1 ዜና መዋዕል 21 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ዳዊት የእስራኤልን ሕዝብ እንደ ቈጠረ ( 2ሳሙ. 24፥1-25 ) 1 ያንጊዜም ሰይጣን በእስራኤል ላይ ተነሣ፤ እስራኤልንም ይቈጥር ዘንድ ዳዊትን አነሣሣው። 2 ዳዊትም ኢዮአብንና የሕዝቡን አለቆች ሁሉ፥ “ሂዱ፥ ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ዳን ድረስ እስራኤልን ቍጠሩ፤ ድምራቸውንም አውቅ ዘንድ አስታውቁኝ” አላቸው። 3 ኢዮአብም፥ “እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ አሁን ባለበት መቶ እጥፍ ይጨምር፤ የጌታዬ የንጉሥ ዐይኖችም ይዩ፤ ሁሉም የጌታዬ አገልጋዮች ናቸው፤ በእስራኤል ላይ በደል ይሆን ዘንድ ይህን ነገር ጌታዬ ለምን ይሻል?” አለ። 4 ነገር ግን የንጉሡ ቃል በኢዮአብ ላይ አሸነፈ፤ ኢዮአብም ወጥቶ በእስራኤል ሁሉ ላይ ተዘዋወረ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም መጣ። 5 ኢዮአብም የቈጠራቸውን የሕዝቡን ድምር ለዳዊት ሰጠ፤ ከእስራኤልም ሁሉ አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎች ተገኙ፤ ከይሁዳም አራት መቶ ሰባ ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎች ተገኙ። 6 የንጉሡ ትእዛዝ ግን በኢዮአብ ዘንድ የተጠላ ነበረና ሌዊና ብንያም ከእነርሱ ጋር አልተቈጠሩም። 7 ይህም ነገር በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሆነ፤ በእስራኤልም ላይ መቅሠፍትን አመጣ። 8 ዳዊትም እግዚአብሔርን፥ “ይህን በማድረግ እጅግ በድያለሁ፤ አሁንም ታላቅ ስንፍና አድርጌአለሁና የባሪያህን ኀጢአት ታስወግድ ዘንድ እለምንሃለሁ” አለው። 9 እግዚአብሔርም ለነቢዩ ለጋድ እንዲህ አለው፦ 10 “ሂድ፥ ለዳዊት፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሦስቱን ነገሮች በፊትህ አኖራለሁ፤ አደርግብህ ዘንድ ከእነርሱ አንዱን ምረጥ ብለህ ንገረው።” 11 ጋድም ወደ ዳዊት መጥቶ፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የምትወድደውን ምረጥ። 12 የሦስት ዓመት ራብ፥ ወይም ሦስት ወር የጠላቶችህ ሰይፍ እንዲያገኝህ ከጠላቶችህ መሰደድን፥ ወይም ሦስት ቀን የእግዚአብሔር ሰይፍ፥ ቸነፈርም በምድር ላይ መሆንን፥ የእግዚአብሔርም መልአክ በእስራኤል ምድር ሁሉ ማጥፋትን ምረጥ፤ አሁንም ለላከኝ ምን እንደምመልስ አስረዳኝ” አለው። 13 ዳዊትም ጋድን፥ “እነዚህ ሦስት ነገሮች እጅግ ይከብዱኛል፥ እጅግም ተጨንቄአለሁ፤ አሁንም ምሕረቱ ብዙ ነውና በእግዚአብሔር እጅ መውደቅ ይሻለኛል፤ በሰው እጅ ግን አልውደቅ” አለው። 14 እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ቸነፈርን ሰደደ፤ ከእስራኤልም ሰባ ሺህ ሰዎች ወደቁ። 15 እግዚአብሔርም ያጠፋት ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም መልአክን ሰደደ፤ ሊያጠፋትም በቀረበ ጊዜ እግዚአብሔር አይቶ ከመቅሠፍቱ ይቅር አለ፤ የሚያጠፋውንም መልአክ፥ “በቃህ፤ አሁን እጅህን መልስ” አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር። 16 ዳዊትም ዐይኖቹን አነሣ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ በምድርና በሰማይ መካከል ቆሞ፥ የተመዘዘም ሰይፍ በእጁ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ተዘርግቶ አየ። ዳዊትና ሽማግሌዎቹም ማቅ ለብሰው በግንባራቸው ተደፉ። 17 ዳዊትም እግዚአብሔርን፥ “ሕዝቡ ይቈጠር ዘንድ ያዘዝሁ እኔ አይደለሁምን? የበደልሁና ክፉ የሠራሁ እኔ ነኝ፤ እነዚህ በጎች ግን ምን አድርገዋል? አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ትሁን፤ ነገር ግን አቤቱ በሕዝብህ ላይ ለጥፋት አትሁን” አለው። 18 የእግዚአብሔርም መልአክ ዳዊት ወጥቶ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ ላይ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ይሠራ ዘንድ ለዳዊት እንዲነግረው ጋድን አዘዘው። 19 ዳዊትም በእግዚአብሔር ስም እንደ ተናገረው እንደ ጋድ ነገር ወጣ። 20 ኦርናም ዘወር ብሎ ንጉሡ ዳዊትን፥ ከእርሱም ጋር ተሸሽገው የነበሩ አራቱን ብላቴኖቹን አየ። ኦርናም ስንዴ ያበራይ ነበር። 21 ዳዊትም ወደ ኦርና መጣ፤ ኦርናም ከአውድማው ወጥቶ ዳዊትን ተቀበለው። በምድርም ላይ ወድቆ ሰገደለት። 22 ዳዊትም ኦርናን፥ “በላዩ ለእግዚአብሔር መሠዊያ እሠራ ዘንድ ይህን የአውድማ ስፍራ ስጠኝ፤ በሙሉ ዋጋ ሽጥልኝ፤ መቅሠፍቱም ከሕዝቤ ይከለከላል” አለው። 23 ኦርናም ዳዊትን፥ “ለአንተ ውሰደው፤ ጌታዬ ንጉሡም በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን ያድርግ፤ እነሆ፥ ለሚቃጠለው መሥዋዕት በሬዎቹን፥ ለእንጨትም የአውድማውን ዕቃ፥ ለእህልም ቍርባን ስንዴውን እሰጥሀለሁ፥ ሁሉን እሰጣለሁ” አለው። 24 ንጉሡም ዳዊት ኦርናን፥ “አይደለም፥ ነገር ግን ለአንተ ያለውን ለእግዚአብሔር አምጥቼ የሚቃጠል መሥዋዕት በከንቱ አላቀርብምና በተገቢው ዋጋ እገዛዋለሁ” አለው። 25 ዳዊትም ስለ ስፍራው ስድስት መቶ ሰቅል ወርቅ በሚዛን ለኦርና ሰጠው። 26 ዳዊትም በዚያ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱንም መሥዋዕት አቀረበ፤ እግዚአብሔርንም ጠራ፤ ከሰማይም ለሚቃጠለው መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ላይ በእሳት መለሰለት፤ እሳቱም የሚቃጠለውን መሥዋዕት በላ። 27 እግዚአብሔርም መልአኩን አዘዘው፤ ሰይፉንም በአፎቱ ከተተው። 28 በዚያም ጊዜ እግዚአብሔር በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ እንደ ሰማው ዳዊት ባየ ጊዜ፥ በዚያ መሥዋዕትን ሠዋ። 29 ሙሴም በምድረ በዳ የሠራት የእግዚአብሔር ማደሪያና ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነው መሠዊያ በዚያን ጊዜ በገባዖን ባለው በኮረብታው መስገጃ ነበሩ። 30 ዳዊት ግን ከእግዚአብሔር መልአክ ሰይፍ የተነሣ ስለ ፈራ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ወደዚያ ይሄድ ዘንድ አልቻለም። |