1 ዜና መዋዕል 26 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእግዚአብሔር ቤት በረኞች 1 በረኞችም እንደዚህ ተመደቡ፤ ከቆሬያውያን ከአሳፍ ልጆች የቆሬ ልጅ ሜሱላም። 2 ሜሱላምም ልጆች ነበሩት፤ በኵሩ ዘካርያስ፥ ሁለተኛው ይዲኤል፥ ሦስተኛው ዘባድያ፥ አራተኛው የትንኤል፤ 3 አምስተኛው ኤላም፥ ስድስተኛው ይሆሐናን፥ ሰባተኛው ኤሊሆዔናይ። 4 ዖቤድኤዶምም ልጆች ነበሩት፤ በኵሩ ሰማያ፥ ሁለተኛው ዮዛባት፥ ሦስተኛው ኢዮአስ፥ አራተኛው ሣካር፥ አምስተኛው ናትናኤል፤ 5 ስድስተኛው ዓሚኤል፥ ሰባተኛው ይሳኮር፥ ስምንተኛው ፒላቲ ነበሩ፤ አምላኩ እግዚአብሔር ባርኮታልና። 6 ለልጁ ለሰማያም ከበኵር ልጁ ከሮሲ ልጆች ተወለዱለት፤ እነርሱም በአባታቸው ቤት የሠለጠኑ እጅግም ኀያላን ነበሩ። 7 የሰማያ ልጆች ዖትኒ፥ ራፋኤል፥ ዖቤድ፥ ወንድሞቹም ኀያላን የነበሩ ኤልዛባድ፥ ኤሊሁ፥ ሰማክያ፥ ኢስባኮም። 8 እነዚህ ሁሉ የዖቤድኤዶም ልጆች ነበሩ፤ እነርሱም፥ ልጆቻቸውም፥ ወንድሞቻቸውም ለማገልገል ኀያላን የነበሩ የዖቤድኤዶም ልጆች ስድሳ ሁለት ነበሩ። 9 ለሜሱላምም ኀያላን የነበሩ ዐሥራ ስምንት ልጆችና ወንድሞች ነበሩት። 10 ከሜራሪም ልጆች ለነበረው ለሖሳ ፊተኛውን በር የሚጠብቁ ልጆች ነበሩት፤ አለቃውም ሰምሪ ነበረ፤ በኵር አልነበረም፤ አባቱ ግን አለቃ አደረገው፤ 11 ሁለተኛውም ኬልቅያስ፥ ሦስተኛውም ጥበልያ፥ አራተኛውም ዘካርያስ ነበረ፤ የሖሳ ልጆችና ወንድሞች ሁሉ ዐሥራ ሦስት ነበሩ። 12 እንደ ወንድሞቻቸው ሆነው በእግዚአብሔር ቤት ያገለግሉ ዘንድ የበረኞች አለቆች በየሰሞናቸው የሚጠብቁ እነዚህ ነበሩ። 13 በበሩም ሁሉ ያገለግሉ ዘንድ በየአባቶቻቸው ቤቶች ታናሹና ታላቁ ተካክለው ዕጣ ተጣጣሉ። 14 የምሥራቁም በር ዕጣ ለሰሌምያና ለዘካርያ ወደቀ። የዮአስም ልጆች ለምልክያ ዕጣ ጣሉ፤ ዕጣውም በሰሜን በኩል ወጣ። 15 ለአብዲዶም በደቡብ በኩል በዕቃ ቤት አንጻር ዕጣ ወጣ። 16 ለሶፊምና ለሖሳም በምዕራብ በኩል በዐቀበቱ መንገድ ባለው በሸለኬት በር በኩል ጥበቃ በጥበቃ ላይ ዕጣ ወጣ። 17 በምሥራቅ በኩል ለየዕለቱ ስድስት፥ በሰሜን በኩል ለየዕለቱ አራት፥ በደቡብ በኩል ለየዕለቱ አራት፥ ለዕቃ ቤትም ሁለት ሁለት ነበሩ። 18 በኦሳም በምዕራብ በኩል በሸለኬት በር ሦስት፥ በምሥራቅ በኩል በዐቀበቱ በር ከጥበቃ በላይ ጥበቃ በቀን ስድስት፥ በሰሜን በኩል አራት፥ በደቡብ በኩል አራት፥ በዕቃ ቤቱ በኩል ተቀባባዮች ሁለት ሁለት፥ በምዕራብ በኩል አራት በመተላለፊያውም መንገድ ተቀባባዮች ሁለት ሁለት። 19 ከቆሬና ከሜራሪ ልጆች የነበሩ የበረኞች ሰሞን ይህች ናት። 20 ወንድሞቻቸው ሌዋውያንም በእግዚአብሔር ቤት በሚሆኑ ቤተ መዛግብትና በንዋየ ቅድሳቱ ቤተ መዛግብት ላይ ተሹመው ነበር። 21 የለአዳን ልጆች፤ ለለአዳን የሆኑ የጌድሶናውያን ልጆች፥ ለጌድሶናዊው ለለአዳን የሆኑ፥ የአባቶች ቤቶች አለቆች ይሔኤሊ፤ 22 የይሔኤሊ ልጆች፤ በእግዚአብሔርም ቤት በሚሆኑ ቤተ መዛግብት ላይ የነበሩ ዜቶም፥ ወንድሙም ኢዮኤል ነበረ። 23 ከእንበረማውያን፥ ከይስዓራውያን፥ ከኬብሮናውያን፥ ከዑዝኤላውያን፤ 24 የሙሴ ልጅ የጌርሳም ልጅ ሱባኤል በቤተ መዛግብት ላይ ተሾሞ ነበር። 25 ወንድሞቹም፤ ከአልዓዛር ልጁ ረዓብያ፥ ልጁም የሳያ፥ ልጁም ኢዮራም፥ ልጁም ዝክሪ፥ ልጁም ሰሎሚት ነበሩ። 26 ይህ ሰሎሚትና ወንድሞቹ፥ ንጉሡ ዳዊትና የአባቶች ቤቶች አለቆች፥ ሻለቆችና የመቶ አለቆች፥ የሠራዊቱም አለቆች፥ በቀደሱት በንዋየ ቅድሳቱ ቤተ መዛግብት ሁሉ ላይ ተሹመው ነበር። 27 የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሕንጻ ወደ ኋላ እንዳይል ዳዊት ከየሀገሩ በማረካቸውና በሰበሰባቸው በቀደሳቸውም ላይ የተሾሙ ናቸው። 28 ነቢዩ ሳሙኤል፥ የቂስም ልጅ ሳኦል፥ የኔርም ልጅ አበኔር፥ የሶርህያም ልጅ ኢዮአብ የቀደሱት የእግዚአብሔር ንዋየ ቅድሳት ሁሉ ከሰሎሚትና ከወንድሞቹ እጅ በታች ነበረ። 29 ከይሰዓራውያን ከናንያና ልጆቹ ጻፎችና ፈራጆች ይሆኑ ዘንድ በውጭው ሥራ በእስራኤል ላይ ተሾመው ነበር። 30 ከኬብሮናውያን ሐሳብያና ወንድሞቹ፥ ጽኑዓን የነበሩት ሺህ ሰባት መቶ ሰዎች፥ ለእግዚአብሔር ሥራ ሁሉ፥ ለንጉሡም አገልግሎት በዮርዳኖስ ማዶ በምዕራብ በኩል ባለው በእስራኤል ላይ ተሾመው ነበር። 31 ከኬብሮናውያንም እንደ አባቶች ቤቶች ትውልዶች የኬብሮናውያን አለቃ ኤርያስ ነበረ። ዳዊት በነገሠ በአርባኛው ዓመት ይፈልጉአቸው ነበረ፤ በእነርሱም መካከል በገለዓድ ኢያዜር ጽኑዓን ኀያላን ሰዎች ተገኙ፤ 32 ወንድሞቹም ጽኑዓን የነበሩት የአባቶች ቤቶች አለቆች ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። ንጉሡም ዳዊት በእግዚአብሔር ቃል ሁሉና በንጉሡ ትእዛዝ ሁሉ በሮቤላውያንና በጋዳውያን፥ በምናሴም ነገድ እኩሌታ ላይ ሹሞች አደረጋቸው። |