ሶፎንያስ 1 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 በይሁዳ ንጉሥ በአሞን ልጅ በኢዮስያስ ዘመን ወደ ሕዝቅያስ ልጅ፣ ወደ አማርያ ልጅ፣ ወደ ጎዶልያስ ልጅ፣ ወደ ኵሲ ልጅ ወደ ሶፎንያስ የመጣ የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤ ስለሚመጣው ጥፋት የተሰጠ ማስጠንቀቂያ 2 “ማንኛውንም ነገር፣ ከምድር ገጽ አጠፋለሁ” ይላል እግዚአብሔር። 3 “ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፤ የሰማይን ወፎች፣ የባሕርንም ዓሦች አጠፋለሁ፤ ለክፉዎችም እንቅፋት የሆኑትን ጣዖታት አጠፋለሁ።” “ማንኛውንም ሰው ከምድር ገጽ አስወግዳለሁ” ይላል እግዚአብሔር። በይሁዳ ላይ የተነገረ ጥፋት 4 “እጄን በይሁዳ፣ በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ሁሉ ላይ አነሣለሁ፤ የበኣልን ትሩፍ፣ የጣዖታቱንና የአመንዝራ ካህናቱን ስም ሁሉ ከዚህ ስፍራ አጠፋለሁ፤ 5 የሰማይን ሰራዊት ለማምለክ፣ በሰገነት ላይ ወጥተው የሚሰግዱትን፣ ለእግዚአብሔር እየሰገዱ፣ በስሙም እየማሉ፣ በሚልኮምም ደግሞ የሚምሉትን፣ 6 እግዚአብሔርን ከመከተል ወደ ኋላ የሚመለሱትን፣ እግዚአብሔርን የማይፈልጉትን፣ እንዲረዳቸውም የማይጠይቁትን አጠፋለሁ።” 7 በጌታ እግዚአብሔር ፊት ዝም በሉ፤ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቧልና። እግዚአብሔር መሥዋዕት አዘጋጅቷል፤ የጠራቸውንም ቀድሷል። 8 “በእግዚአብሔር የመሥዋዕት ቀን፣ መሳፍንቱንና የንጉሡን ልጆች፣ እንግዳ ልብስ የሚለብሱትን ሁሉ እቀጣለሁ። 9 በዚያ ቀን፣ በመድረኩ ላይ የሚዘልሉትን ሁሉ፣ የአማልክታቸውን ቤት፣ በዐመፅና በማጭበርበር የሚሞሉትን እቀጣለሁ።” 10 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በዚያ ቀን ‘ከዓሣ በር’ ጩኸት በሁለተኛው አደባባይ ዋይታ፣ ከኰረብቶችም ታላቅ ሽብር ይሰማል። 11 እናንተ በመክቴሽ ገበያ የምትኖሩ ዋይ በሉ፤ ነጋዴዎቻችሁ ሁሉ ይደመሰሳሉ፤ በብር የሚነግዱትም ሁሉ ይሞታሉ። 12 በዚያ ዘመን ኢየሩሳሌምን በመብራት እፈትሻለሁ፤ ተንደላቅቀው የሚኖሩትን፣ በዝቃጩ ላይ እንደ ቀረ የወይን ጠጅ የሆኑትን፣ ‘ክፉም ይሁን መልካም፣ እግዚአብሔር ምንም አያደርግም’ የሚሉትን ቸልተኞች እቀጣለሁ። 13 ሀብታቸው ይዘረፋል፤ ቤታቸው ይፈራርሳል፤ ቤቶች ይሠራሉ፤ ነገር ግን አይኖሩባቸውም፤ ወይን ይተክላሉ፤ ጠጁን ግን አይጠጡም።” ታላቁ የ እግዚአብሔር ቀን 14 “ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ ነው፤ ቅርብ ነው ፈጥኖም ይመጣል፤ በእግዚአብሔር ቀን የሚሰማው ልቅሶ መራራ ነው፤ በዚያ ጦረኛውም ምርር ብሎ ይጮኻል፤ 15 ያ ቀን የመዓት ቀን፣ የመከራና የጭንቀት ቀን፣ የሁከትና የጥፋት ቀን፣ የጨለማና የጭጋግ ቀን፣ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ይሆናል፤ 16 ያ ቀን በተመሸጉ ከተሞችና፣ በረዣዥም ግንቦች ላይ፣ የመለከት ድምፅና የጦርነት ጩኸት የሚሰማበት ቀን ይሆናል። 17 “እንደ ዕውር እንዲራመዱ፣ በሰዎች ላይ ጭንቀት አመጣባቸዋለሁ፤ በእግዚአብሔር ላይ ኀጢአትን ሠርተዋልና። ደማቸው እንደ ትቢያ፣ ሥጋቸውም እንደ ጕድፍ ይጣላል። 18 በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን፣ ብራቸውም ሆነ ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም።” መላዪቱ ምድር፣ በቅናቱ ትበላለች፤ በምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ፣ ድንገተኛ ፍጻሜ ያመጣባቸዋልና። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.