዓመት ኢዮአዳ በረታ፤ የመቶ አለቆቹንም፥ የኢዮራምን ልጅ አዛርያስን፥ የኢዮአናንም ልጅ እስማኤልን፥ የዖቤድንም ልጅ አዛርያን፥ የኢዳኢንም ልጅ መዓስያን፥ የዘካርያስንም ልጅ ኤሊሳፋጥን ወደ እግዚአብሔር ቤት ከእርሱ ጋር ወሰደ። 2 ይሁዳንም ዞሩ፤ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ሌዋውያንንና የእስራኤልን አባቶች ቤቶች አለቆች ሰብስበው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 3 የይሁዳም ጉባኤ ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ከንጉሥ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። የንጉሥንም ልጅ አሳያቸው፤ አላቸውም፥ “እነሆ፥ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ቤት እንደ ተናገረ የንጉሡ ልጅ ይነግሣል። 4 እነሆ፥ የምታደርጉት ይህ ነው፤ በሰንበት ቀን ከምትገቡት ከእናንተ ከካህናትና ከሌዋውያን ከሦስት አንድ እጅ በመግቢያ በሮች በረኞች ሁኑ፤ 5 ከሦስት አንድ እጅም በንጉሡ ቤት ሁኑ፤ ሌላውም ከሦስት አንድ እጅ በመካከለኛው በር ሁኑ፤ ሕዝቡም ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ይሁኑ። 6 ወደ እግዚአብሔር ቤት ግን ከካህናትና ከሌዋውያን ከሌዋውያኑም አገልጋዮች በቀር ማንም አይግባ፤ እነርሱ ቅዱሳን ናቸውና ይግቡ፤ ሕዝቡም ሁሉ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቅ። 7 ሌዋውያንም የጦር መሣሪያቸውን በእጃቸው ይዘው ንጉሡን በዙሪያው ይክበቡት፤ ወደ ቤቱም የሚገባ ይገደል፤ ንጉሡም ሲገባና ሲወጣ ከእርሱ ጋር ሁኑ።” 8 ሌዋውያንና ይሁዳም ሁሉ ካህኑ ኢዮአዳ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ፤ ካህኑም ኢዮአዳ ሰሞነኞቹን አላሰናበተም ነበርና እያንዳንዱ ከሰንበት መጀመሪያ እስከ ሰንበት መጨረሻ ሰዎችን ወሰደ። 9 ካህኑም ኢዮአዳ በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን የንጉሡን የዳዊትን ሰይፍና ጦር፥ አላባሽ አግሬውንም ጋሻ ለመቶ አለቆች ሰጣቸው። 10 ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ የጦር መሣሪያውን በእጁ እየያዘ በንጉሡ ዙሪያ ከቤተ መቅደሱ ቀኝ እስከ ቤተ መቅደሱ ግራ ድረስ በመሠዊያውና በመቅደሱ አጠገብ እንዲቆም አደረገ። 11 የንጉሡንም ልጅ አውጥቶ ዘውዱን ጫነበት፤ ምስክሩንም ሰጠው፤ አነገሡትም፤ ኢዮአዳና ልጆቹም አነገሡት፥ “ንጉሡ በሕይወት ይኑር” እያሉም ቀቡት። 12 ጎቶልያም የሚሮጡትንና ንጉሡን የሚያመሰግኑትን የሕዝቡን ድምፅ በሰማች ጊዜ ወደ ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ቤት መጣች። 13 እነሆም፥ ንጉሡ በመግቢያው በዓምዱ አጠገብ ሆኖ በንጉሡም ዙሪያ አለቆችና መለከተኞች፥ መኳንንትም ቆመው አየች። ሕዝቡም ሁሉ ደስ ብሎአቸው መለከቱን ይነፉ ነበር፤ መዘምራንም በዜማ ዕቃ እያዜሙ የምስጋና መዝሙር ይዘምሩ ነበር። ጎቶልያም ልብስዋን ቀድዳ፥ “ዐመፅ ነው! ዐመፅ ነው!” ብላ ጮኸች። 14 ካህኑም ኢዮአዳ ወጥቶ በጭፍራው ላይ የተሾሙትን አለቆችና የመቶ አለቆች፥ “ከቤተ እግዚአብሔር ወደ ውጭ አውጡአት፤ የሚከተላትም በሰይፍ ይገደል” ብሎ አዘዛቸው። ካህኑ፥ “በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ አትገደል” ብሎአልና። 15 ገለልም ብለው አሳለፉአት፤ እርስዋም ወደ ፈረሱ በር መግቢያ ወደ ንጉሡ ቤት ሄደች፤ በዚያም ገደሉአት። 16 ካህኑ ኢዮአዳም በእርሱና በሕዝቡ ሁሉ፥ በንጉሡም መካከል የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ ቃል ኪዳን አደረገ። 17 የሀገሩም ሕዝብ ሁሉ ወደ በዓል ቤት ሄደው አፈረሱት፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹንም አደቀቁ፤ የበዓልንም ካህን ማታንን በመሠዊያው ፊት ገደሉት። 18 ካህኑ ኢዮአዳም በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈው እንደ ዳዊት ትእዛዝ በደስታና በመዝሙር ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ ዳዊት በእግዚአብሔር ቤት የከፈላቸውን ካህናትና ሌዋውያን በእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ላይ ሾመ። 19 በማናቸውም ነገር ሁሉ ርኩስ የሆነ ሰው እንዳይገባ በእግዚአብሔር ቤት በር በረኞችን አኖረ። 20 የመቶ አለቆችንም፥ ከበርቴዎችንም፥ የሕዝቡንም አለቆች፥ የሀገሩንም ሕዝብ ሁሉ ወሰደ፤ ንጉሡንም ከእግዚአብሔር ቤት አወረዱት፤ በእግዚአብሔርም ቤት በውስጠኛው በር በኩል ወደ ንጉሡ ቤት አመጡት፤ ንጉሡንም በመንግሥቱ ዙፋን ላይ አስቀመጡት። 21 የሀገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ አላቸው፤ ከተማዪቱም ጸጥ አለች፤ ጎቶልያንም በሰይፍ ገደሉአት። |