ዘካርያስ 6 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምአራቱ ሠረገሎች 1 እንደ ገናም ወደ ላይ ተመለከትሁ፤ እነሆ አራት ሠረገሎች ከሁለት ተራራ መካከል ሲወጡ አየሁ፤ ተራሮቹም የናስ ተራሮች ነበሩ። 2 የመጀመሪያው ሠረገላ ቀይ ፈረስ፣ ሁለተኛው ጥቍር ፈረስ፤ 3 ሦስተኛው ነጭ፣ አራተኛውም ዝጕርጕር ፈረሶች ነበሯቸው፤ ሁሉም ጠንካሮች ነበሩ። 4 እኔም፣ ከእኔ ጋራ ይነጋገር የነበረውን መልአክ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እነዚህ ምንድን ናቸው?” አልሁት። 5 መልአኩም እንዲህ አለኝ፤ “እነዚህ አራቱ ቆመው ከነበሩበት ከምድር ሁሉ ጌታ ፊት የወጡ የሰማይ መናፍስት ናቸው። 6 የባለ ጥቍር ፈረሶች ወደ ሰሜን፤ የባለ ነጭ ፈረሶች ወደ ምዕራብ አገር፣ የባለዝጕርጕር ፈረሶች ወደ ደቡብ አገር ይወጣል።” 7 ጠንካሮቹ ፈረሶች ሲወጡ፣ በምድር ሁሉ ለመመላለስ አቈብቍበው ነበር። እርሱም፣ “ወደ ምድር ሁሉ ሂዱ” አላቸው፤ እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ ሄዱ። 8 ከዚያም ጮኾ እንዲህ አለኝ፤ “እነሆ፤ ወደ ሰሜን አገር የሚወጡት፣ መንፈሴን በሰሜን ምድር አሳርፈውታል።” ለኢያሱ የተደረገለት አክሊል 9 ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 10 “ከባቢሎን ከመጡት ምርኮኞች ከሔልዳይና ከጦብያ፣ ከዮዳኤም ወርቅና ብር ውሰድ፤ በዚያው ቀን ወደ ሶፎንያስ ልጅ ወደ ኢዮስያስ ቤት ሂድ። 11 ወርቁንና ብሩን ወስደህ አክሊል ሥራ፤ በኢዮሴዴቅ ልጅ በሊቀ ካህኑ በኢያሱ ራስ ላይም አድርገው፤ 12 ለርሱም የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገረው፤ ‘እነሆ፤ ስሙ ቅርንጫፍ የተባለው ሰው ይህ ነው፤ እርሱም በቦታው ይንሰራፋል፤ የእግዚአብሔርንም ቤተ መቅደስ ይሠራል። 13 የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሚሠራው እርሱ ነው፤ ክብርን ይጐናጸፋል፤ በዙፋኑ ተቀምጦ ይገዛል፤ በዙፋኑም ላይ ካህን ይሆናል፤ በሁለቱም መካከል የሰላም ምክር ይኖራል።’ 14 አክሊሉም ለሔሌምና ለጦብያ፣ ለዮዳኤና ለሶፎንያስ ልጅ ለሔን በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ መታሰቢያ ይሆናል። 15 እነዚያ በሩቅ ያሉት መጥተው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሲሠራ ያግዛሉ፤ እናንተም የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር በጥንቃቄ ብትታዘዙ ይህ ይሆናል።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.