Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

መዝሙር 66 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


መዝሙር 66
ለመዘምራን አለቃ፤ ማሕሌት፤ መዝሙር።

1 ምድር ሁሉ ለእግዚአብሔር እልል ይበል!

2 ለስሙ ክብር ዘምሩ፤ ውዳሴውንም አድምቁ።

3 እግዚአብሔርን እንዲህ በሉት፤ “ሥራህ እንዴት ግሩም ነው! ጠላቶችህ ከኀይልህ ታላቅነት የተነሣ፣ በፊትህ ይርዳሉ።

4 ምድር ሁሉ ይሰግድልሃል፤ በዝማሬ ያመሰግኑሃል፤ ለስምህም ይዘምራሉ።” ሴላ

5 ኑና፣ እግዚአብሔር ያደረገውን እዩ፤ በሰዎች መካከል ሥራው አስፈሪ ነው!

6 ባሕሩን የብስ አደረገው፤ ወንዙን በእግር ተሻገሩ፤ ኑ፣ በርሱ ደስ ይበለን።

7 በኀይሉ ለዘላለም ይገዛል፤ ዐይኖቹ ሕዝቦችን ይመለከታሉ፤ እንግዲህ ዐመፀኞች ቀና ቀና አይበሉ። ሴላ

8 ሕዝቦች ሆይ፤ አምላካችንን ባርኩ፤ የምስጋናውንም ድምፅ አሰሙ።

9 እኛን በሕይወት የሚያኖረን፣ እግራችንንም ከመንሸራተት የሚጠብቅ እርሱ ነው።

10 አምላክ ሆይ፤ አንተ ፈተንኸን፤ እንደ ብርም አነጠርኸን።

11 ወደ ወጥመድ አገባኸን፤ በጀርባችንም ሸክም ጫንህብን።

12 ሰዎች በራሳችን ላይ እንዲፈነጩ አደረግህ፤ በእሳትና በውሃ መካከል ዐለፍን፤ የኋላ ኋላ ግን ወደ በረከት አመጣኸን።

13 የሚቃጠል መሥዋዕት ይዤ ወደ መቅደስህ እገባለሁ፤ ስእለቴንም ለአንተ እፈጽማለሁ፤

14 በመከራ ጊዜ ከአፌ የወጣ፣ በከንፈሬም የተናገርሁት ስእለት ነው።

15 ፍሪዳዎችን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ፣ አውራ በጎችንም የሚጤስ ቍርባን አድርጌ አቀርብልሃለሁ፤ ኰርማዎችንና ፍየሎችንም እሠዋልሃለሁ። ሴላ

16 እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሁሉ፤ ኑና ስሙ፤ ለነፍሴ ያደረገላትን ልንገራችሁ።

17 በአፌ ወደ እርሱ ጮኽሁ፤ በአንደበቴም አመሰገንሁት።

18 ኀጢአትን በልቤ አስተናግጄ ቢሆን ኖሮ፣ ጌታ ባልሰማኝ ነበር።

19 አሁን ግን እግዚአብሔር በርግጥ ሰምቶኛል፤ ጸሎቴንም አድምጧል።

20 ጸሎቴን ያልናቀ፣ ምሕረቱንም ከእኔ ያላራቀ፣ እግዚአብሔር ምስጋና ይድረሰው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告