Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

መዝሙር 79 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


መዝሙር 79
የአሳፍ መዝሙር።

1 አምላክ ሆይ፤ ሕዝቦች ርስትህን ወረሩ፤ የተቀደሰውን ቤተ መቅደስህን አረከሱ፤ ኢየሩሳሌምንም አፈራርሰው ጣሏት።

2 የባሪያዎችህን ሬሳ ለሰማይ ወፎች፣ የቅዱሳንህንም ሥጋ ለምድር አራዊት፣ ምግብ አድርገው ሰጡ።

3 ደማቸውንም በኢየሩሳሌም ዙሪያ፣ እንደ ውሃ አፈሰሱ፤ የሚቀብራቸውም አልተገኘም።

4 እኛም ለጎረቤቶቻችን መዘባበቻ፣ በዙሪያችንም ላሉት መሣቂያ መሣለቂያ ሆንን።

5 እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህ እስከ መቼ ነው? የምትቈጣውስ ለዘላለም ነውን? ቅናትህስ እንደ እሳት ሲነድድ ይኖራልን?

6 በማያውቁህ ሕዝቦች ላይ፣ ስምህን በማይጠሩ፣ መንግሥታት ላይ፣ መዓትህን አፍስስ፤

7 ያዕቆብን በልተውታልና፤ መኖሪያ ቦታውንም ባድማ አድርገዋል።

8 የአባቶቻችንን ኀጢአት በእኛ ላይ አትቍጠርብን፤ ምሕረትህ ፈጥና ወደ እኛ ትምጣ፤ በጭንቅ ላይ እንገኛለንና።

9 አዳኛችን የሆንህ አምላክ ሆይ፤ ስለ ስምህ ክብር ብለህ ርዳን፤ ስለ ስምህ ስትል፣ ታደገን፤ ኀጢአታችንንም ይቅር በል።

10 ሕዝቦች፣ “አምላካቸው የት አለ?” ለምን ይበሉ? የፈሰሰውን የአገልጋዮችህን ደም በቀል፣ ዐይናችን እያየ ሕዝቦች ይወቁት።

11 የእስረኞች ሰቈቃ በፊትህ ይድረስ፤ በክንድህም ብርታት፣ ሞት የተፈረደባቸውን አድን።

12 ጌታ ሆይ፤ ጎረቤቶቻችን በአንተ ላይ የተዘባበቱትን መዘባበት፣ ሰባት ዕጥፍ አድርገህ አስታቅፋቸው።

13 እኛ ሕዝብህ፣ የማሰማሪያህ በጎችህ፣ ለዘላለም ምስጋና እናቀርብልሃለን፤ ከትውልድ እስከ ትውልድም፣ ውለታህን እንናገራለን።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告