1 ዜና መዋዕል 15 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእግዚአብሔርን ታቦት ለማምጣት የተደረገ ዝግጅት 1 ዳዊትም በከተማው ለራሱ ቤቶችን ሠራ፤ ለእግዚአብሔርም ታቦት ስፍራ አዘጋጀ፤ ድንኳንም ተከለላት። 2 በዚያን ጊዜም ዳዊት፥ “የእግዚአብሔርን ታቦት ይሸከሙ ዘንድ፥ ለዘለዓለሙም ያገለግሉት ዘንድ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ከሌዋውያን በቀር ማንም የእግዚአብሔርን ታቦት ይሸከም ዘንድ አይገባውም” አለ። 3 ዳዊትም ወዳዘጋጀላት ስፍራ የእግዚአብሔርን ታቦት ያመጣ ዘንድ እስራኤልን ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ። 4 ዳዊትም የአሮንን ልጆችና ሌዋውያንን ሰበሰበ። 5 ከቀዓት ልጆች፤ አለቃው ኡርኤል፥ ወንድሞቹም መቶ ሃያ፤ 6 ከሜራሪ ልጆችም፤ አለቃው ዓሣያ፥ ወንድሞቹም ሁለት መቶ ኀምሳ፤ 7 ከጌድሶን ልጆች፤ አለቃው ኢዮሔት፥ ወንድሞቹም መቶ ሠላሳ፤ 8 ከኤልሳፋን ልጆች፤ አለቃው ሰማያ፥ ወንድሞቹም ሁለት መቶ፤ 9 ከኬብሮን ልጆች፤ አለቃው ኢዮሔል፥ ወንድሞቹም ሰማንያ፤ 10 ከዑዝኤል ልጆች፤ አለቃው አሚናዳብ፥ ወንድሞቹም መቶ ዐሥራ ሁለት። 11 ዳዊትም ካህናቱን ሳዶቅንና አብያታርን፥ ሌዋውያንንም፥ ኡርኤልን፥ ዓሣያን፥ ኢዮኤልን፥ ሰማያን፥ ኤሊኤልን፥ አሚናዳብንም ጠርቶ፦ 12 “እናንተ የሌዋውያን አባቶች ቤቶች አለቆች ናችሁ፤ ወዳዘጋጀሁላት ስፍራ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ታቦት ታመጡ ዘንድ እናንተና ወንድሞቻችሁ ተቀደሱ። 13 በቀድሞ ሥራችን አምላካችን እግዚአብሔር እርስ በርሳችን አላጠፋንም፤ በጦር አልፈለገንምና” አላቸው። 14 የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርን ታቦት ያመጡ ዘንድ ካህናቱና ሌዋውያኑ ራሳቸውን አነጹ። 15 በመጽሐፍም እንደ ተጻፈ ሙሴ በእግዚአብሔር ቃል እንደ አዘዛቸው የሌዋውያን ልጆች የእግዚአብሔርን ታቦት በትከሻቸው ላይ በመሎጊያዎቹ ተሸከሙ። መባእና ቍርባንም ከእነርሱ ጋር ነበረ። 16 ዳዊትም በዜማ ዕቃ፥ በመሰንቆና በበገና፥ በጸናጽልም እንዲያዜሙ፥ ድምፃቸውንም በደስታ ከፍ እንዲያደርጉ መዘምራኑን “ወንድሞቻችሁን ሹሙ” ብሎ ለሌዋውያን አለቆች ተናገረ። 17 ሌዋውያኑም የኢዩኤልን ልጅ ኤማንን፥ ከወንድሞቹም የበራክያን ልጅ አሳፍን፥ ከወንድሞቻቸውም ከሜራሪ ልጆች የቂሳንን ልጅ ኢታንን፥ 18 ከእነርሱም ጋር በሁለተኛው ተራ የሆኑትን ወንድሞቻቸውን ዘካርያስን፥ ቤንን፥ አዝኤልን፥ ስሜራሞትን፥ ኢያሄልን፥ ኡኒን፥ ኤልያብን፥ በናእያን፥ መዕሤያን፥ መታትያን፥ ኤልፋይን፥ ሜቄድያን፥ በረኞችንም አብዲዶምን፥ ኢያኤልንና ዖዝያስን አቆሙ። 19 መዘምራንም ኤማንና አሳፍ ኤታንም በናስ ጸናጽል ከፍ አድርገው ያሰሙ ነበር። 20 ዘካርያስ፥ አዝኤል፥ ሰሚራሞት፥ ኢያሔል፥ ዑኒ፥ ኤልያብ፥ መዕሤያ፥ በናያስ በመሰንቆ በልዑል ቃል ያዜሙ ነበር። 21 ማታትያስ፥ ኤልፋላይ፥ ሜቄድያስ፥ አብዴዶም፥ ይዒኤል፥ ዖዝያስም ስምንት አውታር ባለው በገና ይዘምሩ ነበር። 22 የሌዋውያኑም አለቃ ኮነንያስ በዜማ ላይ ተሾሞ ነበር። ብልሃተኛ ነበረና። 23 በራክያና ሕልቃናም ለታቦቷ በረኞች ነበሩ። 24 ካህናቱም ሰበንያ፥ ኢዮሣፍጥ፥ ናትናኤል፥ ዓማሣይ፥ ዘካርያስ፥ በናያስ፥ አልዓዛርም በእግዚአብሔር ታቦት ፊት መለከት ይነፉ ነበር። አብዲዶምና ኢያኤያም የእግዚአብሔር ታቦት በረኞች ነበሩ። 25 ዳዊትም፥ የእስራኤልም ሽማግሌዎች፥ የሻለቆችም የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከአቢዳራ ቤት በደስታ ያመጡ ዘንድ ሄዱ። 26 የእግዚአብሔርንም ቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙትን ሌዋውያንን እግዚአብሔር በአበረታቸው ጊዜ ሰባት በሬዎችንና ሰባት አውራ በጎችን ሠዉ። 27 ዳዊትም፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ሌዋውያንም ሁሉ፥ መዘምራኑም፥ የመዘምራኑም አለቃ ኮኖንያስ የጥሩ በፍታ ቀሚስ ለብሰው ነበር፤ ዳዊትም የከበረ ልብስ ለብሶ ነበረ። 28 እንዲሁ እስራኤል ሁሉ በይባቤ፥ ቀንደ መለከትና እንቢልታ እየነፉ፥ ጸናጽልና መሰንቆም፥ በገናም እየመቱ፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት አመጡ። 29 የእግዚአብሔርም ቃል ኪዳን ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በደረሰች ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፤ ንጉሡም ዳዊት ሲዘፍንና ሲጫወት አይታ በልብዋ ናቀችው። |