2 ዜና መዋዕል 18 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ነቢዩ ሚክያስ በአክዓብ ላይ ትንቢት እንደ ተናገረ ( 1ነገ. 22፥1-28 ) 1 ለኢዮሣፍጥም ብዙ ብልጥግናና ክብር ነበረው፤ ከአክዓብም ወገን ሚስት አገባ። 2 ከጥቂት ዓመታት በኋላም ወደ አክዓብ ወደ ሰማርያ ወረደ። አክዓብም ለእርሱና ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሕዝብ ብዙ በጎችንና በሬዎችን አረደ፤ ወደደውም፤ ከእርሱም ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ ይሄድ ዘንድ አባበለው። 3 የእስራኤልም ንጉሥ አክዓብ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፥ “ከእኔ ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ ትሄዳለህን?” አለው። እርሱም፥ “እኔ እንደ አንተ ነኝ፤ ሕዝቤም ለሰልፍ እንደ ሕዝብህ ናቸው፤” ብሎ መለሰለት። 4 ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ፥ “ዛሬ እግዚአብሔርን ጠይቅ” አለው። 5 የእስራኤልም ንጉሥ ከነቢያቱ አራት መቶ ሰዎችን ሰብስቦ፥ “ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ ልሂድን? ወይስ ልቅር?” አላቸው። እነርሱም፥ “እግዚአብሔር በንጉሥ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ውጣ” አሉት። 6 ኢዮሣፍጥ ግን፥ “እንጠይቀው ዘንድ የእግዚአብሔር ነቢይ የሆነ ሌላ ሰው በዚህ አይገኝምን?” አለ። 7 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፥ “እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን ሁልጊዜ ክፉ እንጂ ከቶ መልካም ትንቢት አይናገርልኝምና እጠላዋለሁ፤ እርሱም የይምላ ልጅ ሚክያስ ነው” አለው። ኢዮሣፍጥም፥ “ንጉሡ እንዲህ አይበል” አለው። 8 የእስራኤልም ንጉሥ አንድ ጃንደረባ ጠርቶ፥ “የይምላን ልጅ ሚክያስን ፈጥነህ አምጣው” አለው። 9 የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ልብሰ መንግሥት ለብሰው በሰማርያ በር መግቢያ አጠገብ በአደባባይ በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያትም ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር። 10 የካህናን ልጅ ሴዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ሶርያውያንን እስክታጠፋቸው ድረስ በእነዚህ ትወጋለህ” አለ። 11 ነቢያትም ሁሉ፥ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ወደ ሬማት ዘገለዓድ ውጣና ተከናወን” እያሉ እንዲሁ ትንቢት ይናገሩ ነበር። 12 ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልእክተኛ፥ “እነሆ፥ ነቢያት በአንድ አፍ ሆነው ለንጉሡ መልካም ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ” አለው። 13 ሚክያስም፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! አምላኬ የሚለውን እርሱን እናገራለሁ” አለ። 14 ወደ ንጉሡም በመጣ ጊዜ ንጉሡ፥ “ሚክያስ ሆይ፥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ ልሂድን? ወይስ ልቅር?” አለው። 15 ነቢዩ ሚክያስም፥ “ውጣ፤ ተከናወን፤ በእጅህም አልፈው ይሰጣሉ” አለ። ንጉሡም፥ “በእግዚአብሔር ስም ከእውነት በቀር እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ?” አለው። 16 እርሱም፥ “እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም፦ ለእነዚህ ጌታ የላቸውም፥ እያንዳንዱም በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ አለ” ብሎ ተናገረ። 17 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፥ “ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት አይናገርልኝም አላልሁህምን?” አለው። 18 ሚክያስም አለ፥ “እንዲህ አይደለም፤ እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይ ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው፤ ቆመው አየሁ።” 19 እግዚአብሔርም፥ “ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ ይወድቅ ዘንድ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን የሚያታልል ማን ነው?” አለ። አንዱም እንደዚህ፥ ሌላውም እንደዚያ ያለ ነገር ተናገረ። 20 መንፈስም መጣ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ቆሞ፥ “እኔ አታልለዋለሁ” አለ። እግዚአብሔርም፥ “በምን ታታልለዋለህ?” አለው። 21 እርሱም፥ “ወጥቼ በነቢያት ሁሉ አፍ የሐሰት መንፈስ እሆናለሁ” አለ። እግዚአብሔርም፥ “ታታልለዋለህ፤ ይቀናሃል፥ ውጣ፤ እንዲህም አድርግ” አለው። 22 “አሁንም እነሆ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ በነቢያትህ አፍ የሐሰት መንፈስን አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም በአንተ ላይ ክፉ ተናግሮብሃል።” 23 የካህናንም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፤ ሚክያስንም በጥፊ መታውና፥ “የእግዚአብሔር መንፈስ ከአንተ ጋር ይናገር ዘንድ በምን መንገድ ከእኔ አለፈ?” አለው። 24 ሚክያስም፥ “እነሆ፥ በዚያ ቀን ልትሸሸግ ከእልፍኝ ወደ እልፍኝ ስትሄድ ታያለህ” አለ። 25 የእስራኤልም ንጉሥ እንዲህ አለ፥ “ሚክያስን ውሰዱ፤ ወደ ከተማዪቱም አለቃ ወደ ኤሜር፥ ወደ ንጉሡም ልጆች አለቃ ወደ ኢዮአስ መልሱት 26 እንዲህም በሉአቸው፦ ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በግዞት አኑሩት፤ የመከራም እንጀራ መግቡት፤ የመከራም ውኃ አጠጡት።” 27 ሚክያስም፥ “በደኅና ብትመለስ እግዚአብሔር በእኔ አልተናገረም” አለ። “ደግሞም እናንተ ሕዝቡ ሁሉ ስሙኝ” አለ። 28 የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ወጡ። 29 የእስራኤል ንጉሥም ኢዮሣፍጥን፥ “ልብሴን ለውጬ ወደ ጦርነት እገባለሁ፤ አንተ ግን የእኔን ልብስ ልበስ” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ልብሱን ለወጠ፤ ወደ ሰልፍም ገባ። 30 የሶርያም ንጉሥ ከእርሱ ጋር የነበሩትን የሰረገሎቹን አለቆች፦ ከእስራኤልም ንጉሥ በቀር ትንሽ ቢሆን ወይም ትልቅ ከማናቸውም ጋር አትጋጠሙ ብሎ አዝዞ ነበር። 31 የሰረገሎችም አለቆች ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ፥ “የእስራኤል ንጉሥ ነው” አሉ፤ ሊጋጠሙትም ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ግን ጮኸ፤ እግዚአብሔርም አዳነው፤ አምላኩም ከእርሱ መለሳቸው። 32 የሰረገሎቹም አለቆች የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ ከእርሱ ተመለሱ። 33 አንድ ሰውም ቀስቱን በድንገት ገትሮ የእስራኤልን ንጉሥ በጥሩሩ መጋጠሚያ በኩል ሳንባውን ወጋው። ሰረገለኛውንም፥ “ተወግቻለሁና እጅህን ግታ፤ ከጦርነት ውስጥ አውጣኝ” አለው። 34 በዚያም ቀን ጦርነት በረታ፤ የእስራኤልም ንጉሥ በሶርያውያን ፊት እስከ ማታ ድረስ በሰረገላው ላይ ራሱን ይደግፍ ነበር፤ ፀሐይም በገባ ጊዜ ሞተ። |