2 ዜና መዋዕል 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የግብፅ ንጉሥ ሱስቀም ኢየሩሳሌምን እንደ ወረረ ( 1ነገ. 14፥25-28 ) 1 እንዲህም ሆነ፤ የሮብዓም መንግሥት በጸናች ጊዜ፥ እርሱም በበረታ ጊዜ፥ የእግዚአብሔርን ሕግ ረሳ፤ እስራኤልም ሁሉ ከእርሱ ጋር ረሱ። 2 ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብፅ ንጉሥ ሱስቀም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። እግዚአብሔርን በድለዋልና፤ 3 ሺህ ሁለት መቶ ሰረገሎችንና ስድሳ ሺህ ፈረሰኞችን ይዞ መጣ፤ ከእርሱም ጋር ከግብፅ ለመጣው ሕዝብ ቍጥር አልነበረውም፤ እነርሱም የልብያ ሰዎች፥ ሞጠግሊያናውያን፥ የኢትዮጵያም ሰዎች ነበሩ። 4 በይሁዳም የነበሩትን ምሽጎች ከተሞች ያዙ። እስከ ኢየሩሳሌምም ደረሱ። 5 ነቢዩም ሰማያ ወደ ሮብዓምና ከሱስቀም ሸሽተው በኢየሩሳሌም ወደ ተሰበሰቡት ወደ ይሁዳ መሳፍንት መጥቶ እንዲህ አላቸው፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እናንተ ተዋችሁኝ፤ ስለዚህ እኔ ደግሞ በግብፅ ንጉሥ በሱስቀም እጅ ተውኋችሁ።” 6 የእስራኤልም መሳፍንትና ንጉሡ አፈሩ፥ “እግዚአብሔር ጻድቅ ነው” አሉ። 7 እግዚአብሔርም እንደ ተመለሱና እንደ ተፀፀቱ ባየ ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል፥ “ከተመለሱ አላጠፋቸውም፤ ከጥቂት ቀንም በኋላ አድናቸዋለሁ፤ ቍጣዬም በኢየሩሳሌም ላይ አይፈስስም” ሲል ወደ ሰማያ መጣ። 8 ለእኔ መገዛትንና ለምድር ነገሥታት መገዛትን ያውቃሉና አገልጋዮች ይሆናሉ። 9 የግብፅ ንጉሥ ሱስቀምም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ የእግዚአብሔርንም ቤተ መዛግብትና የንጉሡን ቤተ መዛግብት ወሰደ፤ ሁሉንም ወሰደ፤ ደግሞም ሰሎሞን የሠራቸውን የወርቁን አላባሽ አግሬ ጋሻዎችን ወሰደ። 10 ንጉሡም ሮብዓም በእነርሱ ፋንታ የናስ አላባሽ አግሬ ጋሻዎችን ሠራ፤ ሮብዓምም የንጉሡን ቤት ደጅ በሚጠብቁ በዘበኞች አለቃ እጅ አኖራቸው። 11 ንጉሡም ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባ ቍጥር ዘበኞች መጥተው ይሸከሙአቸው ነበር፤ መልሰውም በዘበኞች ቤት ውስጥ ያኖሩአቸው ነበር። 12 በተፀፀተም ጊዜ የእግዚአብሔር ቍጣ ከእርሱ ዘንድ ራቀ፤ ፈጽሞም አላጠፋውም፤ በይሁዳ መልካም ነገር ተገኝቶአልና። 13 ንጉሡም ሮብዓም በኢየሩሳሌም ጸና፤ ንጉሥም ሆነ፤ ሮብዓምም በነገሠ ጊዜ የአርባ አንድ ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ስሙን ያኖርባት ዘንድ ከእስራኤል ሀገር ሁሉ በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም ዐሥራ ሰባት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የአሞን ሴት ንዑማ ነበረች። 14 እግዚአብሔርንም ይሻ ዘንድ ልቡን አላቀናም ነበርና ክፉ ነገርን አደረገ። 15 የሮብዓምም የፊተኛውና የኋለኛው ነገር እነሆ፥ በነቢዩ ሰማያና በባለ ራእዩ በአዶ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ሮብዓምም ከኢዮርብዓም ጋር በዘመኑ ሁሉ ይዋጋ ነበር። 16 ሮብዓምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም አብያ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። |