ማሕልየ መሓልይ 3 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 ሌሊቱን ሙሉ በዐልጋዬ ላይ ሆኜ፣ ውዴን ተመኘሁ፤ ተመኘሁት፤ ነገር ግን አላገኘሁትም። 2 ተነሥቼ ወደ ከተማዪቱ እወጣለሁ፤ በዋና ዋና መንገዶችና በአደባባዮች እዘዋወራለሁ፤ ውዴንም እፈልገዋለሁ፤ ስለዚህም ፈለግሁት፤ ነገር ግን አላገኘሁትም። 3 በከተማዪቱ ውስጥ ሲዘዋወሩ፣ የከተማዪቱ ጠባቂዎች አገኙኝ፤ እኔም፣ “ውዴን አይታችኋል?” አልኋቸው። 4 ከእነርሱ ጥቂት ዕልፍ እንዳልሁ፣ ውዴን አገኘሁት፤ ያዝሁት፤ ወደ እናቴ ቤት እስካመጣው፣ በማሕፀን ወደ ተሸከመችኝም ዕልፍኝ እስካገባው ድረስ አልለቀውም። 5 እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት፤ ራሱ እስኪፈልግ ድረስ፣ ፍቅርን እንዳታስነሡት ወይም እንዳትቀሰቅሱት፣ በሚዳቋና በሜዳ ዋሊያ አማፅናችኋለሁ። 6 ከከርቤና ከዕጣን፣ ከነጋዴም ቅመማ ቅመም ሁሉ በተዘጋጀ ሽቱ፣ መዐዛዋ የሚያውድ፣ እንደ ጢስ ዐምድ ከምድረ በዳ የምትወጣው ይህች ማን ናት? 7 እነሆ፤ የሰሎሞን ሠረገላ በታዋቂዎቹ የእስራኤል መኳንንት፣ ስድሳ ጦረኞች ታጅባለች፤ 8 ሁሉም ሰይፍ የታጠቁ፣ ሁሉም በጦርነት የተፈተኑ ናቸው፤ የሌሊት አደጋን ለመከላከልም፣ እያንዳንዳቸው ሰይፋቸውን በወገባቸው ታጥቀዋል። 9 ንጉሥ ሰሎሞን የራሱን ሠረገላ ሠራ፤ የሠራውም ከሊባኖስ በመጣ ዕንጨት ነው። 10 ምሰሶዎቹን ከብር፣ መደገፊያውንም ከወርቅ ሠራ፤ መቀመጫውም በሐምራዊ ሐር የተሸፈነ ነው፤ ውስጡም በኢየሩሳሌም ቈነጃጅት፣ ፍቅር የተለበጠ ነው። 11 እናንተ የጽዮን ቈነጃጅት ውጡ፤ ንጉሥ ሰሎሞን አክሊሉን ደፍቶ እዩት፤ ዘውዱም ልቡ ሐሤት ባደረገባት፣ በዚያች በሰርጉ ዕለት፣ እናቱ የደፋችለት ነው። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.