1 ዜና መዋዕል 29 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ንጉሡ ዳዊትም ለጉባኤው ሁሉ እንዲህ አለ፥ “እግዚአብሔር ብቻውን የመረጠው ልጄ ሰሎሞን ገና ለጋ ብላቴና ነው፤ ሕንጻው ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክ ነው እንጂ ለሰው አይደለምና ሥራው ታላቅ ነው። 2 እኔም እንደ ጉልበቴ ሁሉ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ቤት ወርቅን፥ ብርን፥ ናስን፥ ብረትን፥ እንጨትን፥ ደግሞም መረግድንና በፈርጥ የሚገባ ድንጋይን፥ የሚለጠፍ ድንጋይን፥ ልዩ ልዩ መልክ ያለውንም ድንጋይ፥ የከበረውንም ድንጋይ ከየዓይነቱ፥ ብዙም እብነ በረድ አዘጋጅቻለሁ። 3 ከዚህም በላይ ደግሞ የአምላኬን የእግዚአብሔርን ቤት ስለ ወደድሁ፥ ለመቅደሱ ከሰበሰብሁት ሁሉ ሌላ የግል ገንዘቤ የሚሆን ወርቅና ብር አለኝና እነሆ፥ ለአምላኬ ቤት ሰጥቼዋለሁ። 4 የእግዚአብሔር ቤት ግንቦች ይለበጡበት ዘንድ ከኦፌር ወርቅ ሦስት ሺህ መክሊት ወርቅ፥ ሰባት ሺህ መክሊትም ጥሩ ብር፤ 5 በሠራተኞች እጅ ለሚሠራው ሥራ ሁሉ ለወርቁ ዕቃ ወርቁን፥ ለብሩም ዕቃ ብሩን ሰጥቻለሁ። ዛሬ በዚች ቀን በፈቃዱ አገልግሎቱን ለእግዚአብሔር የሚፈጽም ማን ነው?” 6 የአባቶችም ቤቶች አለቆች፥ የእስራኤልም ልጆች አለቆች፥ ሻለቆችም፥ የመቶ አለቆችም፥ በእግዚአብሔር ቤት ሥራ የተሾሙና የንጉሡ ግንበኞች በፈቃዳቸው አቀረቡ። 7 ለእግዚአብሔርም ቤት ሥራ አምስት ሺህ መክሊት ወርቅና ዐሥር ሺህ ዳሪክ፥ ዐሥር ሺህም መክሊት ብር፥ ዐሥራ ስምንት ሺህም መክሊት ናስ፥ መቶ ሺህም መክሊት ብረት ሰጡ። 8 የከበረ ዕንቍም ያላቸው ሰዎች ሁሉ ለእግዚአብሔር ቤት ለሆነው ቤተ መዛግብት በጌድሶናዊው በኢዩኤል እጅ ሰጡ። 9 ሕዝቡም ፈቅደው ሰጥተዋልና፥ በፍጹም ልባቸውም ለእግዚአብሔር በፈቃዳቸው አቅርበዋልና ደስ አላቸው፤ ንጉሡም ዳዊት ደግሞ ታላቅ ደስታ ደስ አለው። 10 ንጉሡ ዳዊትም በጉባኤው ሁሉ ፊት እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ እንዲህም አለ፥ “አቤቱ፥ የእስራኤል አምላክ አባታችን እግዚአብሔር ሆይ፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ቡሩክ ነህ። 11 አቤቱ፥ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና ታላቅነትና ኀይል፥ ክብርም፥ ድልና ጽንዕ የአንተ ነው፤ ነገሥታቱና ሕዝቡ ሁሉ በፊትህ ይደነግጣሉ። 12 ባለጠግነትና ክብር ከአንተ ዘንድ ነው፤ አቤቱ፥ አንተም ሁሉን ትገዛለህ፤ የሥልጣን ሁሉ ጌታ ነህ፤ ኀይልና ብርታት በእጅህ ነው፤ ኀያል ነህ፤ ታላቅ ለማድረግ፥ ለሁሉም ኀይልን ለመስጠት ዓለምን ሁሉ በእጅህ የያዝህ ነህ። 13 አሁንም እንግዲህ፥ አምላካችን ሆይ፥ እንገዛልሃለን፤ ለክቡር ስምህም ምስጋና እናቀርባለን። 14 ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና፥ ከእጅህም የተቀበልነውን ሰጥተንሃልና ይህን ያህል ችለን ልናቀርብልህ እኔ ማን ነኝ? ሕዝቤስ ማን ነው? 15 አባቶቻችን ስደተኞች እንደ ነበሩ እኛ በፊትህ ስደተኞችና መጻተኞች ነን፤ ዘመናችንም በምድር ላይ እንደ ጥላ ናት፤ አትጸናምም። 16 አቤቱ አምላካችን ሆይ፥ ለቅዱስ ስምህ ቤት እሠራ ዘንድ ይህ ያዘጋጀሁት ባለጠግነት ሁሉ ከእጅህ የመጣ ነው፤ ሁሉም የአንተ ነው። 17 አምላኬ ሆይ፥ ልብን እንደምትመረምር፥ ጽድቅንም እንደምትወድድ አውቃለሁ፤ እኔም በልቤ ቅንነትና በፈቃዴ ይህን ሁሉ አቅርቤአለሁ፤ አሁንም በዚህ ያለው ሕዝብህ በፈቃዱ እንዳቀረበልህ በደስታ አይቻለሁ። 18 አቤቱ፥ የአባቶቻችን የአብርሃምና የይስሐቅ የእስራኤልም አምላክ ሆይ፥ ይህን አሳብ በሕዝብህ ልብ ላይ ለዘለዓለም ጠብቅ፤ ልባቸውንም ወደ አንተ አቅና። 19 ትእዛዝህንም ያደርግ ዘንድ፥ ምስክርህንም፥ ሥርዐትህንም ይጠብቅ ዘንድ፥ ያዘጋጀሁለትንም ቤት ይሠራ ዘንድ ለልጄ ለሰሎሞን ቅን ልብን ስጠው።” 20 ዳዊትም ጉባኤውን ሁሉ፥ “አምላካችን እግዚአብሔርን አመስግኑ” አላቸው። ጉባኤውም ሁሉ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፥ በጕልበታቸውም ተንበርክከው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ ደግሞም ለንጉሡ። 21 በነጋውም ዳዊት ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሠዋ፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ አንድ ሺህ ወይፈን፥ አንድ ሺህም አውራ በጎች፥ አንድ ሺህም የበግ ጠቦቶች፥ የመጠጥ ቍርባናቸውንም፥ ስለ እስራኤልም ሁሉ ብዙ መሥዋዕት አቀረበ። 22 በዚያም ቀን በታላቅ ደስታ በእግዚአብሔር ፊት በሉ፥ ጠጡም። የዳዊትንም ልጅ ሰሎሞንን ሁለተኛ ጊዜ አነገሡት፤ እርሱንም ንጉሥ ይሆን ዘንድ ለእግዚአብሔር ቀቡት፤ ሳዶቅም በካህናት ላይ ተሾመ። 23 ሰሎሞንም በአባቱ በዳዊት ዙፋን ላይ ተቀመጠ፤ በሁሉም ዘንድ ተወዳጅ ሆነ፤ እስራኤልም ሁሉ ታዘዙለት። 24 አለቆቹም ሁሉ፥ ኀያላኑም፥ ደግሞም የንጉሡ የአባቱ የዳዊት ልጆች ሁሉ ለንጉሡ ለሰሎሞን ተገዙለት። 25 እግዚአብሔርም ሰሎሞንን በእስራኤል ሁሉ ፊት እጅግ አገነነው፤ ከእርሱ በፊትም ለነበሩት ነገሥታት ያልሆነውን የመንግሥት ክብር ሰጠው። 26 የእሴይም ልጅ ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ አርባ ዓመት ነገሠ። 27 ሰባት ዓመት በኬብሮን፥ ሠላሳ ሦስትም ዓመት በኢየሩሳሌም ነገሠ። 28 ዕድሜም፥ ባለጠግነትም፥ ክብርም ጠግቦ በመልካም ሽምግልና ሞተ፤ ልጁም ሰሎሞን በእርሱ ፋንታ ነገሠ። 29 የንጉሡም የዳዊት የፊተኛውና የኋለኛው ነገር፥ እነሆ፥ በባለራእዩ በሳሙኤል ታሪክ፥ በነቢዩም በናታን ታሪክ፥ በባለ ራእዩም በጋድ ታሪክ ተጽፎአል። 30 እንደዚሁም የመንግሥቱ ነገርና ኀይሉ ሁሉ በእርሱም፥ በእስራኤልም፥ በምድርም መንግሥታት ሁሉ ላይ ያለፉት ዘመናት ተጽፈዋል። |