1 ዜና መዋዕል 17 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ነቢዩ ናታን ለንጉሥ ዳዊት የነገረው ቃል ( 2ሳሙ. 7፥1-17 ) 1 እንዲህም ሆነ፤ ዳዊት በቤቱ በተቀመጠ ጊዜ ዳዊት ነቢዩ ናታንን፥ “እነሆ፥ ከዝግባ በተሠራ ቤት ተቀምጫለሁ፤ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ግን በመጋረጃዎች ውስጥ ተቀምጣለች” አለው። 2 ናታንም ዳዊትን፥ “እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና በልብህ ያለውን ሁሉ አድርግ” አለው። 3 በዚያም ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን መጣ፤ እንዲህም አለው፦ 4 “ሂድ፥ ለአገልጋዬ ለዳዊት ንገረው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በውስጡ እኖርበት ዘንድ ቤትን የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም፤ 5 ሕዝቤን እስራኤልን ከግብፅ ምድር ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በድንኳንና በማደሪያ ኖርሁ እንጂ በቤት ውስጥ አልኖርሁም። 6 ከእስራኤል ሁሉ ጋር ባለፍሁበት ስፍራ ሁሉ፥ ስለ ምን ቤትን ከዝግባ እንጨት አልሠራችሁልኝም? ብዬ ሕዝቤን ይጠብቅ ዘንድ ከእስራኤል ፈራጆች ላዘዝሁት ለአንዱ በውኑ ተናግሬአለሁን? 7 አሁንም አገልጋዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፦ ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አንተ መንጋውን ስትከተል በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ ከበግ ጥበቃ መርጬ ወሰድሁህ። 8 በሄድህበትም ሁሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ፥ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁ፤ በምድርም ላይ እንዳሉ እንደ ታላላቆች ስም ለአንተ ስምን አደረግሁ። 9 ለሕዝቤም ለእስራኤል ስፍራ አደርግለታለሁ፥ በዚያም እተክለዋለሁ፥ በስፍራውም ይቀመጣል፤ ከዚያም በኋላ አይናወጥም፤ የኀጢአትም ልጆች እንደ ቀድሞው አያስጨንቁትም፤ 10 በሕዝቤም በእስራኤል ላይ ፈራጆችን ካስነሣሁበት ጊዜ ጀምሮ ጠላቶችህን ሁሉ አዋርዳቸዋለሁ፤ አንተንም ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ። እግዚአብሔር ደግሞ ቤትን ይሠራልሃል። 11 ወደ አባቶችህም ትሄድ ዘንድ ዕድሜህ በተፈጸመ ጊዜ ከአብራክህ የተወለደ ዘርህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ። 12 እርሱ ቤትን ይሠራልኛል ፤ ዙፋኑንም ለዘለዓለም አጸናለሁ። 13 እኔም አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆነኛል፤ ከአንተ አስቀድሞ ከነበሩት እንዳራቅሁ፥ ምሕረቴን ከእርሱ አላርቅም። 14 ለቤቴም ታማኝ አደርገዋለሁ መንግሥቱም ለዘለዓለም ነው፤ ዙፋኑም ለዘለዓለም ይጸናል።” 15 እንደዚህ ነገር ሁሉ እንደዚህም ራእይ ሁሉ ነቢዩ ናታን ለዳዊት ነገረው። የዳዊት የምስጋና ጸሎት ( 2ሳሙ. 7፥18-29 ) 16 ንጉሡም ዳዊት ገባ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ፥ “አቤቱ አምላክ ሆይ፥ ለዘለዓም የወደድኸኝ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድን ነው? 17 አምላክ ሆይ፥ ይህ በፊትህ ጥቂት ነበረ፤ ስለ አገልጋይህ ቤት ደግሞ ለሩቅ ዘመን ተናገርህ፤ እንደ አንድ ባለ ማዕረግ ሰው ተመለከትኸኝ። አቤቱ፥ አምላክ ሆይ፥ ከፍ ከፍ አደረግኸኝ። 18 አንተ ባሪያህን ታውቀዋለህና ለባሪያህ ስለ ተደረገው ክብር ዳዊት ጨምሮ የሚለው ምንድን ነው? 19 እንደ ልብህም ይህን ታላቅ ነገር ሁሉ ለእኔ አደረግህ። 20 አቤቱ፥ እንዳንተ ያለ የለም፤ በጆሮአችንም እንደ ሰማን ሁሉ ከአንተ በቀር አምላክ የለም። 21 አንተ እግዚአብሔር ከግብፅ ካወጣኸው ከሕዝብህ ፊት አሕዛብን በማሳደድ ታላቅና የከበረ ስምን ለአንተ ታደርግ ዘንድ፥ ለአንተም ሕዝብ ትቤዥ ዘንድ እንደ መራኸው እንደ አንተ ሕዝብ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ሌላ ሕዝብ የለም። 22 ሕዝብህንም እስራኤልን ለዘለዓለም ሕዝብህ አደረግኸው፤ አንተም አቤቱ፥ አምላክ ሆንሃቸው። 23 አሁንም፥ አቤቱ፥ ስለ ባሪያህና ስለ ቤቱ የተናገርኸው ቃል ለዘለዓለም የታመነ ይሁን፤ እንደ ተናገርህም አድርግ። 24 ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር እርሱ የእስራኤል አምላክ ነው፤ በእውነት የእስራኤል አምላክ ነው ይባል ዘንድ ስምህ ለዘለዓለም ጽኑና ታላቅ ይሁን፤ የአገልጋይህም የዳዊት ቤት በፊትህ የጸና ይሁን። 25 አምላኬ ሆይ፥ ቤት እንድትሠራለት ለባሪያህ በጆሮው ገልጠሃልና ስለዚህ አገልጋይህ ወደ አንተ ይጸልይ ዘንድ ባለሟልነትን አገኘ። 26 አሁንም፥ አቤቱ፥ አንተ አምላክ ነህ፤ ይህንም መልካም ነገር ለባሪያህ ተናግረሃል። 27 አሁንም በፊትህ ለዘለዓለም ይኖር ዘንድ የአገልጋይህን ቤት ትባርክ ዘንድ ጀምረሃል፤ አንተም አቤቱ፥ ባርከኸዋል፤ ለዘለዓለምም ቡሩክ ይሆናል።” |