2 ዜና መዋዕል 15 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 የእግዚአብሔርም መንፈስ በአዳድ ልጅ በአዛርያስ ላይ መላ፤ 2 እርሱም ንጉሡን አሳን፥ የይሁዳንና የብንያምን ሕዝብ ሁሉ ሊገናኝ ወጣ፤ እንዲህም አለ፥ “አሳ ይሁዳና ብንያም ሁሉ ሆይ፥ ስሙኝ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር ጋር ብትሆኑ እርሱ ከእናንተ ጋር ይሆናል፤ ብትፈልጉትም ይገኝላችኋል፤ ብትተዉት ግን ይተዋችኋል። 3 እስራኤልም ብዙ ዘመን እውነተኛውን አምላክ ሳያመልኩ፥ ያለ አስተማሪም ካህን፥ ያለ ሕግም ይኖራሉ። 4 በመከራቸውም ጊዜ ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው ይፈልጉታል፤ እርሱም ይገኝላቸዋል። 5 በዚያም ዘመን ለሚወጣውና ለሚገባው ሰላም አይሆንለትም፤ በሀገሮችም በሚኖሩት ሁሉ ላይ ታላቅ የእግዚአብሔር ቍጣ ይሆናል። 6 እግዚአብሔር በመከራው ሁሉ ያስጨንቃቸዋልና ሕዝብ ከሕዝብ ጋር፥ ከተማም ከከተማ ጋር ይዋጋል። ። 7 እናንተ ግን ለሥራችሁ ዋጋ ይሆንላችኋልና በርቱ፤ እጆቻችሁም አይላሉ።” 8 አሳም ይህን ቃልና የነቢዩን የአዳድን ልጅ የአዛርያስን ትንቢት በሰማ ጊዜ ጸና፤ ከይሁዳና ከብንያምም ሀገር ሁሉ በተራራማው በኤፍሬም ሀገር ከያዛቸው ከተሞች ርኵሰትን ሁሉ አስወገደ፤ በእግዚአብሔርም ቤት ፊት የነበረውን የእግዚአብሔርን መሠዊያ አደሰ። 9 አምላኩም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንደ ሆነ ባዩ ጊዜ ከእስራኤል ዘንድ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተጠግተው ነበርና እርሱ ይሁዳንና ብንያምን ሁሉ፥ ከኤፍሬምና ከምናሴም፥ ከስምዖንም ፈልሰው ከእነርሱ ጋር የተቀመጡትን ሰበሰበ። 10 አሳም በነገሠ በዐሥራ አምስተኛው ዓመት በሦስተኛው ወር በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። 11 በዚያም ቀን ካመጡት ምርኮ ሰባት መቶ በሬዎችንና ሰባት ሺህ በጎችን ለእግዚአብሔር ሠዋ። 12 በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ይሹ ዘንድ ቃል ኪዳን አደረገ፤ 13 የእስራኤልንም አምላክ እግዚአብሔርን የማይፈልግ፥ ታናሽ ወይም ታላቅ፥ ወንድ ወይም ሴት ቢሆን፥ ይገደል ዘንድ ማሉ። 14 ለእግዚአብሔርም በታላቅ ድምፅና በእልልታ፥ በእንቢልታና በቀንደ መለከት ማሉ። 15 በፍጹምም ልባቸው ምለዋልና፥ በፍጹምም ሕሊናቸው ፈልገውታልና፥ እርሱም ተገኝቶላቸዋልና ይሁዳ ሁሉ በመሐላው ደስ አላቸው፤ እግዚአብሔርም በዙሪያቸው ዕረፍትን ሰጣቸው። 16 ንጉሡም አሳ እናቱን መዓካን ለአስጣርቴስ ስለ ሰገደች ከእቴጌነቷ አወረዳት፤ አሳም ምስሉን ቈርጦ ቀጠቀጠው፤ በቄድሮንም ወንዝ አጠገብ አቃጠለው። 17 በኮረብታ ላይ የነበሩትን መስገጃዎች ግን ከእስራኤል አላራቀም። ገና በእስራኤል ዘንድ እስከ አሁን ነበሩ፤ ይሁን እንጂ የአሳ ልብ በዘመኑ ሁሉ ፍጹም ነበረ። 18 አባቱም ዳዊት የቀደሰውን፥ እርሱም የቀደሰውን ወርቁንና ብሩን፥ ልዩ ልዩውንም ዕቃ ወደ እግዚአብሔር ቤትአገባ። 19 አሳም በነገሠበት ዘመን እስከ ሠላሳ አምስተኛው ዓመት ድረስ ጦርነት አልነበረም። |