1 ዜና መዋዕል 28 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ዳዊት ለሰሎሞን የቤተ መቅደስን ምሳሌ እንደ አሳየው 1 ዳዊትም የእስራኤልን አለቆች ሁሉና የፍርድ አለቆችን፥ ንጉሡንም በየተራ የሚጠብቁትን አለቆቹን፥ ሻለቆቹንም፥ የመቶ አለቆቹንም፥ በንጉሡና በልጆቹ ሀብትና ንብረት ላይ፥ መባ ባለበት ላይ የተሾሙትን ጃንደረቦችንም፥ ኀያላኑንና ሰልፈኞቹን ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ። 2 ንጉሡም ዳዊት በጉባኤው መካከል ቆሞ እንዲህ አለ፥ “ወንድሞቼና ሕዝቤ ሆይ፥ ስሙኝ፤ ለእግዚአብሔር ለቃል ኪዳኑ ታቦትና ለአምላካችን እግር ማረፊያ የዕረፍት ቤት ለመሥራት አሳብ በልቤ መጣብኝ፤ ለዚህም ሥራ የሚያስፈልገውን አዘጋጅቻለሁ፤ 3 እግዚአብሔር ግን፦ የሰልፍ ሰው ነህና፥ ብዙ ደምም አፍስሰሃልና ስሜ የሚጠራበትን ቤት አትሠራም ብሎኛል። 4 ነገር ግን የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ የዘለዓለም ንጉሥ እሆን ዘንድ ከአባቴ ቤት ሁሉ መርጦኛል፤ ይሁዳንም አለቃ ይሆን ዘንድ መርጦታል፤ ከይሁዳም ቤት የአባቴን ቤት መርጦአል፤ ከአባቴም ልጆች መካከል በእስራኤል ሁሉ ላይ ያነግሠኝ ዘንድ እኔን ሊመርጠኝ ወደደ። 5 እግዚአብሔርም ብዙ ልጆች ሰጥቶኛልና ከልጆቼ ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ዙፋን ላይ ተቀምጦ በእስራኤል ላይ ይነግሥ ዘንድ ልጄን ሰሎሞንን መርጦታል። 6 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ ልጅ ይሆነኝ ዘንድ መርጬዋለሁና፥ እኔም አባት እሆነዋለሁና ልጅህ ሰሎሞን ቤቴንና አደባባዮቼን ይሠራል። 7 ትእዛዜንና ፍርዴንም መጠበቅ ቢችልና እንደ ዛሬው ቢጸና መንግሥቱን ለዘለዓለም አጸናዋለሁ። 8 አሁንም የእግዚአብሔር ጉባኤ እስራኤል ሁሉ እያዩ፥ አምላካችንም እየሰማ፥ ይህችን መልካሚቱን ምድር ትወርሱ ዘንድ፥ ለልጆቻችሁም ለዘለዓለም ታወርሱአት ዘንድ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሁሉ ጠብቁ፤ ፈልጉም። 9 “አንተም ልጄ ሰሎሞን ሆይ፥ እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ይመረምራልና፥ የነፍስንም አሳብ ሁሉ ያውቃልና የአባቶችህን አምላክ ዕወቅ፤ በፍጹም ልብና በነፍስህ ፈቃድም ተገዛለት፤ ብትፈልገው ታገኘዋለህ፤ ብትተወው ግን ለዘለዓለም ይተውሃል። 10 አሁንም፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር ለመቅደስ የሚሆን ቤትን ትሠራ ዘንድ መርጦሃልና ጠንክረህ ፈጽመው።” 11 ዳዊትም ለመቅደሱ ወለል፥ ለቤቱም፥ ለቤተ መዛግብቱም፥ ለደርቡና ለውስጡም ጓዳዎች፥ ለስርየቱም መክደኛ መቀመጫ ምሳሌውን ለልጁ ለሰሎሞን ሰጠው። 12 ደግሞም ለእግዚአብሔር ቤት አደባባዮችና በዙሪያው ለሚሆኑ ጓዳዎች፥ ለእግዚአብሔርም ቤት ለሚሆኑ ቤተ መዛግብት፥ ለንዋየ ቅድሳቱም ለሚሆኑ ዕቃ ቤቶች፥ ለቀሩትም በመንፈሱ ላሰበው ሁሉ ምሳሌን ሰጠው። 13 የካህናቱንና የሌዋውያኑንም ክፍላቸውን፥ በእግዚአብሔርም ቤት ለሚያገለግሉበት ሥራ ሁሉ፥ በእግዚአብሔርም ቤት ለሚያገለግሉበት ዕቃ ሁሉ፥ ለአገልግሎት ሁሉ ለሚሆነውም፥ 14 ለወርቁ ዕቃ ወርቁን በሚዛን ሰጠው፤ ለአገልግሎት ሁሉ ለሚሆነውም ለብር ዕቃ ሁሉ ብሩን በሚዛን ሰጠው፤ 15 ለወርቁም መቅረዞችና ለቀንዲሎችም ወርቁን በየመቅረዙና በየቀንዲሉ በሚዛን ሰጠው፤ ለብሩም መቅረዞች እንደ መቅረዙ ሁሉ ሥራ ብሩን በየመቅረዙና በየቀንዲሉ በሚዛን ሰጠው፤ 16 ዳግመኛም ለገጹ ኅብስት ገበታዎች ወርቁን በሚዛን ለገበታዎቹ ሁሉ፥ ብሩንም ለብሩ ገበታዎች እንደዚሁ ሰጠው፤ 17 ለሥጋ ሜንጦዎቹና ለድስቶቹ፥ ለመጠጥ ቍርባን መቅጃዎቹም ጥሩውን ወርቅ፥ ለወርቁም ጽዋዎች ወርቁን በየጽዋው ሁሉ በሚዛን ሰጠው፤ ለብሩም ጽዋዎች ብሩን በየጽዋው በሚዛን ሰጠው። 18 ለዕጣኑም መሠዊያ ጥሩውን ወርቅ በሚዛን፥ ክንፎቻቸውንም ዘርግተው የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት የሸፈኑትን የኪሩቤልን የወርቅ ሰረገላ ምሳሌ አሳየው። 19 ዕውቀት እንደ ተሰጠው የእግዚአብሔርን ቤት ይሠራ ዘንድ ዳዊት በእግዚአብሔር ሕግ የተጻፈውን ለልጁ ለሰሎሞን ሰጠው። 20 ዳዊትም ልጁን ሰሎሞንን፥ “ጠንክር፤ ሰው ሁን፤ አይዞህ፥ አድርገውም፤ አምላኬ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና አትፍራ፤ አትደንግጥም፤ ለእግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት የሚሆነውን ሥራ ሁሉ እስክትፈጽም ድረስ እርሱ አይተውህም፤ አይጥልህምም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር ቤት ሕንጻ ምሳሌ፥ የአደባባዩ፥ የቤተ መዛግብቱ፥ የሰገነቱ፥ የውስጡ ቤተ መዛግብት፥ የስርየት ቤቱና፥ የእግዚአብሔር ቤት ምሳሌ። 21 እነሆም፥ ለእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ሁሉ የሚሆኑ የካህናትና የሌዋውያን ክፍሎች በዚህ አሉ፤ ለሁሉም ዓይነት አገልግሎትና ሥራ በጥበብና በነፍሱ ፈቃድ የሚሠራ ሁሉ ከአንተ ጋር ይሆናል፤ አለቆችና ሕዝቡም ሁሉ ፈጽመው ይታዘዙሃል” አለው። |