ሶፎንያስ 2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምይሁዳና ኢየሩሳሌም ከሌሎች ሕዝቦች ጋራ ተፈረደባቸው ይሁዳ ለንስሓ ተጠራ 1 እናንተ ዕፍረት የሌላችሁ ሕዝብ ሆይ፤ በአንድነት ተሰብሰቡ፤ ተከማቹም፤ 2 የተወሰነው ጊዜ ሳይደርስ፣ ቀኑ እንደ ገለባ ሳይጠራርጋችሁ፣ የእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ በእናንተ ላይ ሳይመጣ፣ የእግዚአብሔር የመዓት ቀን ሳይደርስባችሁ ተሰብሰቡ። 3 እናንተ የምድር ትሑታን ሁሉ፣ ትእዛዙን የምትፈጽሙ፣ እግዚአብሔርን እሹ፤ ጽድቅንና ትሕትናን ፈልጉ፤ በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን፣ ትሰወሩ ይሆናል። በፍልስጥኤም ላይ የተነገረ ጥፋት 4 ጋዛ ባድማ ትሆናለች፤ አስቀሎናም ፈራርሳ ትቀራለች፤ አዛጦን በቀትር ባዶ ትሆናለች፤ አቃሮንም ትነቀላለች። 5 እናንተ በባሕር ዳርቻ የምትኖሩ፣ የከሊታውያን ሰዎች ሆይ፤ ወዮላችሁ! የፍልስጥኤማውያን ምድር ከነዓን ሆይ፤ በአንቺ ላይ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤ “ፍጹም አጠፋሻለሁ፤ ከነዋሪዎችሽም የሚተርፍ የለም።” 6 የቀርጤስ ሰዎች የሚኖሩበት በባሕሩ ዳር ያለው ምድር፣ የእረኞች መኖሪያና የበጎች በረት ይሆናል፤ 7 ይህም ለይሁዳ ቤት ትሩፍ ይሰጣል፤ እነርሱም በዚያ መሰማሪያ ያገኛሉ። በአስቀሎና ቤቶች ውስጥም በምሽት ይተኛሉ፤ አምላካቸው እግዚአብሔር ይጐበኛቸዋል፤ ምርኳቸውንም ይመልስላቸዋል። በሞዓብና በአሞን ላይ የተነገረ ጥፋት 8 “የሞዓብን ስድብ፣ የአሞናውያንንም ፌዝ ሰምቻለሁ፤ ሕዝቤን ሰድበዋል፤ በምድራቸውም ላይ ዝተዋል።” 9 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በሕያውነቴ እምላለሁ፤ ሞዓብ እንደ ሰዶም፣ አሞናውያን እንደ ገሞራ፣ ዐረም እንደ ዋጠው ቦታና እንደ ጨው ጕድጓድ ለዘላለም ጠፍ ይሆናሉ። ከሕዝቤ የቀሩት ይዘርፏቸዋል፤ ከወገኔ የተረፉትም ምድራቸውን ይወርሳሉ።” 10 ከትዕቢታቸው የተነሣ የሚደርስባቸው ይህ ነው፤ የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ሰድበው ዘብተውበታልና፣ 11 እግዚአብሔር የምድሪቱን አማልክት ሁሉ በሚደመስስበት ጊዜ፣ በእነርሱ ዘንድ የተፈራ ይሆናል፤ በየባሕሩ ጠረፍ የሚኖሩ ሕዝቦች፣ እያንዳንዳቸው በያሉበት ሆነው ለርሱ ይሰግዳሉ። በኢትዮጵያ ላይ የተነገረ ጥፋት 12 “ኢትዮጵያውያን ሆይ፤ እናንተም፣ በሰይፌ ትገደላላችሁ።” በአሦር ላይ የተነገረ ጥፋት 13 እጁን በሰሜን ላይ ይዘረጋል፤ አሦርንም ያጠፋል፤ ነነዌን ፍጹም ባድማ፣ እንደ ምድረ በዳም ደረቅ ያደርጋታል። 14 የበግና የከብት መንጋዎች፣ የፍጥረት ዐይነት ሁሉ በውስጧ ይመሰጋሉ፤ ጕጕትና ጃርት፣ በግንቦቿ ላይ ያድራሉ። ጩኸታቸው በየመስኮቱ ያስተጋባል፤ ፍርስራሽ በየደጃፉ ይከመራል፤ ከዝግባ የተሠሩ ተሸካሚዎችም ይገለጣሉ። 15 ያለ ሥጋት የኖረች፣ ደስተኛዪቱ ከተማ ይህች ናት፤ እርሷም በልቧ፣ “እኔ ብቻ ነኝ! ከእኔ በቀር ማንም የለም” ያለች፣ ታዲያ እንዴት የዱር አራዊት የሚመሰጉባት፣ ባድማ ሆና ቀረች? በአጠገቧ የሚያልፉ ሁሉ፣ ያፌዙባታል፤ እጃቸውንም በንቀት ያወዛውዙባታል። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.