1 ዜና መዋዕል 27 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 የእስራኤልም ልጆች የአባቶች ቤቶች አለቆችና የሺህ አለቆች፥ የመቶ አለቆችም ለንጉሡና ለንጉሡ ትእዛዝ ሁሉ የሚያገለግሉ ሹማምት እንደ ቍጥራቸው በየክፍላቸው እነዚህ ነበሩ። እነዚህም ክፍሎች እያንዳንዳቸው ሃያ አራት ሺህ ሆነው በዓመቱ ወራት ሁሉ በየወሩ ይገቡና ይወጡ ነበር። 2 ለመጀመሪያው ወር በአንደኛው ክፍል ላይ የዘብድኤል ልጅ ያሶብአም ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 3 እርሱም ከፋሬስ ልጆች ነበረ፤ ለመጀመሪያው ወር በጭፍራ አለቆች ሁሉ ላይ ተሾሞ ነበር። 4 በሁለተኛውም ወር ክፍል ላይ የኤቲ ልጅ ዶድያ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሚኮሎት አለቃ ነበር፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 5 በሦስተኛው ወር ሦስተኛው የጭፍራ አለቃ የካህኑ የዮዳሄ ልጅ በናያስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሽህ ጭፍራ ነበረ። 6 ይህ በናያስ ከሠላሳው መካከል ኀያል ሆኖ በሠላሳው ላይ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ልጁ ዓሚዛባድ ነበረ። 7 በአራተኛው ወር አራተኛው አለቃ የኢዮአብ ወንድም አሳሄል ነበረ፤ ከእርሱም በኋላ ልጁ ዝባድያና ወንድሞቹ ነበሩ፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 8 በአምስተኛው ወር አምስተኛው አለቃ ይዝራዊው ሰማኦት ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 9 በስድስተኛውም ወር ስድስተኛው አለቃ የቴቁሓዊው የአቂስ ልጅ ኢይዝራኤል ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 10 በሰባተኛውም ወር ሰባተኛው አለቃ ከኤፍሬም ልጆች የሆነ ፍሎሳዊው ከሊስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 11 በስምንተኛው ወር ስምንተኛው አለቃ ከዛራውያን የነበረው ኩሳታዊው ሲቦካይ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 12 በዘጠነኛው ወር ዘጠነኛው አለቃ ከብንያማውያን የነበረው ዓናቶታዊው አቢዔዜር ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 13 በዐሥረኛው ወር ዐሥረኛው አለቃ ከዛራውያን የነበረው ነጦፋዊው መዐርኢ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 14 በዐሥራ አንደኛው ወር ዐሥራ አንደኛው አለቃ ከኤፍሬም ልጆች የነበረው ፍርዓቶናዊው በናያስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 15 በዐሥራ ሁለተኛው ወር ዐሥራ ሁለተኛው አለቃ ከጎቶንያል ወገን የነበረው ነጦፋታዊው ኬልዳይ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 16 በእስራኤልም ነገዶች ላይ እነዚህ ነበሩ፦ በሮቤላውያን ላይ የዝክሪ ልጅ ኤልያዛር አለቃ ነበረ፤ በስምዖናውያን ልጅ የመዓካ ልጅ ሰፋጥያስ ነበረ፤ 17 በሌዊ ወገን ላይ የቀሙኤል ልጅ አሰብያ፤ በአሮን ወገን ላይ ሳዶቅ፤ 18 በይሁዳ ወገን ላይ ከዳዊት ወንድሞች ኤልያብ፤ በይሳኮር ወገን ላይ የሚካኤል ልጅ ዖምሪ፤ 19 በዛብሎን ወገን ላይ የአብድዩ ልጅ ሶማዒያስ፤ በንፍታሌም ወገን ላይ የዖዜሄል ልጅ ኢያሪሙት፤ 20 በኤፍሬም ልጆች ላይ የአዛዝያ ልጅ ሆሴዕ፤ በምናሴ ነገድ እኩሌታ ላይ የፈዳያ ልጅ ኢዩኤል፤ 21 በገለዓድ ምድር ባለው በምናሴ ነገድ እኩሌታ ላይ የዘብድያስ ልጅ ኢዮዳኢ፤ በብንያምም ልጆች ላይ የአበኔር ልጅ አሳሄል፤ 22 በዳን ወገንም ላይ የኢዮራም ልጅ ዓዛርኤል፤ እነዚህ የእስራኤል ነገዶች አለቆች ነበሩ። 23 ነገር ግን እግዚአብሔር ሕዝቡ እስራኤልን እንደ ሰማይ ከዋክብት ያበዛ ዘንድ ተናግሮ ነበርና ዳዊት ከሃያ ዓመት በታች የነበሩትን አልቈጠረም። 24 የሶርህያ ልጅ ኢዮአብም መቍጠር ጀመረ፤ ነገር ግን አልፈጸመም፤ ስለዚህ ነገር በእስራኤል ላይ ቍጣ ሆነ፤ ቍጥራቸውም በንጉሡ በዳዊት የታሪክ መጽሐፍ አልተጻፈም። 25 በንጉሡም ቤተ መዛግብት ላይ የዓዳኤል ልጅ ዓዝሞት ሹም ነበረ፤ በሜዳውም፥ በከተሞቹም፥ በመንደሮቹም፥ በግንቦቹም ቤተ መዛግብት ላይ የዖዝያ ልጅ ዮናታን ሹም ነበረ፤ 26 መሬቱን በሚያበጃጁትና እርሻውን በሚያርሱት ላይ የክሉብ ልጅ ዔዝሪ ሹም ነበረ፤ 27 በወይንም ቦታዎች ላይ ራማታዊው ሰሜኢ ሹም ነበረ፤ ለወይንም ጠጅ ዕቃ ቤት በሚሆነው በወይኑ ሰብል ላይ የሳፍኒው ዘብዲ ሹም ነበረ። 28 በቈላውም ውስጥ ባሉት በወይራውና በሾላው ዛፎች ላይ ጌድራዊው በአልሐናን ሹም ነበረ፤ በዘይቱም ቤቶች ላይ ኢዮአስ ሹም ነበረ፤ 29 በሳሮንም በሚሰማሩ ከብቶች ላይ ሳሮናዊው ሰጥራይ ሹም ነበረ፤ በሸለቆዎቹም ውስጥ በነበሩት ከብቶች ላይ የዓድላይ ልጅ ሳፋጥ ሹም ነበረ፤ 30 በግመሎቹም ላይ እስማኤላዊው ኤቢያስ ሹም ነበረ፤ በአህዮቹም ላይ ሜሮኖታዊው ኢያድስ ሹም ነበረ፤ 31 በበጎችም ላይ አጋራዊው ያዚዝ ሹም ነበረ። እነዚህ ሁሉ በንጉሡ በዳዊት ሀብት ላይ ሹሞች ነበሩ። 32 አስተዋይና ጸሓፊ የነበረው በአባቱ በኩል የዳዊት አጎት ዮናታን አማካሪ ነበረ፤ የአክማኔም ልጅ ኢያሔኤል ከንጉሡ ልጆች ጋር ነበረ፤ 33 አኪጦፌልም የንጉሡ አማካሪ ነበረ። አርካዊው ኩሲም የንጉሡ አንደኛ ወዳጅ ነበረ፤ 34 ከአኪጦፌልም ቀጥሎ የበናያስ ልጅ ዮዳሔና አብያታር ነበሩ፤ ኢዮአብም የንጉሡ ሠራዊት አለቃ ነበረ። |