ዘካርያስ 3 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምለሊቀ ካህኑ የሚሆን ንጹሕ ልብስ 1 እርሱም ሊቀ ካህኑን ኢያሱን በእግዚአብሔር መልአክ ፊት ቆሞ፣ ሰይጣንም ሊከስሰው በስተ ቀኙ ቆሞ አሳየኝ። 2 እግዚአብሔርም ሰይጣንን፣ “አንተ ሰይጣን፤ እግዚአብሔር ይገሥጽህ፤ ኢየሩሳሌምን የመረጠ እግዚአብሔር ይገሥጽህ፤ ይህ ሰው ከእሳት የተነጠቀ ትንታግ አይደለምን?” አለው። 3 ኢያሱም ያደፈ ልብስ ለብሶ በመልአኩ ፊት ቆሞ ነበር። 4 መልአኩም ከፊቱ ቆመው የነበሩትን፣ “ያደፉ ልብሶቹን አውልቁለት” አላቸው። ኢያሱንም፣ “እነሆ፤ ኀጢአትህን ከአንተ አስወግጃለሁ፤ ጥሩ ልብስም አለብስሃለሁ” አለው። 5 እኔም፣ “ንጹሕ ጥምጥም በራሱ ላይ አድርጉለት” አልሁ። የእግዚአብሔርም መልአክ በአጠገቡ ቆሞ እያለ፣ ንጹሕ ጥምጥም በራሱ ላይ አደረጉለት፤ ልብስም አለበሱት። 6 የእግዚአብሔርም መልአክ ለኢያሱ ይህን ማስጠንቀቂያ ሰጠው፤ 7 “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በመንገዴ ብትሄድ፣ ትእዛዜንም ብትጠብቅ፣ ቤቴን ታስተዳድራለህ፤ በአደባባዮቼም ላይ ኀላፊ ትሆናለህ፤ በዚህ በቆሙት መካከል ቦታ እሰጥሃለሁ። 8 “ ‘ሊቀ ካህኑ ኢያሱ ሆይ፤ ስማ፤ በፊትህ የሚቀመጡትም ረዳቶችህ ገና ወደ ፊት ለሚመጡት ምልክት የሚሆኑ ሰዎች ናቸውና ይስሙ፤ እነሆ፤ ባሪያዬን ቍጥቋጡን አመጣለሁ። 9 በኢያሱ ፊት ያስቀመጥሁት ድንጋይ እነሆ፤ በዚያ በአንዱ ድንጋይ ላይ ሰባት ዐይኖች አሉ፤ በርሱም ላይ ቅርጽ እቀርጻለሁ፤ የዚህችንም ምድር በደል በአንድ ቀን አስወግዳለሁ’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 10 “ ‘በዚያ ቀን እያንዳንዱ በገዛ ወይኑና በለሱ ሥር ሆኖ ባልንጀራውን ይጋብዛል’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.