1 ዜና መዋዕል 19 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ዳዊት አሞናውያንንና ሶርያውያንን ድል እንደ አደረገ ( 2ሳሙ. 10፥1-19 ) 1 ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የአሞን ልጆች ንጉሥ ናዖስ ሞተ፤ ልጁም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። 2 ዳዊትም፥ “አባቱ ስላደረገልኝ ወረታ እኔ ለናዖስ ልጅ ለሐናን ቸርነት አደርጋለሁ” አለ። ዳዊትም አባቱ ስለ ሞተ ሊያጽናናው መልእክተኞችን ላከ፤ የዳዊትም አገልጋዮች ሊያጽናኑት ወደ ሐናን ወደ አሞን ልጆች ምድር መጡ። 3 የአሞን ልጆች አለቆች ግን ሐናንን፥ “ዳዊት የሚያጽናኑህን ወደ አንተ የላከ አባትህን በማክበር ነውን? አገልጋዮቹስ ከተማዪቱን ለመመርመርና ሀገሪቱንም ለመሰለል ወደ አንተ የመጡ አይደሉምን?” አሉት። 4 ሐናንም የዳዊትን አገልጋዮች ወስዶ የጢማቸውን ግማሽ አስላጫቸው፤ ልብሳቸውንም እስከ ወገባቸው ድረስ ለሁለት ቀድዶ ሰደዳቸው። 5 ሰዎችም ሄደው በሰዎቹ ላይ የተደረገውን ለዳዊት አስታወቁት። ሰዎቹም በብዙ አፍረዋልና ይቀበሏቸው ዘንድ ሰዎችን ላኩ፤ ንጉሡም፥ “ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ ተቀመጡ፥ ከዚያም በኋላ ተመለሱ” አለ። 6 የአሞንም ልጆች የዳዊት ሰዎች እንዳፈሩ ባዩ ጊዜ ሐናን የአሞን ልጆች ንጉሥ ከሶርያ መስጴጦምያ፥ ከሶርያ ሞዓካ፥ ከሱባም ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን ይቀጥሩ ዘንድ አንድ ሺህ መክሊት ብር ላከ። 7 ሠላሳ ሁለትም ሺህ ሰረገሎችን የሞዓካን ንጉሥና ሕዝቡንም ቀጠሩ፤ መጥተውም በሜድባ ፊት ለፊት ሰፈሩ። የአሞንም ልጆች ከየከተሞቻቸው ተሰብስበው ወደ ሰልፍ መጡ። 8 ዳዊትም ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮአብንና የኀያላኑን ሠራዊት ሁሉ ላከ። 9 የአሞንም ልጆች ወጥተው በከተማዪቱ በር አጠገብ ተሰለፉ፤ የመጡትም ነገሥታት ለብቻቸው በሜዳው ላይ ሰፈሩ። 10 ኢዮአብም በፊቱና በኋላው ሰልፍ እንደ ከበበው ባየ ጊዜ ከእስራኤል ጐልማሶችን መረጠ፤ እነርሱም ከሶርያውያን ጋር ተዋጉ። 11 የቀረውንም ሕዝብ ለወንድሙ ለአቢሳ ሰጠው፤ እነርሱም በአሞን ልጆች ላይ ተሰለፉ። 12 ኢዮአብም፥ “ሶርያውያን ቢበረቱብኝ ርዳኝ፤ የአሞንም ልጆች ቢበረቱብህ እረዳሃለሁ። 13 አይዞህ፥ በርታ፤ ስለ ሕዝባችንና ስለ አምላካችንም ከተሞች እንበርታ፤ እግዚአብሔርም በፊቱ ደስ ያሰኘውን ያድርግ” አለ። 14 ኢዮአብና ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ከሶርያውያን ጋር ተዋጉ፤ እነርሱም ከፊታቸው ሸሹ። 15 የአሞንም ልጆች ሶርያውያን ከኢዮአብ ፊት እንደ ሸሹ ባዩ ጊዜ እነርሱ ደግሞ ከወንድሙ ከአቢሳ ፊት ሸሹ፤ ወደ ከተማዪቱም ገቡ። ኢዮአብም ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። 16 ሶርያውያንም እስራኤል ድል እንዳደረጓቸው ባዩ ጊዜ መልእክተኞችን ልከው በወንዝ ማዶ የነበሩትን ሶርያውያን አስመጡ፤ የአድርአዛርም ሠራዊት አለቃ ሶፋክ በፊታቸው ነበረ። 17 ዳዊትም በተነገረው ጊዜ እስራኤልን ሁሉ ሰበሰበ፤ ዮርዳኖስንም ተሻግሮ መጣባቸው፥ ከእነርሱም ጋር ተዋጋ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን ጋር ተዋጋ፥ እነርሱም ከእርሱ ጋር ተዋጉ። 18 ሶርያውያንም ከዳዊት ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን ሰባት ሺህ ሰረገለኞችን፥ አርባ ሺህም እግረኞችን ገደለ፥ የሠራዊቱንም አለቃ ሶፋክን ገደለ። 19 የአድርአዛርም አገልጋዮች በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ ከዳዊት ጋር ታረቁ፤ ተገዙለትም፤ ሶርያውያንም ከዚያ ወዲያ የአሞንን ልጆች ይረዱ ዘንድ እንቢ አሉ። |