መዝሙር 59 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 59 ለመዘምራን አለቃ፤ “አታጥፋ” በሚለው ቅኝት የሚዜም፤ ዳዊትን ለመግደል ሰዎች ቤቱን ከብበው እንዲጠብቁት ሳኦል በላካቸው ጊዜ፤ የዳዊት ሚክታም ። 1 አምላክ ሆይ፤ ከጠላቶቼ እጅ አድነኝ፤ ሊያጠቁኝ ከሚነሡብኝም ጠብቀኝ። 2 ከክፉ አድራጊዎች ታደገኝ፤ ደም ከተጠሙ ሰዎችም አድነኝ። 3 እነሆ በነፍሴ ላይ አድብተዋልና፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ጨካኞች ያለ በደሌ፣ ያለ ኀጢአቴ በላዬ ተሰብስበው ዶለቱብኝ። 4 እነርሱ ያለ በደሌ ሊያጠቁኝ ተዘጋጅተው መጡ፤ አንተ ግን ትረዳኝ ዘንድ ተነሥ፤ ሁኔታዬንም ተመልከት። 5 አንተ እግዚአብሔር አምላክ፣ የሰራዊት ጌታ የእስራኤል አምላክ ሆይ፤ ሕዝቦችን ሁሉ ለመቅጣት ተነሥ፤ በተንኰላቸው በደል የሚፈጽሙትንም ሁሉ አትማራቸው። ሴላ 6 እንደ ውሻ እያላዘኑ፣ በምሽት ተመልሰው ይመጣሉ፤ በከተማዪቱም ዙሪያ ይራወጣሉ። 7 ከአፋቸው የሚወጣውን ተመልከት፤ ሰይፍ በከንፈራቸው ላይ አለ፤ “ማን ሊሰማን ይችላል?” ይላሉና። 8 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ግን ትሥቅባቸዋለህ፤ ሕዝቦችን ሁሉ በንቀት ታያቸዋለህ። 9 ብርታቴ ሆይ፤ አንተን እጠብቃለሁ፤ አምላክ ሆይ፤ አንተ መጠጊያዬ ነህና። 10 እግዚአብሔር በምሕረቱ ይገናኘኛል፤ አምላኬ የጠላቶቼን ውድቀት ያሳየኛል። 11 ጋሻችን ጌታ ሆይ፤ አትግደላቸው፤ አለዚያ ሕዝቤ ይረሳል፤ በኀይልህ አንከራትታቸው፤ ዝቅ ዝቅም አድርጋቸው። 12 ከአፋቸው ስለሚወጣው ኀጢአት፣ ከከንፈራቸውም ስለሚሰነዘረው ቃል፣ በትዕቢታቸው ይያዙ። ስለ ተናገሩት መርገምና ውሸት፣ 13 በቍጣ አጥፋቸው፤ ፈጽመህም አስወግዳቸው፤ በዚህም እግዚአብሔር የያዕቆብ ገዥ መሆኑ፣ እስከ ምድር ዳርቻ ይታወቃል። ሴላ 14 እንደ ውሻ እያላዘኑ፣ በምሽት ተመልሰው ይመጣሉ፤ በከተማዪቱም ዙሪያ ይራወጣሉ። 15 ምግብ ፍለጋ ይንከራተታሉ፣ ካልጠገቡም ያላዝናሉ። 16 እኔ ግን ስለ ኀይልህ እዘምራለሁ፤ በማለዳም ስለ ምሕረትህ እዘምራለሁ፤ አንተ መጠጊያዬ፣ በመከራም ቀን ዐምባዬ ነህና። 17 ብርታቴ ሆይ፤ ውዳሴ አቀርብልሃለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ መጠጊያዬ፣ የምትወድደኝም አምላኬ ነህና። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.