ዘካርያስ 10 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምእግዚአብሔር ለይሁዳ ይጠነቀቃል 1 የበልግ ዝናብ እንዲሰጣችሁ እግዚአብሔርን ጠይቁ፤ ማዕበሉን ደመና የሚያደርግ እግዚአብሔር ነው፤ እርሱ ለሰዎች በቂ ዝናብን፣ ለእያንዳንዱም የምድርን ተክል ይሰጣል። 2 ተራፊም አሳሳች ነገር ይናገራል፤ ሟርተኞች የሐሰት ራእይ ያያሉ፤ የውሸት ሕልም ይናገራሉ፤ ከንቱ መጽናናት ይሰጣሉ፤ ስለዚህ ሕዝቡ እንደ በጎች ተቅበዘበዙ፤ እረኛ በማጣትም ተጨነቁ። 3 “ቍጣዬ በእረኞች ላይ ነድዷል፤ መሪዎችንም እቀጣለሁ፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ መንጋውን የይሁዳ ቤት ይጐበኛልና፤ በጦርነትም ጊዜ እንደ ክብሩ ፈረስ ያደርጋቸዋል። 4 ከይሁዳ፣ የማእዘን ድንጋይ፣ የድንኳን ካስማ፣ የጦርነት ቀስት፣ ገዥም ሁሉ ይወጣል። 5 ጠላትን መንገድ ላይ እንዳለ ጭቃ ይረጋግጣሉ፤ በአንድነት እንደ ጦር ሰልፈኛ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋራ ስለ ሆነ ተዋግተው፤ ፈረሰኞችን ያዋርዳሉ። 6 “የይሁዳን ቤት አበረታለሁ፤ የዮሴፍንም ቤት እታደጋለሁ። ስለምራራላቸው፣ ወደ ቦታቸው እመልሳቸዋለሁ፤ እነርሱም በእኔ እንዳልተተዉ ሰዎች ይሆናሉ፤ እኔ አምላካቸው እግዚአብሔር ነኝና፣ ጸሎታቸውን እሰማለሁ። 7 ኤፍሬማውያን እንደ ኀያላን ሰዎች ይሆናሉ፤ ልባቸውም የወይን ጠጅ እንደ ጠጣ ሰው ሐሤት ያደርጋል። ልጆቻቸው ያዩታል፤ ደስተኛም ይሆናሉ፤ ልባቸውም በእግዚአብሔር ደስ ይለዋል። 8 በፉጨት እጠራቸዋለሁ፤ በአንድነት እሰበስባቸዋለሁ፤ በርግጥ እቤዣቸዋለሁ፤ እንደ ቀድሞው ይበዛሉ። 9 በሕዝቦች መካከል ብበትናቸውም፣ በሩቅ ምድር ሆነው ያስቡኛል፤ እነርሱና ልጆቻቸው ተርፈው፣ በሕይወት ይመለሳሉ። 10 ከግብጽ እመልሳቸዋለሁ፤ ከአሦርም እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደ ገለዓድና ወደ ሊባኖስ አመጣቸዋለሁ፤ በቂ ስፍራም አይገኝላቸውም። 11 በመከራ ባሕር ውስጥ ያልፋሉ፤ የባሕሩ ማዕበል ጸጥ ይላል፤ የአባይም ጥልቅ ሁሉ ይደርቃል። የአሦር ትምክሕት ይዋረዳል፤ የግብጽም በትረ መንግሥት ያበቃል። 12 በእግዚአብሔር አበረታቸዋለሁ፤ በስሙም ይመላለሳሉ” ይላል እግዚአብሔር። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.