መዝሙር 64 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 64 ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 አምላክ ሆይ፤ የብሶት ቃሌን ስማ፤ ሕይወቴንም ከሚያስፈራ የጠላት ዛቻ ከልላት። 2 ከክፉዎች አድማ ሰውረኝ፤ ከዐመፀኞችም ሸንጎ ጋርደኝ። 3 እነርሱ ምላሳቸውን እንደ ሰይፍ ይስላሉ፤ መርዘኛ ቃላቸውንም እንደ ፍላጻ ያነጣጥራሉ። 4 አሸምቀው ንጹሑን ሰው ይነድፉታል፤ ድንገት ይነድፉታል፤ አይፈሩምም። 5 ክፉ ተግባር ለማከናወን እርስ በርስ ይመካከራሉ፤ በስውር ወጥመድ ለመዘርጋት ይነጋገራሉ፤ “ማንስ ሊያየን ይችላል?” ይባባላሉ። 6 ግፍን ያውጠነጥናሉ፤ ደግሞም፣ “የረቀቀች ሤራ አዘጋጅተናል” ይላሉ፤ አቤት! የሰው ልቡ፣ አእምሮውም እንዴት ጥልቅ ነው! 7 እግዚአብሔር ግን በፍላጻው ይነድፋቸዋል፤ እነርሱም ድንገት ይቈስላሉ። 8 በገዛ ምላሳቸው ያሰናክላቸዋል፤ ጥፋትንም ያመጣባቸዋል፤ የሚያዩአቸውም ሁሉ በትዝብት ራሳቸውን ይነቀንቃሉ። 9 የሰው ልጆች ሁሉ ይፈራሉ፤ የእግዚአብሔርን ሥራ በይፋ ያወራሉ፤ ያደረገውንም በጥሞና ያሰላስላሉ። 10 ጻድቅ በእግዚአብሔር ደስ ይበለው፤ እርሱንም መጠጊያ ያድርገው፤ ልበ ቅኖችም ሁሉ ደስ ይበላቸው። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.