ዘካርያስ 5 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምበራሪው የመጽሐፍ ጥቅልል 1 እንደ ገናም ተመለከትሁ፤ በዚያም በፊቴ በራሪ የመጽሐፍ ጥቅልል አየሁ። 2 እርሱም፣ “ምን ታያለህ?” ሲል ጠየቀኝ። እኔም፣ “ርዝመቱ ሃያ ክንድ፣ ወርዱ ዐሥር ክንድ የሆነ በራሪ የመጽሐፍ ጥቅልል አያለሁ” አልሁት። 3 እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “ይህ በምድር ሁሉ ላይ የሚወጣ ርግማን ነው፤ በአንደኛው በኩል እንደ ተጻፈው የሚሰርቅ ሁሉ ይጠፋል፤ በሌላው በኩል ደግሞ እንደ ተጻፈው በሐሰት የሚምል ሁሉ ይጠፋልና። 4 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ‘እኔ ርግማኑን አመጣዋለሁ፤ እርሱም ወደ ሌባው ቤትና በስሜ በሐሰት ወደሚምለው ሰው ቤት ይገባል፤ በዚያም ይቀመጣል፤ ቤቱን፣ ዕንጨቱንና ድንጋዩን ያጠፋል’ ይላል።” በቅርጫት ውስጥ ያለች ሴት 5 ከዚያም ከእኔ ጋራ ይነጋገር የነበረው መልአክ ወደ እኔ መጥቶ፣ “ወደ ላይ ተመልከት፤ ይህ የሚመጣው ምን እንደ ሆነ እይ” አለኝ። 6 እኔም፣ “ምንድን ነው?” አልሁት። እርሱም፣ “የኢፍ መስፈሪያ ነው” አለኝ። ቀጥሎም “ይህ በምድሪቱ ሁሉ ላይ ያለው የሕዝቡ በደል ነው” አለኝ። 7 ከዚያም ከእርሳስ የተሠራው ክዳን ተነሣ፤ የኢፍ መስፈሪያ ውስጥ አንዲት ሴት ተቀምጣ ነበር። 8 እርሱም፣ “ይህች ርኩሰት ናት” ብሎ ወደ ኢፍ መስፈሪያ መልሶ አስገባት፤ የእርሳሱንም ክዳን ወደ ቅርጫቱ አፍ ገፍቶ ገጠመው። 9 ከዚያም ወደ ላይ ተመለከትሁ፤ እነሆም፣ ከፊቴ ሁለት ሴቶች ነበሩ፤ በክንፎቻቸውም ነፋስ ነበር፤ ክንፎቻቸውም እንደ ሽመላ ክንፎች ነበሩ፤ የኢፍ መስፈሪያውንም በምድርና በሰማይ መካከል አነሡት። 10 ከእኔ ጋራ ይነጋገር የነበረውንም መልአክ፣ “ቅርጫቱን የሚወስዱት ወዴት ነው?” አልሁት። 11 እርሱም፣ “ቤት ሊሠሩለት ወደ ባቢሎን ምድር ይወስዱታል፤ በተዘጋጀም ጊዜ ወስደው በቦታው ያስቀምጡታል” አለኝ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.