መዝሙር 81 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 81 ለመዘምራን አለቃ፤ በጊቲት የሚዜም፣ የአሳፍ መዝሙር። 1 ብርታታችን ለሆነው አምላክ በደስታ ዘምሩ፤ ለያዕቆብ አምላክ እልል በሉ። 2 ዝማሬውን ጀምሩ፤ ከበሮውን ምቱ፤ በበገናና በመሰንቆ ጥዑም ዜማ አሰሙ። 3 በሙሉ ጨረቃ፣ በክብረ በዓላችን ዕለት፣ በወሩ መግቢያ፣ ጨረቃ ስትወለድ መለከት ንፉ፤ 4 ይህ ለእስራኤል የተሰጠ ሥርዐት፣ የያዕቆብም አምላክ ድንጋጌ ነውና። 5 ሙሉ ለሙሉ ግብጽን ለቅቆ በወጣ ጊዜ፣ ይህን ለዮሴፍ ደነገገለት። በማላውቀውም ቋንቋ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ 6 “ትከሻውን ከሸክም ገላገልሁት፤ እጁንም ቅርጫት ከመያዝ አሳረፍሁ። 7 በመከራህ ጊዜ ጠራኸኝ፤ እኔም ታደግሁህ፤ በነጐድጓድ መሰወሪያ ውስጥ መለስሁልህ፤ በመሪባ ውሃ ዘንድ ፈተንሁህ። ሴላ 8 “ሕዝቤ ሆይ፤ ሳስጠነቅቅህ ስማኝ፤ እስራኤል ሆይ፤ ምነው ብታደምጠኝ! 9 በአንተ ዘንድ ባዕድ አምላክ አይኑር፤ ለሌላም አምላክ አትስገድ። 10 ከግብጽ ምድር ያወጣሁህ፣ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝ፤ አፍህን በሰፊው ክፈተው፤ እኔም እሞላዋለሁ። 11 “ሕዝቤ ግን አላደመጠኝም፤ እስራኤልም እጅ አልሰጥ አለኝ። 12 ስለዚህ በገዛ ዕቅዳቸው እንዲሄዱ፣ አሳልፌ ለደንዳናው ልባቸው ሰጠኋቸው። 13 “ምነው ሕዝቤ ቢያደምጠኝ ኖሮ፣ እስራኤል በመንገዴ በሄደ ኖሮ፣ 14 ጠላቶቻቸውን ፈጥኜ ባንበረከክኋቸው ነበር፤ እጄን በባላጋራዎቻቸው ላይ ባነሣሁ ነበር። 15 እግዚአብሔርን የሚጠሉ በፊቱ ይርዳሉ፤ ቅጣታቸውም እስከ ዘላለም የሚዘልቅ ነው። 16 እናንተን ግን ምርጡን ስንዴ አበላችኋለሁ፤ ከዐለቱም ማር አጠግባችኋለሁ።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.