Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘካርያስ 14 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


እግዚአብሔር ይመጣል፤ ይነግሣልም

1 እነሆ፤ የእግዚአብሔር ቀን ይመጣል፤ ብዝበዛሽንም በውስጥሽ ይካፈላሉ።

2 ኢየሩሳሌምን እንዲወጉ አሕዛብን ሁሉ እሰበስባለሁ፤ ከተማዪቱ ትያዛለች፤ ቤቶች ይበዘበዛሉ፤ ሴቶችም ይደፈራሉ፤ የከተማዪቱ እኩሌታ ይማረካል፤ የሚቀረው ሕዝብ ግን ከከተማዪቱ አይወሰድም።

3 እግዚአብሔርም በጦርነት ጊዜ እንደሚዋጋ፣ እነዚያን አሕዛብ ሊወጋ ይወጣል።

4 በዚያ ቀን እግሮቹ ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ይቆማሉ፤ የደብረ ዘይት ተራራም ታላቅ ሸለቆን በመሥራት የተራራውን እኩሌታ ወደ ሰሜን፣ እኩሌታውንም ወደ ደቡብ በማድረግ ምሥራቅና ምዕራብ ሆኖ ለሁለት ይከፈላል፤

5 እናንተም በእግዚአብሔር ተራራ ሸለቆ በኩል በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ዘመን በምድር ትሸሻላችሁ፤ ሸለቆው እስከ አጸል ይደርሳልና። በምድር መናወጥ ምክንያት ሸሽታችሁ እንደ ነበረ ትሸሻላችሁ፤ ከዚያም አምላኬ እግዚአብሔር ይመጣል፤ ቅዱሳኑም ሁሉ ዐብረውት ይመጣሉ።

6 በዚያ ቀን በረዶ፣ ውርጭና ብርሃን አይኖርም።

7 ቀኑም የብርሃን ወይም የጨለማ ጊዜ የሌለበት ልዩ ቀን ይሆናል፤ ያም ቀን በእግዚአብሔር የታወቀ ቀን ይሆናል፤ ሲመሽም ብርሃን ይሆናል።

8 በዚያ ቀን የሕይወት ውሃ ከኢየሩሳሌም ይፈልቃል፤ እኩሌታው ወደ ምሥራቁ ባሕር፣ እኩሌታውም ወደ ምዕራቡ ባሕር ይፈስሳል፤ ይህም በበጋና በክረምት ይሆናል።

9 እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ ይነግሣል፤ በዚያ ቀን እግዚአብሔር አንድ፣ ስሙም አንድ ብቻ ይሆናል።

10 ምድር ሁሉ ከጌባዕ አንሥቶ በኢየሩሳሌም ደቡብ እስካለችው ሪሞን ድረስ ተለውጣ ደልዳላ ሜዳ ትሆናለች፤ ኢየሩሳሌም ግን ከብንያም በር እስከ መጀመሪያው በር፣ ከማእዘን በርና ከሐናንኤል ግንብ እስከ ንጉሡ የወይን ጠጅ መጥመቂያ ድረስ በዚያው በቦታዋ ላይ ከፍ እንዳለች ትኖራለች።

11 የሰው መኖሪያም ትሆናለች፤ ከቶም ዳግመኛ አትፈርስም፤ ኢየሩሳሌም ያለ ሥጋት በሰላም ትኖራለች።

12 እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን የወጓትን አሕዛብ ሁሉ የሚመታበት መቅሠፍት ይህ ነው፤ ገና በእግራቸው ቆመው ሳሉ ሥጋቸው ይበሰብሳል፤ ዐይኖቻቸው በጕድጓዶቻቸው ውስጥ እንዳሉ ይበሰብሳሉ፤ ምላሶቻቸውም በአፎቻቸው ውስጥ እንዳሉ ይበሰብሳሉ።

13 በዚያ ቀን ከእግዚአብሔር ዘንድ በሰዎች ላይ ታላቅ ሽብር ይወርዳል፤ እያንዳንዱ ሰው የባልንጀራውን እጅ ይይዛል፤ አንዱም ሌላውን ይወጋዋል።

14 ይሁዳም ደግሞ ኢየሩሳሌምን ይወጋል። በዙሪያው ያሉ የአሕዛብ ሁሉ ሀብት፣ ብዙ ወርቅ፣ ብርና ልብስ ይሰበሰባል።

15 ይህንኑ የሚመስል መቅሠፍት ፈረሶችንና በቅሎዎችን፣ ግመሎችንና አህዮችን እንዲሁም በየሰፈሩ ያሉትን እንስሳት ሁሉ ይመታል።

16 ከዚያም ኢየሩሳሌምን ከወጓት አሕዛብ ከሞት የተረፉት ሁሉ ለንጉሡ፣ ለሰራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ለመስገድና የዳስን በዓል ለማክበር በየዓመቱ ይወጣሉ።

17 የምድር ሕዝብ ሁሉ ለንጉሡ፣ ለሰራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ሊሰግዱ ወደ ኢየሩሳሌም የማይወጡ ከሆነ ዝናብ አያገኙም።

18 የግብጽም ሰዎች ወደዚያ ሳይወጡ ቢቀሩ፣ ዝናብ አያገኙም፤ እግዚአብሔር ወጥተው የዳስ በዓልን በማያከብሩ አሕዛብ ላይ የሚያደርሰውን መቅሠፍት በእነርሱም ላይ ያመጣል።

19 የዳስን በዓል ወጥተው ለማያከብሩ ግብጻውያንና አሕዛብ ሁሉ የተወሰነው ቅጣት ይህ ነው።

20 በዚያ ቀን በፈረሶች ሻኵራ ላይ፣ “ቅዱስ ለእግዚአብሔር” የሚል ጽሑፍ ይቀረጻል፤ በእግዚአብሔር ቤት ያሉ የማብሰያ ምንቸቶች ከመሠዊያው ፊት ለፊት እንዳሉ ሳሕኖች የተቀደሱ ይሆናሉ።

21 በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ያሉ ምንቸቶች ሁሉ ለሰራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር የተቀደሱ ይሆናሉ፤ መሥዋዕት ለማቅረብ የሚመጡ ሁሉ ምንቸቶቹን በመውሰድ ያበስሉባቸዋል፤ በዚያ ቀን በእግዚአብሔር ጸባኦት ቤት ከእንግዲህ ወዲያ ከነዓናዊ አይገኝም።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告